Basic

Goolgule.com: ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያ 20 ቢሊዮን ዶላር ተዘርፋለች!

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Wednesday, 13 February 2019

 

ህወሓት/ኢህአዴግ በግፍ ሲገዛት በነበረችው ኢትዮጵያ፣ አንድ ዓመት ያልሞላው የለውጥ ሒደት ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ባሉት ዘጠኝ ዓመታት (እኤአ 2003 – 2012) ባሉት ዓመታት ውስጥ 20ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ወጥቷል፤ ተዘርፏል። የሪፖርተሩ ብርሃኑ ፈቃደ ያቀናበረው እንዲህ ይነበባል፤

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  (ተመድ) ሥር የሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የአፍሪካ የጤና ክብካቤና የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ እንደሸሸባት አስታውቆ፣ ይህ ገንዘብ ለጤናው ዘርፍ የምታውለውን 87 በመቶ በጀት እንደሚሸፍን አመለከተ።

ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዘጠኝ ዓመታት በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሕገወጥ ገንዘብ በሚያሸሹ አካላት ሳቢያ ተጎጂ ሆናለች ብሏል። በዚህ ሳቢያም ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው ዝቅተኛ በጀትም  በሚሸሸው ገንዘብ ምክንያት ከባድ ተፅዕኖ ውስጥ እንደቆየ አመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ኢኮኖሚዋ (ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት አኳያ) አንድ በመቶ ለጤናው ዘርፍ ትመድባለች ያለው ሪፖርቱ፣ በአንፃሩ በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየሸሸባት በመሆኑ 87 በመቶውን የጤናውን ዘርፍ በጀት ወደ ውጭ የሚሸሸው ገንዘብ እንደሚሸፍነው ሪፖርቱ አሥፍሯል።

ከዚህም በተጓዳኝ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከሚያወጣው ወጪና ለዕዳ ክፍያ ከሚያውለው ገንዘብ ተቀናንሶ ሲሰላም፣ አገሪቱ በየዓመቱ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ክፍተት እንደሚገጥማት ታውቋል።

እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት አማካይ ጠቅላላ የዕዳ ክምችት መጠን 55 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ተመድ አውስቶ፣ ከሕገወጥ ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ባሻገር ለዕዳ ክፍያ የሚውለው ከፍተኛ ገንዘብም እንደ ጤናው መስክ ባሉት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ጫና ማሳደሩን አስታውቋል።

እንዲህ ያሉትን እውነታዎች ያጎላው የተመድ ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ አፍሪካ በጠቅላላው ከ300 እስከ 600 ቢሊዮን ዶላር  በሕገወጦች ገንዘብ የማሸሽ ድርጊት ሳቢያ ማጣቷትን አመልክቷል። ከጤናው መስክ አኳያም አገሮች ከዓመታዊ በጀታቸው አምስት በመቶ ለጤና ዘርፍ ይመድባሉ ተብሎ ቢገመት፣ በአፍሪካ ለጤናው መስክ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የ66 ቢሊዮን ዶላር ክፍት እንደሚታይ ይፋ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዳንጎቴ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባሰናዳው የ“አፍሪካ ቢዝነስ ሔልዝ ፎረም 2019” በተሰኘው መድረክ ላይ የናይጄሪያ ቢሊየነር ሐጂ አሊኮ ዳንጎቴ ልጅ ሐሊማ ዳንጎቴ ይፋ እንዳደረገችው፣ የዳንጎቴ ግሩፕ ኩባንያዎች ከታክስ ተቀናሽ በኋላ ከሚያስገቡት ትርፍ ውስጥ በአፍሪካ ጤናው ዘርፍ እንዲውል የአንድ በመቶ ገቢያቸውን ያውላሉ።

 እ.ኤ.አ. በ1994 የተመሠረተው የዳንጎቴ ፋውንዴሽን ከምሥረታው ጀምሮ፣ ለጤናና መሰል የበጎ ተግባራት የሚውል የ1.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን የፋውንዴሽኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የአፍሪካ መንግሥታት ብቻቸውን ከፍተኛ የጤና ክብካቤ ችግሮች በሚስተዋሉባት አፍሪካ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደማይችሉ በማመን፣ ድጋፍ ለማድረግ በዳንጎቴ ፋውንዴሽን አማካይነት መሰባሰብ የጀመሩት የአፍሪካ ባለሀብቶች፣ ለጤናው ዘርፍ የአፍሪካ የቢዝነስ ጥምረት የተሰኘ መድረክም በአዲስ አበባው ፎረም ይፋ አድርገዋል።

የዓለም እግር ኳስ ኮከቡ ኮትዲቯራዊ ዲዲዬር ድሮግባ፣ በጤናና በትምህርት መስክ ለአፍሪካውያን ድጋፍ የሚያደርግበትን የዲዲዬር ድሮግባ ፋውንዴሽንን እንቅስቃሴዎች በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል።

በዚሁ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ፣ የቦትስዋና ፕሬዚዳንት ሞክዊትሲ ማሲሲአ፣ እንዲሁም የኬንያ፣ የግብፅና የሌሎች አገሮች የጤና ሚኒስትሮች ስለአገሮቻቸው የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ገለጻ አቅርበዋል። (ምንጭ፤ ሪፖርተር)


6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events