Basic

Dahabshiil long banner 728x90
Eritrea for mobile viewing

EthiopianReporter.com: ቆይታ: ‹‹በትግራይ ላይ የሚሠራው አንድነትን የሚበትን ነው›› ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Tuesday, 18 June 2019

‹‹በትግራይ ላይ የሚሠራው አንድነትን የሚበትን ነው››  ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ማስተዳደር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የትግራይ ክልል በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በኩል እየደረሱበት ስላሉ ጫናዎችና ግፊቶች ከረር ያሉ ቅሬታዎችን በማሰማት፣ የክልሉ ሕዝብ ከተስፋ መቁረጥ አፋፍ ስለደረሰባቸው ጉዳዮች ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ በትግራይ ክልል ላይ ያነጣጠረ የዘር ጥቃት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በተለይም በአማራ ክልል በኩል እየተፈጸመ ስለመሆኑ የሚሟገቱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በመንግሥት ዕውቅና ጭምር ዋና ዋና የፌዴራል መንግሥት የገነባቸው መንገዶች ሆነ ተብለው ሲዘጉ እየታየ በዝምታ መታለፋቸው፣ መንግሥት ጉዳዩን እንዲመለከተውና ጣልቃ በመግባት ሥርዓት እንዲያሲዝ ሲጠየቅም፣ መለሳለስ ማሳየቱ ፖለቲካዊ ሥሌት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በቀድሞው የደኅንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የተመሠረተውን ክስ ያጣጣሉት ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ በደኅንነት ሥራ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኃላፊዎችና ሌሎችም ለአገር በመሥራታቸውና ሕዝብን ከውጭ ጥቃት በመከላከላቸው ሊከበሩ ይገባቸዋል በማለት መታሰራቸው እንደሚያንገበግባቸው ተናግረዋል፡፡ በኢንተሊጀንስ ሥራ ‹‹ለምን ሰለልክ ተብለው ታስረዋል›› በማለት በመስኩ በአገር ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሥራ ስለመሠራቱ፣ ፍትሕን መሻቱ በእውነት ተፈልጎ ከሆነ ግን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎች የነበሩና ሌሎችም በየድርሻቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በአዲሱ አስተዳደር ተስፋ ማጣቱን፣ የመገንጠል ሐሳብ ውስጥ መግባቱን እያባባሱ ካሉ አሠራሮች መካከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን በትግራይ ክልል ላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ተስፋፍቷል ማለቱና ይኼንኑ ተከትሎም የበጀት ቅነሳ ለማድረግ መነሳቱ፣ ከዚህ ቀደም ሲከሰቱ የነበሩ ጫናዎች ተደማምረው ሕዝቡ ለገባበት ተስፋ መቁረጥ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡ ከዘር ተኮር ጥቃት እስከ ኤርትራ ጉዳይ፣ ከደኅንነት ኃላፊዎች እስከ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ ባሉት ነጥቦች ላይ ሳሙኤል ጌታቸው ከምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይ የልማት ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ እርስዎ ከመጡ ወዲህ ስላሉት ለውጦች ቢነግሩን?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- መጀመርያ ለምን የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ለውጡ ከካቻምና ጀምሮ በተለይ ዓምና ሲደረግ በርካታ ግምገማዎች ተካሂደው ነበር፡፡ በመንግሥት ሥራና በሕዝቡ ላይ የነበረው ሁኔታ ግምገማ፣ ድርጅታዊ ግምገማና ሌሎችም አጠቃላይ ግምገማዎች ተካሄደዋል፡፡ በተለይ በመቀሌ 35 ቀናት የወሰደብንን አጠቃላይ ግምገማ አካሂደናል፡፡ ለውጡ የግምገማ ውጤት ነው፡፡ ብዙ ያልሠራናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የሠራናቸውም አሉ፡፡ እንደ ክልልም እንደ አገርም በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ነገር ግን በልማቱም በሌላውም መስክ ከዚህ በላይ መሥራት ይጠበቅን ነበር፡፡ አካሄዳችንን እንቀይር ለውጥ ያስፈልጋል ብለን ደምድመናል፡፡ ለውጥ ያስፈልጋል ብቻም ሳይሆን፣ ለውጡን እንዴት እናምጣው በሚለው ዙሪያም ያስቀመጣናቸው ሐሳቦች አሉ፡፡ በርካታ ችግሮች ስለነበሩ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያመነጩ ምሁራንን እናሳትፍ ብለናል፡፡ ከግምገማው በኋላ በነበሩት ሁለት ወራት ውስጥ የትግራይ ምሁራንን በየመስኩ አሳትፈናል፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ጥራት ችግር አለ ብለናል፡፡ የትምህርቱን ጥራት እንዴት እናሻሽል በሚለው ላይ መንግሥት ያስቀመጣቸው ሐሳቦች አሉ፡፡ ግን ደግሞ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘትና በአፈጻጸም የጎደላቸው ነገር ስለነበር ነው ጥራት ያልመጣው የሚል ሐሳብ በመንግሥት በኩል አለ፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት የሚያስፈልገን ከሆነ አዳዲስ ነገሮችን ማየት ቢያስፈልገንስ ብለን ልምዱም፣ ብቃቱም ዕውቀቱም ያላቸውን በዘርፉ ብዙ የጻፉ ሰዎች ሐሳብ እንዲያመጡ የቤት ሥራ ሰጥተናቸው ነበር፡፡ ወደ ልማቱም ሥራ ስንመጣ እንደዚሁ አድርገናል፡፡ የትግራይን ልማት እንዴት እናሻሽል፣ ኢንቨስትመንቱን እንዴት እናሻሽለው ብለን ዓይተናል፡፡ ችግሮች እንዳሉ ገምግመናል፡፡ በቂ ሥራ እንዳልተሠራ ዓይተናል፡፡ እንዴት እናሻሽል በሚለው ላይ በርካታ ምሁራንን አሳትፈናል፡፡ ትልቅ ቡድን የተዋቀረበት የኢንቨስትመንት መስኩን የሚያጠና የምሁራን ቡድን ዘርፉን በደንብ አጥንቷል፡፡ እንደ ፖለቲካ አመራርና እንደ መንግሥትም የገመገምነው በጣም ጥልቀት እንዲኖረውና መፍትሔ እንዲቀመጥበት በተባለው መሠረት መፍትሔዎቹን መተግበር ጀምረናል፡፡ ይሠሩ የተባሉትን ነገሮች መተግበር ጀምረናል፡፡ ተቋማዊ ለውጦች ይደረጉ በተባለው መሠረት በትግራይ ብቻም ሳይሆን፣ በየክልሉም በሌላ አግባብ የኢንቨስትመንትና የኤክስፖርት ኮሚሽን ይቋቋም የሚል ሐሳብ ምሑራኑ አመነጩ፡፡ አገልግሎት በአንድ ማዕከል መስጠቱ ኤክስፖርትን ጨምሮ እንዲሠራበት የሚል ሐሳብ በማምጣታቸው ይህንኑ በትግራይ ክልል ምክር ቤት አስወስነን ወደ ትግበራ ገብተናል፡፡ ሌሎች ሐሳቦችም አሉ፡፡

ልማቱ በብዙ መልኩ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ይህ የኢንቨስትመንቱ ግን አንዱ ሐሳብ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ለውጥ እናምጣ የሚለው ነው መሠረቱ፡፡ የጎደለን ነገር አለ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ድህነትም አለ፡፡ የትግራይን ሁኔታ ከአገር አቀፉ ደረጃ ጋር ስናነፃፅረው ድህነቱ ከፍተኛ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ከፍ ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንደሚያከናውነው፣ በትግራይ ክልል በራሳችን ጥናት አካሂደናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የተውጣጣ ቡድን የትግራይን ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲያጠና አድርገናል፡፡ በወረዳና በቤተሰብ ደረጃ በዝርዝር ጥናት እንዲካሔድ አድርገናል፡፡ ከአገር አቀፉ ጥናት ለየት ይላል፡፡ በመሆኑም ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ካወጣው መረጃ በላይ የድህነት ችግር በትግራይ እንዳለ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ግፊት አለ፡፡ ሕዝቡ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ መኖር የለበትም፡፡ እያወራን ያለነው ስለትግራይ ስለሆነ ነው እንጂ ሌላውም ሕዝብ በድህነት ውስጥ መኖር የለበትም፡፡ በመሆኑም በትግራይ ከፍተኛ ድህነት ስላለ ልማቱን በዚያው መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለማምጣት መፍጠን አለብን፡፡ የነበረውን የአፈጻጸም ችግር መፍታት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያለንበት ነባራዊ ሁኔታን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀየር ተጨማሪ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ለለውጡ በርካታ ግብዓቶች አሉ፡፡ ተጠንቶ በ2011 ዓ.ም. ይኼንን ሥራ ወደ መሥራቱ እንግባ ተብሎ የተጀመረ አይደለም፡፡ የአንድ ዓመት ሥራ አይደለም፡፡ የበርካታ ዓመታት ጉድለቶችንና አዳዲስ ሐሳቦችንም በመረጃ ላይ በመመሥረት ይህ ግፊት ያሳደረበት እንቅስቃሴ ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ጅምር ነው፡፡ በሁሉም መስክ እንቅስቃሴው አለ፡፡

በአርሶ አደሩ አካባቢም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በዋናነት ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረውን ችግር ከግምገማው በኋላ ለመፍታት ጥረት አድርገናል፡፡ ማዳበሪያ ከመውሰድ ጀምሮ በአርሶ አደሩ ላይ በጫና የሚሠሩ ሥራዎች ነበሩ፡፡ አሁን ነፃ እንዲሆን አድርገናል፡፡ የማዳበሪያ አጠቃቀም በሳይንስ ላይ የተመረኮዘና የኤክስቴንሽን ሠራተኞች በሚያስተምሩት መሠረት የሚካሄድ ቢሆንም፣ አርሶ አደሩ ግን በግፊትና በጫና ነበር እንዲወስድ የሚገደደው፡፡ በራሱ ፈልጎ መጥቶ እንዲወስድ ማድረግ መቻል ትልቅ ለውጥ ነው እንላለን፡፡ በክልል ደረጃ ሙሉ በሙሉ እንደዚህ አድርገናል፡፡ አርሶ አደሩ በፍላጎቱ እንዲሠራ ነው የምንፈልገው፡፡ እኛ ነን የምናውቀው፣ እኛ የተሻለ ሐሳብ አለን ብለን አንጫነውም፡፡ ከድህነት እንዲወጣ ብንፈልግም ከእኛ በላይ በድህነት መሰቃየቱን የሚያውቀው ራሱ አርሶ አደሩ በመሆኑ መውጫ መንገዱንም የሚያውቀው እሱ ነው፡፡ ስለዚህ ጫና ማስከተል ስሜቱንም መጉዳት ስለሚሆን በአካሄዳችን ላይ የነበሩ ጉድለቶችን ከጫፍ ጫፍ አስተካክለናል፡፡ በፍላጎቱ መሥራት ሲጀምር የተሻለ የለውጥ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ገና አንድ ዓመት ቢሆንም የተሻለ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በስብሰባና በሌላውም ምክንያት በገጠሩ አካባቢ ሳይቀር ይጠፋ የነበረውን ጊዜም እንዲቀንስ፣ ለልማት የሚውለው ጊዜም እየጨመረ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ የልማት ድጋፍ የሚሰጠውም አካል ጊዜውን ለዚሁ እንዲያውል፣ በተመደበበት ሥራ ላይ እንዲያደርግ በመደረጉ ለውጦች እየመጡ ነው፡፡

ትልቁ ለውጥ ግን ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የመጣው ነው፡፡ የአርሶ አደሩ ከዚህ በፊት የነበረውን ማሻሻል ነው ያስፈለገው፡፡ የኢንቨስትመንት ግን ያልነበረና አዲስ ነገር ነው፡፡ በመቀሌ አንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ አለ፡፡ ግን አይበቃም፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጪ ለማደግ የሚያነሳሱ ፍላጎቶች አሉ፡፡ የእኛ አያያዝም ለውጥ መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው በአጠቃላይ የፖለቲካው ከባቢ ሁኔታ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በትግራይ ካለው ሰላም ጋር በንፅፅር ሲታይ ችግር አለበት፡፡ ስለዚህም ሰላም ፈላጊ ሁሉ እየመጣ ነው፡፡ የትግራይ ብቻም ሳይሆን፣ የውጭ ኢንቨስተርም ጭምር እየመጣ ነው፡፡ ለምን እዚህ ክልል ውስጥ ሰላም አለ፡፡ የሚሠራና ሥራ ላይ ያለ መንግሥት አለ፡፡ የፈራረሰ የቀበሌ መዋቅር አይለደም ያለን፡፡ የነበረውን መዋቅር በአዳዲስ ኃይል አሻሽለን አገልግሎት ተኮር በማድረግ አሻሻልነው እንጂ፣ የተዳከመና እንደ ሌላው የሚፈርስ አይደለም፡፡ ሰላም በራሱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አስችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰላም ለቤተሰብ መሪም ሆነ አገርን ለሚመራ አካል የሚያስፈልገው፣ መጪ ትውልድም ሥራውንም ሆነ ትምህርቱን በአግባቡ እንዲያተኩርበት ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ኢንቨስተሮች ላይ ድንጋይ ሲወረወር ይታያል፡፡ በቅርቡም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲገዳደሉ ዓይተናል፡፡ እንደ አገር ወዴት እየሄድን ነው?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ለዚህ ነው የትግራይ ይለያል ብዬ ያነሳሁት፡፡ እንደ አገር በጣም መጥፎና አደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ የአንድ ወይም የሁለት ተማሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ እስካሁን ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በሁሉም አካባቢ ሞት እየተከሰተ ነው፡፡ ከፍተኛ የሞት መጠን እየታየ ነው፡፡ ችግሩ እየቀጠለ ነው፡፡ በርከት ያለው የሞት ቁጥርም ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ የነበረውን ብትመለከት እንኳ እንዲህ ያለ ግድያ አልታየም፡፡ ችግሩ የሕዝቡ ነው ልትል አትችልም፡፡ የተበላሸ አመራር፣ የተበላሸ ፖለቲካና የተበላሸ መንግሥት እንዳለን የሚያሳይ ነው፡፡ ሕግ በሁሉም ዘንድ ይከበራል ብንልም፣ ሕጉን ማስከበር ያለበት የመጨረሻው አካል ግን መንግሥት ነው፡፡ ሥነ ሥርዓት ማስያዝ አለበት፡፡ ለችግሩ መነሻ ምልክቶች ነበሩ፡፡ ዝም ብለህ ወደ መገዳደል አትገባም፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት የሚታዩ ምልክቶች ይኖራሉ፡፡ የአስተሳሰብና የሐሳብ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁ በድንገት የሚፈነዳ ነገር ሳይሆን፣ መነሻ ያለው ክስተት ነው፡፡ ይህን ዓይቶና ተከታትሎ ሥርዓት የሚያሲዝ መንግሥት ነው፡፡ ሕግ ማስከበሩ ላይ መንግሥት መዳከሙን የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ሥርዓት የወደቀው ነገር ካልተስተካከለ መገዳደሉ ሊቀጥል ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ችግሩ በአንድ ወይም በሁለት ተማሪዎች ሞት የሚታይ አይደለም፡፡ በትግራይ ግን እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡ ልዩነቱም እሱ ነው፡፡

እዚህ እንደ ክልል ባለው የራስ አስተዳደር መብት መሠረት የሚሠራ መንግሥት አለ፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር እየተግባባ የሚሠራ መንግሥት ነው፡፡ ከዚህ በቀር ግን የልማቱ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በተለያየ መንገድ ይገለጹ እንጂ ችግሮቹ እንደ አገር ሁሉም ጋ ያሉ ናቸው፡፡ በትግራይ ግን ችግሮቹ የሚገለጹት በመገዳደል አይደለም፡፡ የተገደለውን ተማሪ አንስተሃል፡፡ ለእኛ እንግዳና አዲስ ነገር ነው፡፡ በሌላው ክልል እኮ በመቶዎች ነው እየተገደሉ ያሉት፡፡ በቤኒሻንጉልና በሌላውም የምናየው አገሩ የሞት አገር እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ ይህን መቆጣጠር ያልቻለ መንግሥት እንዳለ ያሳያል፡፡ እኛ አንድ አጋጣሚ ገጥሞን መኮነን፣ አለበት የተበላሸ አስተሳሰብ ነው ብለን ዕርምጃ ወስደናል፡፡ በተማሪው ግድያ ላይ የተሳተፉ ሰዎችን አስረናል፡፡ ከግቢ ወጥተው የተደበቁና እየተፈለጉ ያሉም አሉ፡፡ ለቅመን እናስገባለን፡፡ አጥፊውን ለሕግ በማቅረብ የተጎዳውን አካል መካስ ይገባል፡፡ ሕግ አልተከበረም ብሎ መኮነን ብቻም ሳይሆን መቆጣጠርም አለብን፡፡ አጥፊን ስትቆጣጠር ችግሩ እንዳይቀጥል ታደርጋለህ፡፡ ከቀጠለም ታስቆመዋለህ፡፡ ዝም ካልክ ግን መቀጣጠሉ አይቀርም፡፡ በየአካባቢው የምናየው ይኼንን ነው፡፡ ዝም ስትል እየተቀጣጠለ ይቀጥላል፡፡ መንግሥት የለም፣ ሥርዓት የለም ያስብላል፡፡ ለጥፋት የሚቆም ወገን የለም ማለትም አይደለም፡፡ ሁሉም ሰላማዊ አይሆንም፡፡ መንግሥት መሥራት ካልቻለ አጥፊው እንደፈለገው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ውድቀቱ ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሚፈጸመው ጥቃት ተፈናቅሎ የመጣው የትግራይ ሰው ብዙ ነው፡፡ በተለይ ዓምና ብዙ ሰው ተፈናቅሏል፡፡ ከአጠገባችን ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ ብዙ ሰው ንብረቱ ተቃጥሎ፣ ተዘርፎ፣ ተገድሎ፣ በሥነ ልቦናውም ብዙ ሰው ተጎድቷል፡፡ ስለተጎዳን እንጉዳ የሚል አስተሳሰብ እዚህ የለም፡፡ ጉዳትም ደርሶ የመሸከም ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ደብረ ማርቆስ ላይ የትግራይ ሰው ስለተገደለ፣ እዚህ የአማራ ተወላጅ በመግደል ነፍስ ልትሰጥ አትችልም፡፡ ለግድያ መልሱ ግድያ አይደለም፡፡ ይህ የበለጠ ያባብሳል፡፡ አጥፊን በሕግ ነው የምትቀጣው፡፡ ሰው ቅሬታ የሚያነሳው ዝም ስላልን እኮ ነው ይልሃል፡፡ ሰው እየሞተ ለምን የሆነ ነገር አይደረግም ይልሃል፡፡ መንግሥት መሥራቱ ለብዙ ነገር መፍትሔ አለው፡፡ በብዙ መንገድ የትግራይ ክልል የተሻለ ነው የሚሠራው፡፡ ጉዳት ባይኖርም ሲከሰት ግን ወዲያውኑ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ እንዳይቀጥል ስለምንፈልግ ነው፡፡ ሕዝብን ማንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ሕዝብ የሚመራው ይፈልጋል፡፡ ችግር ሲኖር ወደፊት በመምጣት ኃላፊነት የሚወስድ አካል መሆን አለበት፡፡ የመንግሥትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ላይ በአገራችን በሰፊው የሚታዩ ልዩነቶች ስላሉ፣ ከፌዴራል ጀምሮ ሕዝቡ በፍፁም ሊገመት በማይችል ደረጃ እየተጎዳ ነው፡፡ ሥርዓቱ እየፈራረሰ ነው፡፡ ሕዝብ ግን ችግር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በአማራና በትግራይ ክልሎች ግፊት ይታያል፡፡ አንዳንዴ በአማራ ክልል አካባቢ ምግብ ወደ ትግራይ እንዳይሄድ መኪና አስቁመው ሲዘርፉ የሚታዩ አሉ፡፡ ሌሎችም ችግሮች ታይተዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ለማስቆም ምን ተሠርቷል? ሰዎች ትግራይም አማራም ለምን እንደሆነ በቅጡ ያወቁ አይመስልም፡፡ ችግሩንና ድህነቱን የሚገነዘበው ጥቂት ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለ ሰው ትግራይ ኒውዮርክ ናት ብሎ ያስባል፡፡ መሪ ለመሪ በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው? 

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ችግሩ ሄዶ ሄዶ ከሕግ ጋር የሚያያዝበት መንገድ አለው፡፡ አንዳንዱ ትግራይን እንደ ኒውዮርክ ሊያያት ይችላል፡፡ ጥሩ ይሁን፡፡ ከዚያ አልፎ ግን ጉዳት እስከ ማድረስ መሄድ ሌላ ነገር ነው፡፡ እስኪያውቃት ድረስ እንደዚያ ብሎ ሊገምታት ይችላል፡፡ የተለያየ ምክንያትም ስላለው ሊሆን ቢችልም የሌለ ነገር እንዴት እንደዚህ እንደሚታይ ግን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ መንገድ ወደ መዝጋት መግባት ግን ያውም በሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ፀረ ሕዝብ ተግባር ከመሆኑም በላይ ከባድ ወንጀል ነው፡፡ በሕዝብ ላይ እንዴት እንደዚህ ያለ ተግባር ትፈጽማለህ? ይህ በግለሰብ ወይም በሆነ ቡድን ላይ የተቃጣ ሳይሆን፣ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል ነው፡፡ እኔ ዕብደት ነው የምለው፡፡ ጠላት የሚባል አካል ቢኖር እንኳ እሱ ላይ የማይደረግ ነገር ነው የተፈጸመው፡፡ ታጋይ በውጊያ ይሳተፋል፡፡ ጠላትን የምትፋለመው በውጊያ ነው እንጂ፣ ከበነው እህል ውኃ እንዳያገኝ በማድረግ እናሸንፈዋለን ማለት አዋጭ አይደለም፡፡ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ በፖለቲካ ነው የምትገለው፡፡ ጠላት የምትለውን አካል እንኳ በማስራብና እንዲጠማ በማድረግ ፖለቲካን መዋጋት አትችልም፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በሌላው ላይ ጠላት ሊሆን አይችልም፡፡ የተወሰኑ አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ጥቂት ሰዎች ወይም ቡድን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሕዝብ ግን ጠላት አይደለም፡፡ እኛ ወደ አማራ የሚሄደውን እናስቁም አላልንም፡፡ መልስ አልሰጠንም፡፡ ማስቆም ይቻላል፡፡ አንድም ነገር አላደረግንም፡፡ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ የሚል አመለካከት የለንም፡፡ ኅብረተሰቡም የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የለውም፡፡ የድርጅትም፣ የመንግሥትም ሐሳብ አይደለም፡፡ ሰው ግን ይገርመዋል፡፡ ምን እየተሠራ ነው ይላል፡፡ እኛ ለፌዴራልም ለክልልም መንገድ ሲዘጋ እያያችሁ እንዴት ዝም ትላላችሁ ብለናል፡፡ ትግራይ ክልል በር ስለሆነና አጠገባችን ስለሚገኝ መንገዱን ሄደን ማፍረስ እንችል ነበር፡፡ ግን ይህ በፖለቲካዊ መንገድ ነው መፈታት ያለበት፡፡ የአማራ ክልል መንግሥትም የፌዴራል መንግሥትም ባሉበት መንገድ እንዴት ይዘጋል ነው ጥያቄው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የሚያስተዳድረው መንገድ እንዴት ሲዘጋ ዝም ይባላል ብለናል፡፡ መንገድ የዘጉት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትም ችግር አለበት እንላለን፡፡ መንግሥት ስለፈቀደ ነው ድርጊቱ የተፈጸመው ባዮች ነን፡፡

መንግሥት በትግራይ ሕዝብና በክልሉ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ይህ ግን በጣም አደገኛና አብረህ እንዳትሠራ የሚያደርግ፣ እስከ መቼስ ተሸክሜ እኖራለሁ የሚያስብል ጉዳይ ነው፡፡ መኪና ማለፉ አለማለፉ ሳይሆን ዝምድናው እንደዚህ የሚያስፈርጅ ከሆነ፣ በሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ብያኔ የሚሰጥበት ከሆነ፣ በድርጊቱ የተሳተፉ ቡድኖች ብቻም ሳይሆኑ ሥርዓት ማስያዝ ያልቻለውም አካል ለእኛ ተጠያቂ ነው፡፡ እኛ እኮ ወጣቱ ወታደሩን አታልፍም ሲለው ገብተን እንከላከላለን፡፡ ሥርዓት እናሲዛለን፡፡ ልቀቁ እንላለን፡፡ አሳምነንና ኃይልም ተጠቅመን ወታደሩን እናሳልፋለን፡፡ መልፈስፈስ አለ፡፡ እኛ ግን ነገሩ ፍላጎትም አለበት ባዮች ነን፡፡ ይህ ሕዝብ በጫና ፀጥ እንዲል ይፈጋል፡፡ ድምፁ እንዳይሰማ ለማዳከምና ለማድቀቅ ይፈለጋል፡፡ ይህ ከክልልም ከፌዴራልም የተቃጣ የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ ግጭት እንዳይፈጠር ደም መፋሰስ እንዳይኖር እያሉ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ታዲያ ግን ሕዝብ ዋጋ እየከፈለ ይሙት እየተባለ ነው ወይ ማለት ነው? ትግራይ እንደፈለገ ይሁን ከሌላው ጋ ግን አንጋጭም የሚል አዝማሚያ ነው ያለው፡፡ ችግር በሚፈጥረው ክልል ውስጥ ያለው ሕዝብ ችግር የለበትም፡፡ እኛም ይኼንን እናውቃለን፡፡ መሪ ስላጣና መፍታት የሚገባው አካል ችግሩን መፍታት ስላልቻለ ነው ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት፡፡ በተወሰኑ አካላት ነው ችግሩ እየተነሳ ያለው፡፡ ፖለቲካዊ ብልሽት እንዳለ፣ ሕዝባችንን ለማሰቃየት እንደተፈለገ ነው የምንገነዘበው፡፡ አስተሳሰቡ እንደዚያ ነው፡፡ ሕዝባችን ግን አልተሰቃየም፡፡ ችግሩን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ ልማቱ ግን የበለጠ ይፋጠን ነበር፡፡ ከዚህ ተነስተን አገራዊ እንቅስቃሴውም መዳከሙን መመልከት እንችላለን፡፡ ክልል በሙሉ እየዘጋህ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ይኖራል? ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ ሕዝብን ሆን ተብሎ ለማስራብ ተሞክሯል፡፡ ምግብ መብላት ስለማይችል ግን አይደለም፡፡ ይህ አስተሳሰብና ተግባር ከዚህ በፊት የተደረገ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ድረስ ያለና የሚታይ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ትግራይን ስንጎበኝ የእርስዎና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፎቶዎች በየቦታው ተሰቅለው እናያለን፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ፎቶዎች ዓይታዩም፡፡  ጊዜው እንዴት ነው እያልን ሰዎችን ስናናግር መንግሥት ትግሬዎችን እያጠቃ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ እውነት እንዲህ ያለ ቅሬታ እርስዎ ከሚመሩት ሕዝብ ይሰማሉ? ሕዝቡ የሚጠቃ ይመስልዎታል?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ስለጠየቅኸኝ በጥያቄ ልመልስልህ አልችልም እንጂ፣ ፖለቲካው እንደዚያ ነው እየሆነ ያለው፡፡ መንገድ ላይ ያገኘኸውን ሰው ስላናገርክ አይደለም፡፡ በግላጭ እኮ ነው ትግሬ እንደዚህ አደረገን፣ እንዲያ አደረገን የሚባለው፡፡ በተለይም በአማራ ክልል ሚዲያና በፌዴራል ደረጃ የምትሰማው በትግራይ ላይ በግላጭ ያነጣጠረ ዘመቻ ሲያካሂዱ ታያለህ፡፡ በእነዚያ ሁሉ ዓመታት የተሠራው ሥራ በሙሉ እንዳልተሠራ ተደርጎ የጨለማ ዘመን ሲባል ትሰማለህ፡፡ ይህም የትግራይ አመራርን ጥላሸት ለመቀባት ነው፡፡ ሁሉም ሰው እነሱ ናቸው እንዲል ነው የተደረገው፡፡ በጨለማ ነው የነበርነው፣ ወደ ጨለማውም ያስገቡን ትግሬዎች ናቸው የሚል ጥቃት እየተካሄደ ነው፡፡ የትግራይ አመራሮች ባሉባቸው መሥሪያ ቤቶችም ውስጥ ተቋማዊ ጥቃት ተፈጽሟል እንላለን፡፡ ዕርምጃ ያልተወሰደበት የትግራይ አመራር የለም፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ ግን በፖለቲካዊ አቋሙ ሳይሆን የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ አመራሩ ከኃላፊነት እየተነሳ ነው፡፡ ወደ ከፋ አቅጣጫ እየሄደ ነው፡፡ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበረው ብቻም ሳይሆን ወረድ ስትልም ይህ ሲደረግ ታገኛለህ፡፡ ከፌደራሉ መንግሥት ጀምሮ ዘር ላይ ያነጣጠረ ፖለቲካ እየተሠራ ነው፡፡ እነ ጄነራል ክንፈ ዳኘው ሲያዙ የተላለፈውን ፊልም ታስታውሳለህ፡፡ አካኋኑ ትግራይን ለመንካት ነው፡፡ ጄነራሉ የትግራይ ሰው ስለሆኑ ሆን ተብሎ በዚያ መንገድ ማቅረብ ተፈለገ፡፡ ለአገር ሲሠራ የነበረ ሰው ነው፡፡ ካጠፋም ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ ትችላለህ፡፡ ባለፈው ስንል የነበረውና እናስተካክል ያልነው የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓታችን ይስተካከል ነው፡፡ ግን ዘመቻ ነው የተካሄደው፡፡ የትኛው ጦርነት ላይ የተማረከ ሰው ነው እንደዚህ ታስሮ እንዲቀርብ የሚደረገው? በነገራችን ላይ እኔ ነኝ እንዲያዝ የወሰንኩት፡፡ የሆነውን ሳይ ግን ምን ተፈጠረ እንድል ነው ያደረገኝ፡፡ እኛ ይዘን አስረከብናቸው እነሱ ግን በካቴና አስረው እንደዚያ ማሳየቱን ፈለጉ፡፡ ለምን ብዬ ጠይቄያለሁ፡፡ ቢያንገራግርና ሌላ ነገር ቢፈጥር ኖሮ እንደዚያ መያዙ ይሁን ትላለህ፡፡ ያለ ምንም ግርግር ይዘን ያስረከብናቸውን ሰው፣ የትግራይ ጄኔራል እንደዚህ ይዘናል ለማለት የተደረገ ነው፡፡ የሸፈተ ወታደርና የሸፈተ ጄኔራል ከካይሮ በአውሮፕላን በክብር ሲገባ ግን እናያለን፡፡ አገሩን ሲያገለግል የነበረውን ግን እንደዚህ አድርገህ በመሳለቅ ዘር ላይ ያነጣጠረ አካሄድ መከተል ተጀመረ፡፡ ትኩረቱ ትግራይ ላይ ነው የሚለው ግልጽ ነው፡፡

በእስር ቤት ምርመራ ተደረገ የሚለው ስሞታ መርማሪዎቹ በሙሉ ትግርኛ ተናጋሪ ናቸው እየተባለ ሲነሳ ነበር፡፡ ይህ ግን ፍፁም ውሸት ነው፡፡ ሁሉም መርማሪ ትግርኛ ተናጋሪ አይደለም፡፡ እውነታውን እኛ እናወቀዋለን፡፡ ግን ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ ሰው ሁሉ እነዚህ ናቸው እንዴ ይኼንን ሁሉ የሠሩት እያለ ትግራይ ላይ እንዲያነጣጥር የተከፈተ ዘመቻ ነው፡፡ በይፋ የተከፈተ ጥቃት ነው፡፡ ከራሳችን መንግሥት ብቻም ሳይሆን፣ ከራሳችን የማንጠብቀው ኦፊሴላዊ ጥቃት ተከፍቶብናል፡፡ የዕብደት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ትግራይ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አሁን ጭራሽ በየቢሮው በመሄድ በብቃታቸው ሳይሆን፣ የትግራይ ሰዎች በመሆናቸው ብቻ እየተነሱ ነው፡፡ በአቅምና በአፈጻጸም ችግርማ እኛም እናነሳ ነበር፡፡ ብቃት የሌለው መነሳት አለበት፡፡ ግን በይፋ የታወጀ ጥቃት ነው፡፡ አንድ ቦታ ኮሽ ባለ ቁጥር የትግራይ እጅ አለበት፣ ወያኔ አለበት ነው የሚባለው፡፡ ቤኒሻንጉል በለው፣ ሶማሌ ክልል በለው ችግር ሲፈጠር ትግራይ ይወቀሳል፡፡ ሦስተኛ ወገን ግን አለ፡፡ አንዳንዴ በግላጭም ጭምር እኛን ለማጣላት የሚፈልግ ሦስተኛ ወገን አለ፡፡ እሱም ትግራይ ነው፣ ወያኔ ነው እየተባለ ነው፡፡ በአገር ደረጃ የዕብደት ሥራ ነው የምንለው ይኼንን ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ፣ ከአማራ ክልልም ተነጋግረንበታል፡፡ በአማራ ክልል አስመላሽ ኮሚቴ ተብለው ስለወልቃይት፣ ስለራያ ያነሱልሃል፡፡ ትግራይን ለማጥቃት እንጂ ጥያቄው የእነሱ ሆኖ አይደለም፡፡ ማዶ ቆሞ አንተ አማራ ነህ ሊልህ አይችልም፡፡ በውክልና የሚደረግ ጦርነት ነው ያለው፡፡ የማንም ሽፍታ እየታጠቀ በትግራይ ላይ ሲፎክር ነበር፡፡ ለዚህ ነው የአደባባይ ዘመቻ በትግራይ ላይ እየተካሄደ ነው የምንለው፡፡ ግን ከልክ አለፈ፡፡ ምላሽ አልሰጠንም፡፡ እነሱ እንዳበዱት ማበድ አንችልም፣ እንረጋጋ ብለናል፡፡ ኃፊነት አለብን፡፡ የትግራይ ብቻም ሳይሆን በሌላውም ላይ ኃላፊነት ስላለብን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፡፡ የእኛ ሥራ ማቀጣጠል አይደለም፡፡ ወደ መቀሌ ጠባቂ ሳይቀር ተልኳል እኮ፡፡ ፌዴራል ወደ ክልል ታጣቂ ልኳል፡፡ በበላይነት ሰላም እንዲሰፍን ኃላፊነት የወሰደው አካል ሲያበላሽ እኛ ነን ያስተካከልነው፡፡ ለማይፈለግ ጥቃት የተላከውን ከበን በመጨረሻው እንዲመለስ አድርገናል፡፡ ሰው ለማገዳደል ነው፡፡ ተኩስ ቢጀመር እዚህ ያለው ሰው ዝም እንደማይል ይታወቃል፡፡ እዚህ ራሱ መዓት ወታደር ነው ያለው፡፡ በተለያየ አካባቢ የምናየውን ብጥብጥ እዚህም በመንግሥት ለማስጀመር ተሞክሮ ነበር፡፡ እስከዚህ ድረስ ያለ ሕግ ጥቃት ለመፈጸም ተሞክሯል፡፡ በሕግ አግባብ ፀጥታ ካልደፈረሰ ወይም አገር ካልፈረሰ በቀር ዝም ብለህ ሰላም ባለበት አካባቢ ወታደር አትልክም፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ትግራይ ትግራይ ማለት ይቁም በዛ እያለ ነው፡፡ የራሳችንን ሥራ እንሥራ፣ መልካም አስተዳደር አጥተናል፣ ለልጆቻችን የሥራ ዕድል የለም፣ ሰላም አጥተናል እያለ ነው፡፡ በቃን እያለ ነው፡፡ በአደባባይ እየተሳ ሌላም አካባቢ እንደ አማራ ሁሉ በቃን ማለት ጀምሯል፡፡ ችግር ቢኖር ትነጋገራለህ፡፡ በግምገማ ታያለህ፡፡ እኛ ጋ የተለየ ችግር ግን የለም፡፡ ሁሉም ጋ ያለው ችግር ነው ያለው፡፡ ይህም ቢሆን በክልል ደረጃ ነው የሚጠየቀው፡፡ በአገር ደረጃና በኢሕአዴግ ደረጃ ችግር ካለ እንነጋገራለን፡፡ የተደረገውም ይኸው ነው፡፡ ከዚህ የተለየና እዚህ ድረስ የሚያስመጣ ችግር ኖሮ ሳይሆን፣ በድብቅ የሚሠራ ተንኮል ስላለ ነው ያሰኛል፡፡ አሁን ላይ ሰው በጥቂቱ ቀዝቀዝ የማለትና የመሰልቸት አዝማሚያ ከማሰየቱ በቀር፣ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ ከፍተኛ ቅስቀሳና ዘመቻ ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሆን ተብሎ እየለዩ ማሰርም በትግራይ ላይ የሚደረግ ነው፡፡ በአንድ ተቋም አምስት የግዥ አባላት ቢኖሩና ሁለቱ ትግራይ ቢሆኑ እነሱ ይታሰራሉ፡፡ ሌሎቹ ይተዋሉ፡፡ ጉድ እኮ ነው ያለው፡፡ የምናወጣው ጉድ አለ፡፡ መጠየቅ ያለባቸው ሁሉም ናቸው፡፡ ግን ደማቅ ፊርማ ያለው ወይም ቀለል ያለና ፈዛዛ ፊርማ ያለው የሚባል ነገር የለም፡፡ እስር ቤት ያለውን ብታይ የሚገርም ታሪክ ነው፡፡ እንደ ኮሚቴ ሲሠሩ የነበሩ ግን በትግሬነታቸው እየተለዩ ታስረዋል፡፡ ልትገምተው የማትችለው መውረድ፣ የእኛ መንግሥት ነው ልትለው በማትችልበት ደረጃ እየሄደ ነው፡፡ አደገኛ ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አዝማሚያው አገር እንዲበተን እያደረገ ነው፡፡ ትግራይ ወይም ሌላም ብሔር በመሆኑ ሳይሆን፣ መጠየቅ ካለበት ማንም ቢሆን ይታሰር፡፡ እኛም ይኼንን ነበር የምንከተለው፡፡ በፊርማው ነጥለህ ማሰር ግን ከዚህ በላይ ዘረኛነት ምን አለ? ነገሩን ሁሉ ሰው ላያውቀው ይችላል ግን ዘረኝነት በዝቷል፡፡

አሁንም ገና ሽግግር ላይ ስለሆንን ሊስተካከል ይችል ይሆናል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ግን የግለሰቦች እንጣጥ ማለት ሳይሆን መንግሥታዊ ይዘት ያለው አካሄድ መሆኑ ነው አስጊው ነገር፡፡ ለምሳሌ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ትግራይ በመሠረተ ልማት የተለየ ተጠቃሚ ነች እያለ  የመንግሥት አመራሮች ባሉበት መድረክ ላይ ሲነገር የምትሰማው ተጨማሪ ዕብደት ነው፡፡ የሌለ መንገድ ሥራ እንዳለ ያለውንም በሌለ አኳኋን በማስገመት የሚነገር ነው፡፡ ቅድም ትግራይ ኒውዮርክ ነች እንዳልከው ዓይነት የሌለውን እንዳለ አድርጎ የማስቀመጥ ነው፡፡ ትግራይ በአብዛኛው ከተማነት የተስፋፋበት ክልል ነው፡፡ ወደ ደሴ፣ ወደ ጎንደር የሚሄደው ዋናው መንገድ የጣሊያን ጊዜ መንገድ ነው፡፡ ጥንትም የነበረ መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ ነው የተስፋፋውና የተሻሻለው፡፡ ይህ በመደረጉ ትግራይ በተለየ ጠቃሚ ናት ልትል አትችልም፡፡ ቅድም እንዳየነው አምስት ሰዎች ፈርመው ሁለቱ እንደታሰሩት ሁሉ፣ በዚህ የመሠረተ ልማት መመዘኛም ሁሉም በእኩል መታየት ሲገባቸው፣ ይኼንን ትተው ወረዳ ቆጥረው ወረዳው ብዙ አስፋልት አለው የሚል ክርክር አመጡ፡፡ ወረዳው ከተማ ቢሆንስ? ከዚህ ባሻገር አብዛኞቹን ወረዳዎች ለአስተዳደራዊ ምቹነት ስንል መስመር ላይ ነው ያደረግናቸው፡፡ ይህ ግን ትግራይ ተጠቃሚ ነች ማሰኘት አልነበረበትም፡፡ ይልቁንም ጥቃት ነው የምንለው ጉዳይ የባሰ ወደ በጀትም እየመጣ እንደሆነ እያሳየን ነው፡፡ በበጀት ለመጉዳት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ማለት ነው፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ እንዲህ እያደረገ የሚመራ አመራር ካለ አገር ለመበተን የሚሠራ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ መንግሥት ጋር ምን ብለህ አብረህ ትሠራለህ? በሥነ ሥርዓት ካልመራ እንዴት ብዬ አብሬው መሆን እችላለሁ? ልሆን አልችልም፡፡ ትደጋገፋለህ እንጂ ሊጎዳህ ብሎ የሚሠራ ከሆነ ማንም አብሮት ሊሠራ አይችልም፡፡ ፖለቲካዊ ጨዋታው ያሳዝናል፡፡ ትግራይ ላይ በፕሮፓጋንዳ ብቻም ሳይሆን በተጠና ዘዴ ነው ዘመቻው የሚደረገው፡፡ በበጀትም ጭምር ለመጉዳት እየተሞከረ ነው፡፡ መንገድ አያስፈልጋችሁም፣ እላፊ አላችሁ፣ ሌሎች ክልሎች ገና ናቸው የሚል የሌለ መመዘኛ እየተሰማ ነው፡፡ መንገድ አካላዊ ነው፡፡ መለኪያው ሌላ መሆን አለበት እንጂ የወረዳ አስተዳደር መሆን የለበትም፡፡ ስላነሳኸው እንጂ በትግራይ ላይ ሲበዛ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፡፡ ይህ ከቀጠለ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ትግራይ ከዚህ በኋላ ምን ቀረኝ ብሎ ከዚህ ሥርዓት ጋር አብሮ ይሠራል? አንድነትህን ማጠናከር ሲገባህ ራስህ እየበተንከው ነው ማለት ነው፡፡ አንድነት የሚባለው በቃል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አንድነት በምትሠራው ሥራ፣ በአያያዝህ አመዛዝነህ አንድነትን የሚያጠናክር ነገር ነው መሥራት ያለብህ፡፡ በትግራይ ላይ የሚሠራው ሥራ ግን አንድነትን የሚበትን ነው፡፡ ገዥው አስተሳሰብም ይኼው እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት የመገንጠል ስሜት አለ ማለት ነው?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- አዎ፡፡ የእንገንጠል ስሜት አለ፡፡ እኛ እንዴት መገንጠል መፍትሔ ይሆናል? አብረን ነው መሥራትም መልፋትም ያለብን፣ አብረን ማስተካከል ያለብንን እናስተካክል እያልን እያረጋጋን ነን፡፡ አሁን ግን ይህንን የሚገፋፋው ሌላው ነው፡፡ እኛ አብረን እናርመው ሊስተካከል ይችላል እያልን ነው፡፡ ሰው ግን በጣም አንገሽግሾታል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ለምን ለስብሰባ ትሄዳለህ እየተባልኩ ነው፡፡ ምን ልታደርግ ትሄዳለህ? ሰዎቹ ትግራይን አያከብሩም፡፡ ፋይዳ ለሌለው ስብሰባ ባትሄድ ይሻላል የሚል ገዥ አስተሳሰብ እየበዛ ነው፡፡ ሰው እስከዚህ ድረስ ደምድሟል፡፡ ስሜታዊ ሆኖ አይደለም፡፡ ሁሉ ነገር ተደማምሮበት ነው፡፡ ይህ አደገኛ ነገር ነው፡፡ እኛ እንደ መሪ ስህተት ነው፣ እናስተካክለው እያልን ሐሳቡን እየገታን ነው፡፡ ግፊቱ ግን ሌላ ነው፡፡ እኛ ሕዝቡን ስለቀሰቀስነው አይደለም፡፡ ራሳቸው በራሳቸው ነው ሕዝቡንም ምሁሩንም እንዲህ ያነሳሱትና እንዲደመደም ያደረጉት፡፡ ሕዝቡ የእኛ መንግሥት አይደለም እያለ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሲመጡ የነበረውን ስሜት ታስታውስ እንደሆነ የተለየ ነበር፡፡ ሰው ሁሉ ነበር የተቀባላቸው፡፡ ከጫፍ ጫፍ በፕሮፓጋንዳ ልትቀይረው አትችልም፡፡ ታዝቦ፣ የሚሆነውንና እየሆነ ያለው ሲደማመርበትና ሲበዛበት በፊት የነበረውን ስሜት ወደ ባዶነት ከተተው፡፡ ይኼ እኛ የሠራነው አይደለም፡፡ ራሳቸው በራሳቸው ላይ ያደረጉት ነው፡፡ በዙሪያችን በተለይ ከአማራ ክልል በጦር እንወጋችኋለን የሚል ፉከራ ነበር እኮ፡፡ ሕዝብ ምን አደረገ? ይህ ሥርዓት እንዲመጣ መስዋዕትነት ስለከፈልን፣ ክልሉ የተለየ ነው ብሎ የሌለውን እንዳለው ማየት በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ትግራይ ኒውዮርክ መሆኗን እንዴት እናረጋግጥ ይባላል እንዴ? ያልሆነችውን፡፡ ለምሳሌ በወረዳ የተሠራ የፌዴራል መንገድ የለም፡፡ ወረዳ ለአስተዳደር እንዲመች የሚዋቀር አደረጃጀት ነው፡፡ ዛሬ ያስቀመጥከው ወረዳ ነገ ላይኖር ይችላል፡፡ መሬት ግን ግዑዝና የሚታይ ነገር ነው፡፡ በፊት በትግራይ ክልል 81 ወረዳዎች ነበሩ፡፡ አሁን ላይ ተጨፍልቀው ወደ 36 ዝቅ ተደርገዋል፡፡ ከግማሽ በታች ወርደዋል፡፡ ይህ በሆነበት እንዴት ነው ወረዳው ሁሉ በመንገድ ተገናኝቷል የምትለው፡፡ ነገ ሲያስፈልግ 50 ወይም 70 ላደርገው እችላለሁ፡፡ ቁጥርን በወረዳ አደረጃጀት በኩል ልትቀይረው አትችልም፡፡ እኔ ምን ዓይነት ሞኞች ናቸው እላለሁ፡፡ ሰው እንዴት እስከዚህ ድረስ ወርዶ ሞኝ ይሆናል? በዚህ ከቀጠሉ ከእነሱ ጋር አብሮ መሥራት አይቻልም፡፡ የሚያጠቃህ አጋርህ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደዚህ ከቀጠለ ሕዝቡ ብቻም ሳይሆን እኔም አልቀበለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለጄኔራል ክንፈ ዳኘው አንስተው ነበር፡፡ ሕዝቡ የመጠቃት ስሜት ስላደረበት እስከ መገንጠል ድረስ እንደሚያስብ ገልጸዋል፡፡ ሥርዓቱም ጥቃት እየፈጸመብን ነው የሚለውንም አንስተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሞክረን ሥርዓቱ ስለከሸፈና እምነቱም ስለሌን ነው ከሚል መነሻ ነው? ወይስ የቀረበውን ክስ ውድቅ ከማድረግ ወይም ሐሰት ነው ከማለት አኳያ ነው አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ መስጠትን የማትቀበሉት?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ወደ ተያዘው ጉዳይ ባልገባም የራሴ አቋም አለኝ፡፡ የተደረደረው በሙሉ የውሸትና የፈጠራ ነው፡፡ ለአገሩ የሠራ ሰው አገሩን በማገልገሉ ምክንያት ተከሳሽ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢንተለጀንስ ሥራ እኔም ቀደም ሲል ሠርቻለሁ፡፡ ልጆቹ የታሰሩት እኮ አገር እየወጉ የነበሩትን ኃይሎች ሰልላችኋል ተብለው ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አገር የምትጠበቀው? አገርን የሚጎዳ ኃይል ሲኖር የመረጃ ሰው ትልክበታለህ፡፡ ኢንተለጀንስ ማለት እኮ ይህ ነው፡፡ ይህን ስለሠሩ ነው የተከሰሱት፡፡ እኔ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ያሳፍረኛልም፡፡ መንግሥት እንደዚህ ማድረግ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንተ የግንቦት ሰባት አባት ብትሆን እኔ ልገለብጥህ እችላለሁ፡፡ ማለትም ለመንግሥት እንድትሠራ አደርግሃለሁ ማለት ነው፡፡ ገንዘብም ሆነ ሌላም ነገር ሰጥቼህ እዚያው ባለህበት ሆነህ ለመንግሥት እንድትሠራ ላደርግህ እችላለሁ፡፡ ይህን ማድረግ የኢንተለጀንስ ተግባር ነው፡፡ ኢንተለጀንስ እንደ መበደኛ ሥራ አይደለም፡፡ ግን ይህንን አድርገሃል ተብለው የታሰሩ አሉ፡፡ ዕውር ድንብሩ የጠፋባቸው ሰዎች እየከሰሷቸው ነው፡፡ ይህ የኢንተለጀንስ ሥራ እንደሆነ የማውቀው ስለሆነ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ የኢንተለጀንስ ሥራ የዴሞክራሲ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለየት ያለ አገርን የመጠበቅና የመከላከል ተግባር የተሰጠው እንጂ፣ እንደ መደበኛ የሲቪል ሥራ እምነት ክህደት እያልክ ፍርድ ቤት የምታቀርበው አይደለም፡፡ የኢንተለጀንስ ሥራ የሚሠራ ሰው እንዲያውም ጥበቃ ሊደረግለት ነበር የሚገባው፡፡ አገር በማገልገላቸው የተያዙት ልጆች ያሳዝኑኛል፡፡ የእኔ አቋም እንዲለቀቁ ነው፡፡ እንዴት አገር በማገልገላቸው ይጠቃሉ?

የወረረና አገር የወጋ እንደፈለገ እየፈነጨ፣ በተገላቢጦሹ የሰከረ አስተሳሰብ በማራመድ ለአገር የለፉትን ማሰርና ማንገላታት ግን ሌላ ነው፡፡ ፍጥጫ ከሆነ የሚፈለገው ይለይልንና ወደዚያ እንግባ፡፡ መከበር ነው ያለባቸው፡፡ የየትኛውም ብሔር ተወላጅ ይሁኑ አገርና ሕዝብ ያገለገሉ ሰዎች መለቀቅ አለባቸው፡፡ አቋም ከቀየርክ አቋምህን በቀየርክበት ጊዜ ያንን ትዘጋለህ፡፡ ግንቦት ሰባት ወዳጄ ነው ካልክ የኢንተሊጀንስ ሥራው ይቀራል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ ለምን የመንግሥት አቋም ስለነበር፡፡ ሠርተሃል፣ አስመራ ልከሃል እየተባሉ ሲከሰሱ ነው የምሰማው፡፡ ጉድ የሚያስብል ነው፡፡ ሩሲያዊ ሆኖ አሜሪካ በመግባት የኢንተሊጀንስ ሥራ ይሠራል፡፡ ይገለብጣል፡፡ ይህንን በማድረጉ የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ቢከስ ግን በዓለም ላይ የሌለ ታሪክ ነው፡፡ እኛ የሚገርምና የሚያሳዝን ነገር እያደረግን ነው፡፡ ይህች አገር በዚህ አካሄድ አገር ልትሆን አትችልም፡፡ አፌን ነው የያዝኩት፡፡ እንደ ወንጀል ተደርጎ የተመሠረተው ክስ ስህተት ነው፡፡ ይህንን ስናገር ግን የማምንበት ነገር እኔም፣ አንተም፣ ማናችንም በግላችን ያጠፋነው ጥፋት ካለ መጠየቅ አለብን ብዬ ነው፡፡ ማንም በግል ያጠፋው ነገር ላይ መጠየቅ አለበት፡፡ በጅምላ ማሰር ግን በጣም ነው የሚያንገበግበኝ፡፡ ስለዚህ እኔ የማወራው ስለአቶ ጌታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሥራው አግባብ የታሰረው ሰው ሁሉ ይፈታ ነው የምለው፡፡ የመንግሥት ሥራ በመሥራቱ እየተጠቃ ነው፡፡

የሥርዓት ውድቀትን በማንኛውም ሁኔታ መቀበል የለብንም፡፡ በጭራሽ፡፡ በግሉ ያጠፋው ጉዳይ ካለ ግን ጌታቸውንም ሆነ ሌላውንም ሰው አንጠልጥሉት ብያለሁ፡፡ ግን በአግባቡ መለየት አለበት፡፡ የትግራይ ሰው በመሆኑ እንጂ የኢንተሊጀንስ ሥራ በመሥራቱ ስላጠፋ አይደለም አቶ ጌታቸውም ሌላውም የተጠየቀው፡፡ ለምን ብትለኝ የኢንተሊጀንስ ሥራ የሚሠራው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱን ጉዳይ ሳይወስን ጌታቸውም ሆነ ሌላው አካል የኢንተለጀንስ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ለትንንሹ ነገር ሳይቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ መረጃ መሰብሰብን ጨምሮ ሌላውንም ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳታማክር መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ እንደ ሥርዓት ካየነው የኢንተለጀንስ ሥራ የሚያስጠይቅ ከሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው መጀመር ያለበት፡፡ ኢንተለጀንስ ሥራው ላይ ጌታቸውን ብቻ ልታስረው አትችልም፡፡ ስትቆርጠው ግን ፖለቲካዊ ይሆንና ማሰር የምትፈልገው ሰው እንዳለ ያስታውቅብሃል ማለት ነው፡፡ ኢንተለጀንስ ይለያል፡፡ ግንኙነቱም ዕለታዊ ነው፡፡ ልክ እንደ መከላከያ ነው፡፡ ከሌሎች ሥራዎችም የተለየ ነው፡፡ በየቀኑ ሪፖርት ማድረግ ይገባል፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ለአገር አሳሳቢ የሆኑ መረጃዎችም ስለሚኖሩ ግድ ነው፡፡ በየዕለቱ የሚደረግ ነው፡፡ እኔ ስሠራበት ስለነበር በተጨባጭ አውቀዋለሁ፡፡ እኔ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር በነበርኩ ጊዜ ኢንተለጀንሱም ስላለኝ ብዙ መሥራት እችል ነበር፡፡ በጭራሽ ግን አይደረግም፡፡ አልችልም፡፡ ጣጣዎችና የሚነካኩ ነገሮች ስላሉት አልችልም፡፡ በአካልም በሪፖርትም በየዕለቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ትገናኛለህ፡፡ ስለዚህ የደኅንነት ኃላፊውን ልያዘው ካልክ ደምረህ ያዘው፡፡ ሙሉ ይሁን፡፡ ይህንን ስል ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይታሰር የሚል አመለካከት ኖሮኝ አይደለም፡፡ አገሩን ነው ያገለገለው፡፡ ያጠፋው ነገር ካለ ግን መያዝ አለበት፡፡

ሰው ያላግባብ ታስሯል፣ ተገርፏል እየተባለም ክስ ይቀርባል፡፡ የሚታሰረው ግን ፌዴራልም ጭምር መሆን ነበረበረት፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎችም መታሰር አለባቸው፡፡ ሰው ለይቶ ማሰር ግን አያስኬድም፡፡ እንደ ሥርዓት አገር ላይ ጥፋት ተፈጽሟል ካልክ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ኃላፊዎቹ ድረስ እንዲሁም የምርመራ ኃላፊዎቹም ድረስ መሄድ አለበት፡፡ እጁ ያለበት ሁሉ ይግባ፡፡ ነጥለህ ስታመጣው ግን ፖለቲካዊ ውሳኔ ይሆናል፡፡ የፍትሕ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ግን በዚያ ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ተጠያቂ ይደረጉ ነበር፡፡ በግልጽ የምነገርህ ጥያቄው ፍትሕ ቢሆን ኖሮ እሱም [አቶ ጌታቸውም] ይያዛል፡፡ ግን ፖለቲካ ነው፡፡ እኛ እንደ አካሄድ የመረጥነው መጀመርያ ፖለቲካውን ማስተካከል እንደሚገባ ነው፡፡ ፖለቲካው ይጥራ፡፡ ደመናው ይግፈፍ፡፡ ከዚያ በኋላ የፍትሕ ጉዳይ ይሆንና ሁሉም ይጠየቃል፡፡ ጌታቸው ብቻም አይደለም፡፡ ሁሉም ይጠየቃል፡፡ በተለይ ከጄኔራል ክንፈ በኋላ ነገሩ ሌላ ሆኗል፡፡ እሱም ላይ ጥርጣሬ ነበረን፡፡ ግን መንግሥት ማስረጃ አለኝ ስላለ እንሂድበት ብለን ነው፡፡ ሄድን፡፡ የሆነው ሆነ፡፡ በሚዲያ መፍረድ ተጀመረ፡፡ የፍትሕ ጥያቄ እንዳልሆነ አሳየ፡፡ ይህንን ያመጡትና የበከሉት ራሳቸው ናቸው፡፡ ሁሉም እንደ ተሳትፎው መጠየቅ ካለበት የአንድ ብሔር ብቻ አይደለም ሁሉም ይግባ፡፡ ግን ሌላውን ጥግ አስቀምጠህና ነጥለህ የምትወስደው ዕርምጃ በእውነት በጣም የተባለሸና የሚያሳዝን አካሄድ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ትግራይን ስዞር የታዘብኩት ነገር ብዙ የተቀየረ ነገር የለም፡፡ በፊት የነበሩ ነገሮች ቅርሶችና ሌሎችም ታሪካዊ ሥፍራዎች ላይ ብዙም የሚያስደስቱ ነገሮች አይታዩም፡፡ እርስዎም አቶ መለስም የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ዓይቻቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም እርስዎ የተማሩበት ይሻላል እንጂ ብዙዎቹ ያን ያህል ናቸው፡፡ እናንተ በ27 ዓመታት የትግራይን ሕዝብ ለመርዳትና ከድህነት ለማውጣት ያመለጣችሁ ዕድል ነበር ሊባል ይችላል? ከድህነቱ ለማውጣትና ፈቅ እንዲል ለማድረግ ጥረት አድርገናል ትላላችሁ?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ጉዞው እንደ ጉዞው ከነበረበት አንፃር ስታየው ውድቀት ልትለው አትችልም፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ወደ 22 ሚሊዮን ሕዝብ ነው በድህነት ውስጥ ያለው፡፡ በትግራይ ሲታይ ወደ 29 በመቶ ነው፡፡ እኛ አገር ማስተዳደር በጀመርንበት ጊዜ እስከ 60 በመቶ ነበር በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረው የሕዝብ ቁጥር፡፡ የሕዝቡን ብዛት በዚያን ወቅት ስታየው አሁን ካለው አኳያ አነስተኛ ነበር፡፡ ትልቁ መለኪያችን ከድህነት መውጣት ሲሆን፣ የነበረው ጉዞ እንደ ውድቀት የሚታይ አይደለም፡፡ በጣም ፈጣንና ትልቅ ጉዞ ነው የታየው፡፡ በትምህርት ደረጃም በጣም አስገራሚ ለውጥ ነበር የታየው፡፡ በሁሉም መለኪያዎች ወደፊት የተራመደ ጉዞ ነው የተደረገው፡፡ ሆኖም ከዚህም በላይ መጓዝና ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር የሚለው ላይ ትክክል ነው፡፡ የስኬት ታሪክን የበለጠ ስኬታማ ማድረግም ይቻል ነበር ነው ግምገማው፡፡ እንዲያውም አንተ የሁለተኛ ትምህርት ቤቶችን አንስተሃል፡፡ እሱ ብዙም አይለደም፡፡ ከእሱ የሚበልጡ ትልልቅ ብዙ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ አንተ ያየኸው አንድ ያልተቀየረችውን ሊሆን ይችላል፡፡ ያልነበሩ በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች እኮ ተሠርተዋል፡፡ ስለዚህ አንተ ያየኸው ትክክለኛውን ሥዕል ሊያሳይህ አይችልም፡፡ በየቀበሌውና በየደጃፉ ትምህርት ቤት አለ፡፡ አሁን ከ30 በመቶ በላይ ተማሪ አሉ፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ግን ከዚህም በላይ መሆን ነበረበት፡፡ ድህነቱ ከተቀነሰውም በታች መቀነስ ነበረበት ነው የምንለው፡፡ ትራንስፎርሜሽን በአገር ደረጃ ብቻም ሳይሆን እዚህም መጀመር ነበረብን፡፡ ግብርናውም ቱሪዝሙም እስካሁን ካሳየው በላይ መሄድ ነበረበት፡፡ ትልቅና ቅድሚያ የሚሰጠው ግብርናና ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የተከተልነውም ራዕይ ትክክል ነው፡፡ በአገር ደረጃም ሆነ ከትግራይ ክልል አንፃር ሲታይ አቅጣጫው ትክክል ነበር፡፡ በመሆኑም ያጣነው ዕድል ልለው የምችለው መሄድ ከነበረብን አኳያ ባለመሄዳችን እንጂ ውድቀት ስለነበር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ሲጀመር ሁለቱ መሪዎች ታላቅና ታናሽ እስኪመስሉ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ታይቷል፡፡ አሁንም ደግሞ ከአስመራ ወደ ትግራይ ያነጣጠሩ ክሶች ይደመጣሉ፡፡ ድንበሩም ተዘግቷል፡፡ ነገሩ ወዴት እየሄደ ነው? በእናንተ አስተያየት ትሩፋቱ ጥሩ ነው? ወይስ ያልተፈቱ ጉዳዮችስ አሉ?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ምንም እንኳ የትግራይ ጉዳይ አንዱ ቢሆንም፣ ከትግራይ አንፃር ብቻ ግንኙነቱን ማየት የለብንም፡፡ እንደ አገር ነው መታየት ያለበት፡፡ አጀማመሩ ጥሩ ነው፡፡ ሰላም መስፈኑ፣ የተዘጋጋው ነገር መከፈቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ውሳኔውን ያነሳሳው ሕወሓት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በነበሩበት ጊዜ ነው ይህ ነገር እስከ መቼ ነው እንዲህ ሆኖ የሚኖረው? እንደ ኢሕአዴግም አጀንዳ ብለን ያቀረብነው፡፡ እንደ ኢሕአዴግ የተረሳውን አጀንዳ እናንሳው ብለን ነው ያቀረብነው፡፡ እኛ ራሳችን ነን ይበቃል፡፡ በአመራሩና በፖለቲካው የተለያየ አመለካከት ቢኖርም፣ ሰላሙን እንፈልጋለን ብለን አጀንዳውን አንስተን ብዙ ተሳትፎ አድርገንበታል፡፡ በመጨረሻም ውሳኔ ሲሰጥበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ተነስተው ወደ ኤርትራ ሄዱ፡፡ አዎንተዊ ዕርምጃ ወሰድን፡፡ ጥሩ ነገር ተፈጠረ፡፡ ከዚያ ግን ወደ ሥርዓት ሊቀየር አልቻለም፡፡ ማስጀመሩ ጥሩ ሆኖ ሥርዓት ካልተበጀለትና ተቋማት ካልተዋቀሩበት በመሪዎች ደረጃ ብቻ መሆኑ ብዙ አያስኬድም፡፡ አንተ ስትዋደድ ይኖራል ሳይሆን ሲቀር ግንኙነቱ ይጎዳል፡፡ ተነሳሽነቱን እንደግፋለን፡፡ ግን ወደ ሥርዓት መቀየሩ ላይ ነው ችግሩ ያለው፡፡ ተቋማቱ የሉም ሊባል ይችላል፡፡ ያሉትንም እንጠቀምባቸው፡፡ በግለሰብ በሁለትና በሦስት ሰዎች ከሆነ ግን ወደ ዘላቂ ለውጥ አይወስደንም፡፡ በርካታ ጉዳዮች አሉ መታየት ያለባቸው፡፡ ባለሙያ፣ የታሪክ ሰው ሌላም የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲሳተፉበት ማድረግ ይገባል፡፡ የአልጄርስ ስምምነት፣ የድንበር፣ የካሳ ጥያቄና ሌሎችም ጉዳዮች አሉ፡፡ የተጀመረው ወደ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች ማምራት ሲገባው ጭራሹኑ የተከፈተው ድንበርም ተዘጋ፡፡ ሥርዓት ከሌለ ምን ትጠብቃለህ? ሲፈለግ ይዘጋል ሳይፈለግም ያው ምን ትጠብቃለህ?

ለረዥም ጊዜ የተንጠለጠሉ ጉዳዮች ተፈትሸው ተግባራዊ የሚደረጉ ነገሮች ካሉ እንተገብራለን፡፡ የሚሻሻሉ ነገሮች ካሉም እንቀይራለን፡፡ ከዚህ ውጭ የትግራይና የኤርትራ ብቻ ሳይሆን፣ የመላው አገሪቱ ጉዳይ ነው፡፡ ስሜቶች ይኖራሉ፡፡ የአይደር ትምህርት ቤት ተደብድቧል፡፡ ውጊያ ከሆነ ውጊያ ነው፡፡ ሕፃናትን መጨፍጨፍ ግን ምን ትለዋለህ? ስለአገር ጉዳይ ነው የሚነሳው፡፡ በዚያ በኩልም ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እኛም ብዙ ማንሳት እችላለን፡፡ አሁን ግን የእሱ ጊዜ አይደለም፡፡ እንዝጋው፡፡ አገር ለአገር ያለውን ጉዳይ በአጀንዳ በሥርዓት እንነጋገርበት እናስጨርሰው ነው የምንለው፡፡ በስሜት የሚጀመር ነገር መቼም ማለቂያ የለውም፡፡ በሥነ ሥርዓት እንፍታው፡፡ ሰነዶች አሉ፡፡ የውጭ አካላት ሁሉ የተሳተፉበት ሒደት አለ፡፡ ሒደቱን ግልጽ እናድርገው፡፡ በድብቅ የምትሠራው ነገር አይደለም፡፡ ሳዑዲ ወይም ዱባይ ለብቻህ ሄደህ የምትሠራው አይደለም፡፡ አዲስ አበባም አስመራም ሆነህ በግልጽና በሚታይ መንገድ ተቋሞቻችንና ሌሎችም ገብተውበት ማከናወን ይቻላል፡፡ የውጭ አካላት እጃቸውን አስገብተው ውሳኔም ተሰጥቶበታል፡፡ አሁን ወደዚያ መግባት ሳይሆን፣ የተጀመረው መቀጠል ነው ያለበት፡፡ ድንበር መዘጋት የለበትም እንላለን፡፡ አጀማመሩ ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ኤምባሲ መከፈቱ ጥሩ ነው፡፡ ይከፈት እንላለን፡፡ ሕዝቡን ወደ ማቀራረቡ ማምጣት ይገባል፡፡ ስሜቱ ከረገበ በኋላ ግን በመሠረታዊና በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይጀመር ግን መሀል ላይ ተቋረጠ፡፡ ነገሩ በግልጽ ይሁን፡፡ ድብቅ አይሁን ነው የምንለው፡፡ በነበረው ጥሩ መነሳሳትና ተስፋ ቶሎ ብለን ወደ ሥርዓት ማስገባት ይቻል ነበር እላለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ ግን ዕድሉን አልተጠቀምንበትም ብዬ አስባለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአልጄርስ ስምምነት ሃያ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ይህንን ስምምነት በደፈናው እንቀበለዋለን መባሉ ስህተት ነበር? ለምሳሌ ኢሮብ ለሁለት ይከፈላል፡፡ ባድመ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ ይህን ያህል የቆየውን ስምምነት እንዲሁ እንቀበላለን ከመባሉ በፊት ተነጋግራችሁበታል?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- እኛ እኮ ያየነው ነገር የለም፡፡ ይህ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ባድመ ከተወሰደ የአገር መሬት ተወስዷል ማለት ነው፡፡ እንደ ክልል አይደለም የሚታየው፡፡ ከትግራይ በላይ ነው፡፡ እኛ ግን ወደዚያም አልገባንም፡፡ እንደ መንግሥት ድሮ እንደተስማማነውና እንደተቀመጠ ያለ ነው፡፡ ምንም ማለት የምንችልበት ነገር የለም፡፡ ወደ ድርድር ሲመጣ ስምምነቶቹን አንቀጽ በአንቀጽ ማየቱ ስለሚኖር ነው ተቋማት ይመሥረቱ የምንለው፡፡ በወቅቱ አስፈላጊ የነበረ በአሁኑ ሁኔታ ግን የማይጠቅም ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላ አያስፈልግም ሊባል የሚችል ነገር ይኖራል፡፡ እንደ አገር አሁን ሳይሆን በፊት ነው የአልጄርስ ስምምነትን የተቀበልነው፡፡ ግን እንዴት ይተገበራል የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ የስምምነት አንቀጾቹ ይታዩ፡፡ እኛም እነሱም ያንብቡትና የሚስተካከለው፣ የሚቀረው ይታይ፡፡ ወደ አፈጻጸም ሲገባ ሕዝብም ስላለ ከላይ ብቻ የምትጨርሰው ጉዳይ አይደለም፡፡ ወደ ጉዳዩ ስትገባ እንዴት እንፍታው የሚለው ይታያል፡፡ እንደ ውሳኔ እንደ መንግሥት ተቀባይነት ያገኘና የነበረ ነው፡፡ ውሳኔው ውሳኔ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን እንነጋገር፡፡ ውሎቹ ምን ይመስላሉ የሚለውን እንየው፡፡ ጥሩ መንፈስ ካለ እኔ ካላሸነፍኩ ብለህ ወደ ክርክር አትገባም፡፡ ለሁለታችን በሚጠቅም መንገድ ነው መወያየትና መስማማት ያለብን፡፡ ጉዳዩ የመሬት ሳይሆን የግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ መንገዱ ከሚዘጋ ይልቅ እሱ እየቀጠለ ወደ ውይይትና ወደ ንግግር መግባት ይገባ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በካናዳ የአንድ ግዛት ተወካይ በብቸኝነት ማሸነፉን ተከትሎ ሲናገር፣ ይህ አግባብ እንዳልሆነና እንደ ሥርዓት እየወድቅን ነው ብሎ ነበር፡፡ ይህን ያለው እሱ ቢያሸንፍም ተቃዋሚዎች ስላላሸነፉ ነው፡፡ በትግራይ ተቃዋሚዎች እየመጡ ነው፡፡ ነገር ግን ጫና እንዳለባቸውና ፖሊስ እንደሚያዋክባቸው ይናገራሉ፡፡ ስለተቃዋሚዎች እንቅስቃሴና የእነሱን ብሶት መስማትና ስለሥርዓት ጉዳይ ምን እየተደረገ ነው?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- ይህ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ አያያዛችን ላይ ችግር ነበረበት፡፡ ጫናዎች በዝተዋል ብለን ዓይተናል፡፡ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ሲታሰሩ ይህንን ጉዳይ አንስተን ተነጋግረንበታል፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲታገሉ የነበሩና የሚታይ እንቅስቃሴ የነበራቸውን እነዚህን ሰዎች ማሰር ይጎዳል ብለናል፡፡ ሊያሳስራቸው የሚችል ጉዳይ እዚህም እዚያም ሊገኝባቸው ይችላል፡፡ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ይጎዳል፡፡ ለፖለቲካው ምኅዳር ሲባል ቢለቀቁ ይሻሻል ተብሏል፡፡ ሐሳብም ተከታይም አላቸው፡፡ ፖለቲከኛ ስለሆነ እንደፈለገ ይሁን፣ ይግደል፣ ወንጀል ይፈጽም፣ ዝም እንበለው ማለትም አይደለም፡፡ ይሻሻል የሚል አቋም ይዘናል፡፡ እንደ ሥርዓት የሚሻሻል ጉዳይ ነው ብለን ወስነናል፡፡ ስብሰባ የሚከለከሉ፣ አባሎቻቸው የሚታሰሩባቸው ብለው እነሱ የሚያነሷቸው እኛም ያየናቸው እንዲስተካከሉ ተስማምተናል፡፡ ብዙ አልተኬደበትም እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ ውክልና እንዲኖራቸውም ተስማምተናል፡፡ ልክ እንደ አሜሪካና እስራኤል ከፍተኛውን ድምፅ ያገኘው መንግሥቱን ይይዝና ሌሎች ድምፅ ያገኙት ግን ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለናል፡፡ የምንከተለው ሕግ ከ51 በመቶ በላይ ያገኘ ስለሚል ነው እንጂ፣ 40 እና 30 በመቶ እያገኙ ውድቅ ይደረግባቸው ነበር፡፡ ውክልና አያገኙም ነበር፡፡ አብላጫውን ድምፅ ያገኘው እያለፈ ሌላው የሚወድቅበት በሥርዓት ተስተካክሎ እንዳገኘው ድምፅ የፓርላማ ወንበር የሚያገኝበት አሠራር ይዘረጋል፡፡ ይኼ የአገራችንን ሁኔታ ከእነ ጭራሹ ይቀይረዋል፡፡ አናሳ ድምፅ ያገኙ ሲገቡ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ የሕዝብ ድምፅ ተሰሚነት ያገኛል፡፡ ወደፊት ይህ እየታሰበ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደ መድረክ፣ እንደ ቅንጅት ያሉ ፓርቲዎች የሚያገኙት ድምፅ ይታወቃል፡፡ ግን ሥርዓቱ የማይፈቅድ ስለነበር ውድቅ ይደረግ ነበር፡፡ በትግራይ እስካሁን አረና ነው የቆየው፡፡ ከሌሎች አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች አኳያ ሲታይ ሲያገኝ የቆየውም ድምፅ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ሆኖ አዲሱ አሠራር ለሁሉም ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ ትግራይ ላይ የደከመም ቢሆን እንዲሁ ልንወረውረው አንችልም፡፡ ተጎዳን፣ ጥቃት ደረሰብን በሚሉት ላይም ወደፊት እንዳይደገም አብረን እንሠራለን፡፡ ትግራይ ላይ ሰው ሊያሠልፍ የሚችል ሐሳብ እስካላቸው ድረስ ትንሽ ነው፣ አናሳ ነው ብለን አንተውም፡፡ እንደ መንግሥት እንደደግፋቸዋለን ብዬ ተናግሬአለሁ፡፡ አሁን መውጣት የጀመሩ አሉ፡፡ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሐሳብ መገደብ የለብንም፡፡ የዴሞክራሲያዊነት አንዱ መገለጫው የተቃውሞ ድምፆችም መስተናገድ ሲችሉ ነው፡፡ ሐሳብ ይውጣ፡፡ የተሻለው ሐሳብ በድምፅ ሲያሸንፍ ዴሞክራሲ ይንሰራፋል፡፡ ይህ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ27 ዓመታት የእርስዎና የአጋሮችዎ ትኩረት በአብዛኛው ሥራና ቁም ነገር ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ አሁን አሁን እርስዎ ከሰዎች መገናኘት፣ በአደባባይ ዙፋን ላይ መቀመጥ፣ ካባ መልበስ፣ መስጂድ እየሄዱ ንግግር በማድረግና በመሰል ጉዳዮች ይታያሉ፡፡ የእርስዎ ደጋፊዎች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛፍ ስለተከሉ ወይም ከልጆች ጋር ፎቶ ስለተነሱ ለውጥ አያመጡም፣ ቁም ነገሩ ያለው መሥራቱ ላይ ነው ይላሉ፡፡ እርስዎ የሚያሳዩት ለውጥ ከየት የመጣ ነው?

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፡- እኔ እኮ እዚህ አልነበርኩም፡፡ ግን ደግሞ ሥራዬንም እየሠራሁ ከሕዝብ ጋርም በሚገባ እገናኛለሁ፡፡ ሥራዬ ከሁሉም ጋር ያገናኘኛል፡፡ ይህንን ለውጥ ልትለው አትችልም፡፡ እኔ ስህተት ብገባም መብት አለኝ፡፡ ሕዝቡ ግን አቀባበል እናደርጋለን አለ፡፡ የአክሱም አካባቢ የቆየ የአቀባበል ሥርዓት አለው፡፡ አባቶች መደረግ አለበት አሉ፡፡ መስጂድም በዓል ስለሆነ በጥሪም ጭምር ነው እንድትሳተፍ ተጠራሁ፡፡ አልባሳትን አቅርበው አለበሱኝ፡፡ ራያ ስሄድ የራያ ያለብሱኛል፡፡ ሌላውም ጋ ስሄድ እንደ ባህሉና አኗኗሩ አክብሮቱንና ግንኙነቱን እየገለጸ ነው፡፡ 

Dm eri tv subscribe

EmbassyMedia - Exclusive Interview with Samuel GhebreAdonai