Basic

(የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) የኤርትራ የግብርና ልዑክ ቡድን በአማራ ክልል የቆጋ መስኖ ፕሮጅክትን እየጎበኘ ነው

Posted by: Semere Asmelash

Date: Tuesday, 10 December 2019

የኤርትራ የግብርና ልዑክ ቡድን በአማራ ክልል የቆጋ መስኖ ፕሮጅክትን እየጎበኘ ነው

December 10, 2019

(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የመስኖ ውሃ ተቋማትን ገንብቶ ውሃን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ለጎረቤት አገራት ምሳሌ የሚሆኑ ተግበራትን በማከናወን ላይ መሆኗን የኤርትራ የግብርና ልዑክ ቡድን አባላት ገለፁ።
የልዑክ ቡድኑ አባላት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የቆጋ መስኖ ፕሮጀክትና የወተት አባይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን እየጎበኙ ነው።

የልዑክ ቡድኑ መሪ ኢንጂነር ገብረመስቀል ታደሰ እንዳሉት በኢትዮጵያ በመስኖ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተከናወነ ያለው ሥራ ለጎረቤት አገራት ልምድ የሚሆን ነው።

በመስኖ ልማት በኩል ኤርትራ ተመሳሳይ ሥራ እየሰራች ቢሆንም ውሃን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ክፍተት መኖሩንና ለእዚህም ከኢትዮጵያ ልምድ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

የልዑክ ቡድኑ የተሻለ ልምድ ከመቅሰም ባለፈ በመስኖ ለሚለሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የንግድ ትስስር ለመፍጠር ጭምር ወደኢትዮጵያ መምጣቱን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአነስተኛ መስኖ ተወካይ ዳይሬክተር ኢንጂነር ኃይሉ እንግዳየሁ በበኩላቸው በክልሉ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማት ቢችልም በአሁኑ ወቅት እየለማ ያለው 800 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

“በልምድ ልውውጡ ያለንን በጎ ተሞክሮ ከማካፈል ባለፈ የእነሱንም ልምድ እንጋራለን” ያሉት ኢንጂነር ኃይሉ፣ የልምድ ልውውጡ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በጎብኝቱ ላይ 12 የኤርትራ የግብርና ዘርፍ የልዑካን ቡድን አባላትና የአማራ ክልል የተለያዩ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ከቀትር በኋላና በቀጣይ ቀናት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ እንደሚጎበኝ ታውቋል።

ena.et

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events