Basic

Goolgule.com: የለማ መገርሣ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ትርክትና የመሐመድ አዴሞ ሹመት

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Sunday, 14 October 2018

የኦሮሚያ ክልላዊ ምክርቤት ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. የበርካታ አዲስ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀትን ሲያጸድቅ የአዳዲስ ተሿሚዎችን ሹመትም አጽድቋል። ከእነዚህ መካከል የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዋና ዳይሬክተር እንዲሆን የተሾመው መሐመድ አዴሞ ነው። የአቶ ለማ መገርሣ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የሚለው ልብ የሚያረካ አባባል ከመሐመድ አዴሞ ለዓመታት የዘለቀ ፀረ ኢትዮጵያዊነት አቋም ጋር የሚጋጭባቸው ወገኖች የሹመቱ ጉዳይ ትልቅ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ መሐመድን ብቃት ካለው ባለሙያ አንጻር የሚመለከቱት ሹመቱ ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን ገጣሚም ነው ይላሉ።

ለሃያ ሰባት ዓመታት በግፍ ቀንበር ሥር የነበረውን ሕዝብ በለውጥ ማዕበል ውስጥ በማስገባት “እንቁላሉን ከውስጥ የሰበሩት” የለማ ቡድን (ቲምለማ) አባላት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ሞተ፣ አበቃለት የተባለውን ኢትዮጵያዊነትንም እንደገና እንዲያንሠራራ አድርገዋል። ከዚህም አንጻር በአንድ ወቅት አቶ ለማ “የኢትዮጵያ ህዝቦችን ያስተሳሰረው የደም ሐረግ ብርቱ ነው። ድልድያችን ሻማ፣ ከዘራችን ቄጤማ አይደለም፤ ዘመን ባስቆጠረ አብሮነታችን ወደላቀ ደረጃ እንደምንሸጋገር እናምናለን” ማለታቸው ይታወሳል። ከዚያም ሲያልፍ የእርሳቸው ቡድን አገር ያዳነ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ይህንን ያህል ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ ያደረጉ ታላቅ ሰው እንደ መሐመድ አዴሞ ዓይነት ፀረ ኢትዮጵያዊ አቋሙን በገሃድ ለዓመታት ሲሰብክ የቆየ ሰው የኦሮሚያን ሚዲያ እንዲመራ እንዴት ፈቀዱ ሲሉ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ይጠይቃሉ። አቶ መሐመድ አዴሞ በርግጥ በባለሙያነቱ ብቃት ያለው ሰው ነው በማለት የሚናገሩ በፖለቲካ አቋሙ ግን ፍጹም ለቦታው የማይመጥን ነው በማለት ያለፈውን ታሪኩን በማንሳት ይዘረዝራሉ።

ጎልጉል ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሚዲያ ሰው እንደሚሉት “መሐመድን በቅርብ ባላውቀውም ከሥራ ጋር በተያያዘ ለመገናኘት ችለናል፤ በተደጋጋሚ በማንኛውም ሚዲያ ላይ ቃለምልልስ እንዲያደርግ ሲጠየቅ በእንግሊዝኛ ወይም በኦሮሚኛ ካልሆነ አልቀርብም በማለት መልስ የሚሰጥ ሰው እንደነበር አውቃለሁ፤ ለራሴም ይህንኑ መልስ ሰጥቶኛል” በማለት ይናገራሉ።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት መሐመድን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸውን በመጥቀስ ሲናገሩ፤ “እኔ እስከማውቀውና በኔ አመለካከት መሐመድ አዴሞ በፀረ ኢትዮጵያዊነት ከጃዋር የሚበልጥ ጽንፈኛ ነው ለማለት እችላለሁ፤ ጃዋር የፖለቲካ ቁማር የሚጫወት ጥቅመኛ ስለሆነ አንዳንዴ እንኳን ሰዎች ደስ የሚላቸውን በመናገር የሚደልል ቁጭ በሉ የሚባል ዓይነት ነው፤ መሐመድ ግን ተሳስቶ እንኳን ይህንን የሚያደርግ አይደለም፤ ጥላቻውን ባገኘው መስመር ያለልክ የሚናገርና የሚጽፍ ነው” ይላሉ።

መሐመድ አዴሞ ከአስራስድስት ዓመት የስደት ኑሮ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የለማን ቡድን የተቀላቀለው ከበርካቶች አስቀድሞ ነው። ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የአቶ ለማ መገርሣ አማካሪ ሆኖ ሲሠራ ቆቷል። ድምጻቸው ጎልቶ ባይሰማም የመሐመድን በፍጥነት የአቶ ለማ አማካሪ መሆን የጠየቁ ግን ጥቂቶች አልነበሩም። በተለይ እርሱ ለዓመታት ሲያራምደው የነበረው አቋም፤ የለማ ቡድን ከሚከተለው የኢትዮጵያዊነት ትርክት ጋር በቀጥታ የሚጋጭ በመሆኑ መሐመድ ለአቶ ለማ ሊሰጠው የሚችለው ምክር ምን እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ ሆኖ ቆይቷል። ከዚህ አልፎ ግን የኦቢኤን ዋና ዳይሬክተር ሆኖ መሾሙ አቶ ለማ መሐመድን አጠመቁት ወይስ መሐመድ አቶ ለማን “በምክሩ” አሸነፋቸው ብሎ የሚያስጠይቅ ሆኗል።

መሐመድ አዴሞን በቅርብ የሚያውቁትና በኦሮሚያ ውስጥ በጋዜጠኝነት የሚሠሩ ለጎልጉል የሰጡት አስተያየቶች መሐመድን የሚጠራጠሩት ከሰጡት በሌላው ጥግ የሚመደብ ነው። “መሐመድን ልንለካ የሚገባው ከለውጡ በፊት ባለው አቋሙ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ባለው ነው፤ እኔ እስከማውቀው ከለውጡ በኋላ ከዚህ በፊት የነበረውን አቋም የማያራምድ መሆኑን ተመልክቻለሁ፤ ጽሁፎቹን ስከታተል ስለነበር እንደበፊቱ ዓይነት ምንም ዓይነት ነገሮችን ሲጽፍ አላነበብኩም” የሚሉት ኦቢኤንን ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን በግል ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያ ናቸው።

ስለ ኦቢኤን በቅርብ የሚያውቁ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ደግሞ በፓርቲው (ኦዴፓ) በተወሰነው መሠረት ከፓርቲው ውጪ ያሉ ሰዎች ወይም ባለሙዎች በአመራር ላይ ብቃታቸው እየተመዘነ ይመደቡ በሚል በተወሰነው መሠረት መሐመድ ይህንን መስፈርት የሚሟላ ሰው ነው። ፓርቲውም ቃሉን በመጠበቁ ሊመሰገን ይገባዋል ይላሉ።

ጎልጉል ከተለያዩ ባለሙያዎችና በኦሮሚያ ላይ በሚዲያው አካባቢ የሚሠሩ ሰዎችን አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሠረት አብዛኛው በፖለቲካው ዙሪያ ያለ ሰው የመሐመድን መሾም እንደሚደግፍ ነው። አንዳንዶች እንደተናገሩት ደግሞ ከስድስት ወር በፊት ጽንፈኛ አቋም መያዝ የመሐመድ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኦሮሞዎች አመለካከት ነበር፤ አሁን ግን ለውጥ ከመጣ ወዲህ በርካታዎቹ ለዘብተኛ ወደመሆንና የጋራ የሆነች አገር ለመሥራት ፍላጎትም ፈቃደኝነትም እያሳዩ ነው፤ መሐመድም በዚሁ መታየት አለበት የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያዊነት አቋማቸው የበርካታዎችን ቀልብ የሳቡት አቶ ለማ መገርሣም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች አንዳንዶች በዓይነቁራኛ ይመለከቱታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንዶች አልፈው ተርፈው የትግራይ የበላይነት በኦሮሞ እየተተካ ነው የሚል የድፍረት አስተያየት በመስጠት ይሞግታሉ።

የመሐመድ አዴሞን ሹመት በርካታ በሙያው ላይ ያሉ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቲች በተለይ ደግሞ የህወሓትን አቋም በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የሚሰብኩ “ታጋዮች” ደግፈዋል፣ ሙያዊ ብቃቱንም አሞካሽተዋል። ፍጹም መቀበል የከበዳቸው ደግሞ ከፓርቲ ውጪ ያሉ ሰዎች ይሾሙ ቢባልም ለቦታው የሚመጥን ሌላ አወዛጋቢ ያልሆነ ኦሮሞ ጠፍቶ ነው አቶ ለማ ይህንን ሹመት የፈቀዱት ብለው በመጠየቅ ቀጥሎስ የጃዋርንና የፀጋዬ አራርሣን ሹመት እንጠብቅ ሲሉ ይሳለቃሉ።

መሐመድ አዴሞ በትዊተር ገጹ ላይ ኦቢኤን የሕዝብ ሚዲያ መሆኑን በመግለጽ የግል አመለካከቱ በሙያዊ ሥራውና (በሹመቱ) ላይ ተጽዕኖ እንደማያስከትልበት፤ ሥራውንም የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ እንደሚያከናውን ተናግሯል። ይህንን የተመለከቱ አንድ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት “ቅዱሱ መጽሐፍ ‹በሥራቸው ታውቋቸዋላችሁ› እንዳለው እንግዲህ ወደፊት በሥራው እናየዋለን” ብለዋል።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events