Basic

BBC.com: ግራ መጋባትን የፈጠረው የህወሓት መግለጫ

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Friday, 15 June 2018

  • 15 ጁን 2018
 የህወሓት አርማ
TPLF FACEBOOK

ከእሑድ አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በር ዘግቶ የተሰበሰው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ረቡዕ አመሻሽ ላይ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ህወሀት የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢሕአዴግ ምክር ቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበትና ሳይወያዩበት እንደመጨረሻ ውሳኔ መወሰዱ እንደ ጉድለት እንደሚያየው አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ግንባሩ ህገ-ደንብ እና ተቋማዊ አሰራር ያልተከተሉ የአመራር ምደባዎችን እንዲያርም ጠይቋል።

የመግለጫው አንቀጾች ታዲያ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄን የሚጭሩ ሆነዋል ይላሉ ታዛቢዎች።

በቅርቡ የኢትዮጵያዊያን ሃገራዊ ንቅናቄ (ኢሃን) የሚል አዲስ ፓርቲ የመሠረቱት አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በአራቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረው የውስጥ ሽኩቻ ህወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ "አደባባይ ይዞት ወጥቷል" ይላሉ።

ነገር ግን የአራቱ ፓርቲዎች ፍቺ ቶሎ ሊፈጸም አይችልም የሚሉት አቶ ይልቃል ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንዳቸው አንዳቸውን ስለሚፈልጉ ነው በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

በመቀጠልም "ዞሮ ዞሮ ግን እየተዳከሙ ይሄዳሉ። በአገር ደረጃም ጉዳት ካደረሱ በኋላ ግን መፈራረሳቸው አይቀርም። ሽኩቻውና መነታረኩ ይቀጥላል። ከሕዝብ ጥያቄ ጋር ተዳምሮ የኢህአዴግ ፍጻሜ ይሆናል" ይላሉ።

ለአቶ ይልቃል እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሦስቱ ፓርቲዎች ህወሓት ለክቶ በሚሰጣቸው ነጻነት መጠን ነበር ሲተነፍሱ የኖሩት። አሁን ግን እስከዛሬው የነበረው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ የህወሓት ነጻ አውጪነትና የሌሎች ነጻነት ተቀባይነት ከሕዝብ ጥያቄ ጋር ጉልበት አግኝቶ እየተሸረሸረ መሆኑን ይገልፃሉ።

ብአዴን በከፊል ኦህዴድም በሰፊው በሕዝብ ድጋፍ ወደፊት እንዲመጡና ህወሓትን እንዲገዳደሩት አስችሏቸዋል የሚሉት አቶ ይልቃል ውስጣዊ ሽኩቻው በሰፊው እንደሚቀጥልም ይጠብቃሉ፤ ለእርሳቸው የግንባሩ የመፈራረስ አደጋም ቅርብ ነው።

ብይ አመድ አዲሱ ፈተናወሓት?

"ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቆራጥ እርምጃ ወደ ትግሉ ይገባሉ ብዬ አላስብም " ይላሉ አቶ ይልቃል። ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ሲያስቀምጡ "ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያልሙት የነበረውን ሥልጣን ከህወሓት ጋር በመላተም ሊያጡት ስለማይሹ " በማለት መሞገቻ ሃሳብ ያቀርባሉ።

"በእኔ ግምት ዶክተር አብይ ሥልጣናቸውን ማስረገጥ ስለሚወዱ ይቺን ሁለት ዓመት እንደምንም አመቻምቸው የሚቀጥለውን አምስት ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ማረጋገጥ ይሻሉ። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ከህወሓት ጋር የለየለት መቆራቆዝ ውስጥ መግባት አይፈልጉም።"

የቀድሞ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው ''የህወሓት ድምጹን ተነጥሎ ማሰማቱ ያልተለመደ ቢሆንም ክፋት የለውም'' ይላሉ፤ ''መለመድም አለበት'' ሲሉ ያስረግጣሉ።

"ህወሓቶች በአሁኑ ሰዓት ተገፍተናል የሚል ስሜት አላቸው። ስለተገፉ ሳይሆን ከነበራቸው ከፍተኛ ተጠቃሚነት ገሸሽ ስለተደረጉ ነው። ሁሉን ነገር እኛ ካልያዝነው ልክ አይሆንም ብለው ነው የሚያስቡት። ግብጾች ይሄን ያህል ውሃ ያስፈልገናል ይላሉ። ሌላው ግን ምንም አያስፈልገውም ብለው ያስባሉ' ህወሃትም እንደዚያ ነው የሚያስበው" በማለት ሃሳባቸውን ያብራራሉ።

ነባር አባላትና እውቅና

አቶ ሰይፉ "ህወሓት ቢፈልግ ሜዳሊያ ይሸልማቸው። ነገር ግን ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎችን ጡረታ የማውጣት ሥራ መንግሥታዊ አሠራር እንጂ የፓርቲ ሥራ አይደለም። ህወሓትም በዚህ ሊከፋው አይገባም" ይላሉ።

''እውነት ለመናገር አሁን ይቅር እንባባል እየተባለ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎቹ የሌብነት ዕውቅና ነው ሊሰጣቸው የሚገባው'' ሲሉም ጉዳዩን የሚያዩበት መንገድ የተለየ መሆኑን ያስረዳሉ።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ መሃሪ ዮሃንስ በበኩላቸው ከመግለጫው ምንም የተለየ ነገር እንዳላገኙ በመጥቀስ፤ የብአዴን ተሞክሮን አንስተው ከዚህ በፊትም ቢሆን ከኢህአዴግ መግለጫ ጋር የማይስማሙ ሃሳቦችን ሌሎች ፓርቲዎች አንጸባርቀው ነበር ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ይህን የህወሓት መግለጫ በማንሳትም ከዚህ በፊት ህወሓት ተገቢ ያልሆነ ቦታ ይዞ እንደነበረና ይህንን ለማስተካከል እንደሚደረግ እርምጃ ከሆነ ግን እንደሚቀበሉት ይገልፃሉ።

አክለውም "ዶክተር አብይ እና ሌሎች የኢህአዴግ አባላት የህወሓት አባላትን የማጥቃት እርምጃዎች የሚወሰዱ ከሆነ እናሳስባቸዋለን የሚል አይነት መልዕክት ያለው ይመስለኛል'' ብለዋል።

''ኢህአዴግ ቀውስ ውስጥ እንደገባና ሃገሪቱንም ቀውስ ውስጥ እንደከተታት ይታወቃል'' ያሉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ-መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና፤ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት እየተደራጀ እንደሆነ ይታወቃል ይላሉ።

የአቶ መሃሪን ሃሳብ የሚጋሩት ዶክተር መረራ፤ ከዚህ አልፎ ግን አንዱ ድርጅት እንዲህ ሆኗል፤ ሌላኛው ወዲህ ሄዷል የሚባል ነገር በእኔ እይታ ገና ነው ብለዋል ።

''የህወሓት መግለጫ ከዚህ በፊት ኢህአዴግ ሲሰራበት የነበረውን አሰራር የጣሰ ነው ብዬ አላምንም'' ያሉት ዶክተር መረራ፤ ''ፓርቲው ችግር ውስጥ ስለሆነ እንደድሮው የውስጥ ልዩነቶቹን ደብቆ ማቆየት ስላልቻለ ነው'' ይላሉ።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events