Dehai News

Ethsat.com: በምስራቅ ሃረርጌ ከ20 ያላነሱ የልዩ ሃይል አባላት በደፈጣ ውጊያ መገደላቸው ታወቀ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Tuesday, 14 February 2017

በምስራቅ ሃረርጌ ከ20 ያላነሱ የልዩ ሃይል አባላት በደፈጣ ውጊያ መገደላቸው ታወቀ

Feb. 14, 2017

Watch this:

ESAT Daily News Amsterdam February 14,2017

የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአቶ አብዲ ሙሃመድ የሚመሩት የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት በጉርሱምና ቦምባሴ አካባቢ ያደረጉትን ወረራ ተከትሎ ፣ በደፈጣ ውጊያ ከ20 ያለነሱ የልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውን የደህንነት ምንጮች ገለጹ።
እርምጃውን የወሰዱት በአካባቢው የንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ሲሆኑ፣ 12 የጦር መሳሪያዎችን እና በአማካኝ እስከ 44 የሚደርሱ ካርታ ጥይቶች ተወስደዋል።
የሶማሊ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በ7 የኦሮምያ ከተሞች የክልሉን ባንዲራ በመስቀል ከተሞቹ የሶማሊ ክልል መሆናቸውን ለማሳየት ሙከራ ቢያደርጉም፣ በደንብ የታጠቁት የአካባቢው ነዋሪዎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ፣ ልዩ ሃይሉ ከአካባቢው እንዲወጣ ተገዷል። አካባቢውን ከሃረር የተነሳው የምስራቅ እዝ ወታደሮች የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ ዛሬ ወይም ነገ በ7 ከተሞች ላይ የሰአት እላፊ አዋጅ ይጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተወሰዱ የጦር መሳሪያዎችን ለማስመለስ በህዝቡ ላይ ወከባ ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ምንጮች ገልጸዋል።
የሶማሊ ክልልን ልዩ ሃይል እየመሩ ወደ ኦሮምያ ክልል ከገቡት አዛዦች መካከል አንደኛው በቅጽል ስሙ ደቂ ላባጎሌ የሚባለው የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የእህት ልጅ ሲሆን እሱና ሌላ አንድ የጦር አዛዥ ለሁለት ቀናት በተደረገው ውጊያ መገደላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በዚህ የተበሳጩት የሶማሊ ክልል መሪዎች በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን ይዘው አስረዋል። የህወሃት አገዛዝ በሶማሊ ክልልና በኦሮምያ ክልል ለተነሳው የድንበር ግጭት እጁ እንዳለበት የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በጽኑ ቢያምኑም ጥቃቱን ለማስቆም የሚያስችል አቅም ግን የላቸውም።
በሌላ በኩል የህወሃት አገዛዝ በሶማሊላንድና በሶማሊያ የነበረውን የቁጥጥር ሃይሉን ሙሉ በሙሉ እያጣ በመምጣት ላይ መሆኑን እነዚህ የደህንነት ምንጮች ይገልጻሉ። ሶማሊላንድ ወደቧን ለዱባይ ለማከራየት መወሰኑዋን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚደገፉትና ከኢትዮጵያ ተጽዕኖ ለመላቀቅ የሚፈልጉ የሶማሊላንድ የፓርላማ አባላት እርስ በርስ ተጋጭተዋል። ሶማሊላንድ የጦር መሳሪያ እንደልብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በማድረግ በተለይ በምስራቅ አገሪቱ ክፍል የሚታየው ግጭት እንዲባባስ ልታደርግ ትችላለች የሚል ስጋት በህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ዘንድ አለ።
የኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ተወካይ ሆነው የሚያገለግሉት የ14ኛ ክፍለጦሩ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል በርሄ ተስፋየ The National ለተባለ ጋዜጣ ኢትዮጵያ ሶማሊላነድ ወደቧን ለደባይ ለማከራየት መወሰኗን እንደምትደግፍ ገልጸዋል። ጄኔራሉ የተናገሩት ግን በተግባር ከሚታየው ጋር ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ። የሶማሊላንድ ባለስልጣናት በአዲስ አበባ ተገኝተው ውይይት ማድረጋቸው፣ በሁለቱ የደህንነት ባለስልጣናት መካከል የነበረው የመረጃ ልውውጥ መቀነሱ፣ ያለ ኢትዮጵያ እውቅና በእስር ላይ የነበሩና አገዛዙ እንዲፈቱ የማይፈልጋቸው ስደተኞች መፈታታቸው አለማቀፍ እውቅና ባላገኘችው ሶማሊላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩን የሚያስ መሆኑን ይገልጻሉ።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events