Dehai News

Goolgule.com: የትግራይ ብሄርተኞች ዕብሪትና የጣናው ሞገድ ፈተና በመቀሌ!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Tuesday, 16 May 2017

የትግራይ ብሄርተኞች ዕብሪትና የጣናው ሞገድ ፈተና በመቀሌ!

 
  • “የትምክህት ፈረስ፣ ነፍጠኛ፣ የምኒልክ ርዝራዥ፣ አማራ አህያ፣ ገና መቶ ዓመት እንገዛሃለን፣ …” የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ጭፈራ
  • “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎች የመልስ ጭፈራ
  • የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆን? ያስፈራል!

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድድር ከፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች የተለየ ትኩረት ይስባሉ። የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ወደ ፕሪሚየርሊግ ለማደግ የሚደረጉ ፍልሚያዎች በመሆናቸው የተመልካቾችን ቀልብ ይስባሉ። የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ምድብ “ሀ” ላይ የተደለደሉት ክለቦች በወጣላቸው መርሐ-ግብር መሰረት ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጨዋታቸውን አድርገዋል።

የዚህ ውድድር ተሳታፊ የሆኑት መቀሌ ከነማ እና ባህርዳር ከነማ (የጣናው ሞገድ) በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ግቢ (FB campus) በተለምዶ አጠራር “አዲ ሀቂ” ስታዲየም ጨዋታቸውን አድርገዋል። የመቀሌ ከነማ እና የባህርዳር ከነማ ጨዋታን  ለመከታተል ከባህርዳር ወደ መቀሌ ከተማ ከተጓዙት የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች እና ጨዋታውን ከተከታተሉት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዕለቱ ጨዋታ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ የሰበሰብናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

የጨዋታው ድባብ

ጨዋታው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የተካሄደ እንደመሆኑ መጠን በርከት ያሉ ተመልካቾች ተገኝተው ጨዋታውን ተከታትለዋል። ባህርዳር ከነማን ለመደገፍ መኪና ተኮናትረው ከባህርዳር ወደ መቀሌ የተጓዙ ከ30 የማይበልጡ የደጋፊ ማህበሩ አባላት እና  በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች የጣናውን ሞገድ በባህላዊ ጭፈራና የእግር ኳስ ድጋፍ ዜማ  ለመደገፍ ቢጥሩም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች በሚያሰሙት ማንነት ላይ ያተኮረ ስድብ በጭፈራ ሲውጧቸው ታይቷል።

“የትግራይ ብሄርተኞችን ዕብታዊ ባህሪ አደባባይ ላይ ያወጣ ትዕይንት ነበር” የሚሉት የመረጃ ምንጮቻችን “የአማራን ባህልና ታሪክ ለማጉደፍ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታትን ሳይቀር በሥም እየጠሩ የስድብ ውርጅብኝ ሲያወርዱ ታይቷል” ይላሉ። በእያንዳንዱ ጭፈራቸው “የትምክህት ፈረስ፣ ነፍጠኛ፣ የምኒልክ ርዝራዥ፣ . . .” የሚሉ ስድቦችን “አማራ አህያ፣ ገና መቶ አመት እንገዛሃለን፣. . .” በሚሉ ፀያፍ ስድቦችና ዕብሪታዊ ኃይለ ቃላት በማጀብ በስታዲየሙ ውስጥ በጭፈራ መልኩ ማንነትን የሚነካ ስድብ በመሳደብ የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾችንና ደጋፊዎችን በሥነ-ልቦና ለማሸማቀቅ ሲጥሩ ታይቷል ሲሉ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሆኑ ለጎልጉል ይጠቁማሉ።

በአንፃሩ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ድጋፋቸውን በባህላዊ ጭፈራ አጅበው ክለባቸውን ሲደግፉ ቢቆዩም፣ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች የሚያሰሙት የማንነትን ክብር የሚነካ ስድብ እየጎላ በመምጣቱ “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” የሚል ምላሽ በጭፈራ እንዳሰሙ የጎልጉል መረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ።

በዚህ ሂደት “ጨዋታው በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ ባህርዳር ከነማ በተጋጣሚው መቀሌ ከነማ ላይ ጎል አስቆጠረ፤ ከጎሉ መቆጠር በኋላ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች የማንነትን ክብር የሚነካ ስድቦችንና የጎንዮሽ ጠብ ጫሪነት ድርጊታቸውን ገፉበት” በማለት በዕለቱ በስታዲየሙ የነበሩ መረጃ አቀባዮቻችን ይናገራሉ። ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ቀጥለው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቀቀ።

ከእረፍት መልስ የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ ሁኔታ ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ሆኖ ተጀመረ የሚሉት የመረጃ ምንጮቻችን “ጨዋታው በጀመረ በ60ኛው ደቂቃ ያልተገባ ፍፁም ቅጣት ምት ለመቀሌ ከነማ ተሰጠ” ይላሉ። በዳኛው ውሳኔ የባህርዳር ከነማ አሰልጣኝና ተጫዋቾች ቅሬታ ቢያሰሙም ዳኛው በውሳኔያቸው በመፅናታቸው በፍፁም ቅጣት ምቱ አማካይነት መቀሌ ከነማ ጎል አስቆጥሮ አቻ ሊሆን ቻለ። ከአቻነቷ ጎል በኋላም የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ዕብሪት አከል የማንነት ስድብ እና የጠብ ጫሪነት  ድርጊት እየጨመረ መሄዱን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ይናገራሉ።

“ሜዳ ላይ የነበረው ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ የመቀሌ ከነማ ተጫዋቾች በባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች ላይ ሜዳ ውስጥ ምራቅ እስከመትፋት የደረሰ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ጨዋታ ነበር” የሚሉት የባህርዳር ከነማ የደጋፊዎች ማህበር አመራሮች “የጨዋታው ኮሚሽነርና የመሀል ዳኛው ተነጋግረው የከፋ ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ጨዋታውን ማቋረጥ ነበረባቸው” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

በተለይም ከአቻነቱ ጎል በኋላ የመቀሌ ከነማ ተጫዋቾች የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች ላይ ያልተገባና ግልጽ ፋውል መስራት ጀመሩ። ጨዋታው በጀመረ በ85ኛው ደቂቃ አንድ የባህርዳር ከነማ ተጫዋች የቀኝ እግር ቁርጭምጭሚቱን በኃይል በመጎዳቱ ለህክምና ዕርዳታ ወደ ሜዳ የገቡ የህክምና ባለሙያዎች ተጫዋቹን በአልጋ (ስትሬቸር) ላይ አድርገው ከሜዳ ከወጡ በኋላ ሰብዓዊ ርህራሄ በሌለው መልኩ በቁማቸው ሲጥሉት በቅርበት የነበረው የባህርዳር ከነማ በረኛ ተመለከተ። ወደ ህክምና ባለሙያዎች በመሄድ እንዴት ይህን ታደርጋላችሁ በሚል ሲከራረከር፤ በዚህ ቅጽበት የመቀሌ ከነማ ተጫዋቾች ከባህርዳር ተጫዋቾች ጋር የአካል ፍትጊያ ያለው ግጭት እንደፈጠሩ የመረጃ ምንጮቻችን ዘገባ ይጠቁማል። ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ጥሰው መግባት ጀመሩ። ቁጥራቸው እጅግ አናሳ የነበሩ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ራሳቸውን ከአደጋ ለማራቅ ሽሽት ቢመርጡም ግራና ቀኝ ከከበባቸው የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ዱላ ማምለጥ ተሳናቸው። በዕለቱ ጨዋታ በተነሳው ግጭት ከባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች ሰባት ከደጋፊዎች ደግሞ አስራ ስምንት በድምሩ 25 የጣናው ሞገድ ቤተሰቦች ቀላልና ከባድ የአካል  ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአብዛኛዎቹ ጉዳት በድንጋይ በመፈንከት የደረሰ ጉዳት በመሆኑ ጉዳቱ ለተጫዋቾች የከፋ እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻችን ዘገባ ይጠቁማል።

የመቀሌ ፀጥታ ኃይል ሚና

በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ውስጥ ከፊሉ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ላይ የድንጋይ ውርጅብኝ እያዘነቡ ከፊሉ ደግሞ የሜዳውን አጥር ጥሰው ወደ ሜዳው ገብተው የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾችን እያሳደዱ በነበረበት ሁኔታ በስቴዲየሙ ውስጥ የነበሩ የፖሊስ አባላት ከተለያየ አቅጣጫ ሦስት አስለቃሽ ጭስ ቦምብ ተኩሰዋል።

በአስለቃሽ ጭሱ የታፈኑ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች እርዳታ ፍለጋ ወዲያና ወዲህ ቢሉም በፀጥታ ኃይሎች ከመገፈታተርና የፖሊስ ዱላ ከመቅመስ የተሻገረ ድጋፍ አላገኙም። አማራ ላይ ያነጣጠሩ የማንነትን ክብር የሚያጎድፉ ስድቦች ከመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች አንደበት ሲወጣ እያዩ ዝም ያሉት የመቀሌ ፖሊስ አባላት ከግጭቱ በኋላ ተጎጂዎች የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎችን ከተጫዋቾች “ተለዩ፣ ራቅ በሉ” በሚል ሲገፈታትሩ፣ እልፍ ሲልም ዱላ ሲያነሱ እንደታዩ የመረጃ ምንጮቻችን ዘገባ ይጠቁማል።

የጣናው ሞገድ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች በአጠቃላይ የቡድኑ አባላት ከባህርዳር ወደ መቀሌ የመጡባቸው መኪናዎች በመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች የድንጋይ ውርጅብኝ የመኪናዎቹ መስታወት እና የጎን አካል ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው የታሰሩ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች አለመኖሩ ብዙዎቹን እያነጋገረ ይገኛል።

የህክምና ዕርዳታ ጉዳይ

በዕለቱ ግጭት ከባህርዳር ከነማ ሰባት ተጫዋቾች እና አስራ ስምንት ደጋፊዎች በድምሩ 25 የጣናው ሞገድ ቤተሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአንፃሩ የቡድኑ ተጫዋቾች በክለቡ ወጌሻ በኩል ጊዜያዊ የህክምና ዕርዳታ የተደረገላቸው (ኋላ ላይ አይደር ሆስፒታል ተወስደዋል) ቢሆንም አስራ ስምንቱ የጣናው ሞገድ ደጋፊዎች ግን አፋጣኝ የህክምና ዕርዳታ ማግኘት ሳይችሉ ሰዓታት እንደተቆጠሩ የመረጃ ምንጮቻችን ይጠቁማሉ።

ከፀጥታ ኃይሎች የተተኮሱት የጭስ ቦምቦች ጭስ በረድ ካለ በኋላ ወደ ህክምና የተወሰዱት ተጎጂዎች በአይደር ሆስፒታል ከረፈደም ቢሆን የህክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸዋል። እንደ መረጃ አቀባዮቻችን ዘገባ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አይደር ሆስፒታል የሥራ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሐብታሙ አለምየ የተባሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ለተጎጂዎች ህክምና እየሰጡ በነበረበት ሁኔታ ከህክምና ክፍላቸው በፖሊሶች ታፍነው ተወስደዋል።

የእነ አባይ ወልዱ ለጣናዉ ሞገድ ያቀረቡት “የጉዞ ቅድመ ሁኔታ”

ከእግር ኳሱ ግጭት ጋር በተያያዘ በዕለቱ መቀሌ ዩኒቨርሰቲ የቢዝነስ ካምፓስ በትግራይ ብሄርተኞች ዕብሪታዊ ድርጊት ሲታመስ ውሏል። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ ፀያፍ ስድቦችን ሲሰደቡ፣ ዶርማቸው ሲደበደብ አምሽቷል። የኢትዮጵያ ነገሥታት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ምኒልክ በትግራይ ብሄርተኞች ስማቸው እየተጠራ ሲዘለፉ አምሽቷል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የባህርዳር ከነማ የቡድኑ አባላት እና ደጋፊዎች “የተጎዱ ተጫዋቾቻችንና ደጋፊዎቻችን ይዘን ከመቀሌ ከተማ ወጥተን እናድራለን” ቢሉም፣ የመጡባቸው መኪኖች ጉዳት የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ የአባይ ወልዱ የታጠቁ ኃይሎች ከከተማው መውጣት እንደማይችሉ እንደነገሯቸው የባህርዳር ከነማ የደጋፊዎች ማህበር አመራሮች የሰጡን መረጃ ያመለክታል።

“የዕለቱ ግጭት (ቅዳሜ ግንቦት 05/2009 ዓም) ምሽት ላይ የክለባችን አሰልጣኝ እና የቡድን መሪ እንዲሁም አምበሉ ለትግራይ ክልል ጋዜጠኞች በአማርኛ ቋንቋ መግለጫ እንዲሰጡ ተጠየቁ” የሚሉን የደጋፊ ማህበሩ አመራሮች፣ “በዕለቱ ጨዋታ ለተነሳው ግጭት የባህርዳር ከነማ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ስህተት ሰርተዋል” የሚል መግለጫ እንዲሰጡ በግልጽ የተጠየቁት የክለቡ አመራሮች በእምቢታ በመፅናታቸው ምሽቱን ሙሉ በውዝግብ እንዳሳለፉ ይናገራሉ።

“እኛ ባልነው መንገድ ጋዜጣዊ መግለጫውን ካልሰጣችሁ መቀሌ ከተማን ለቃችሁ መሄድ አትችሉም” ያሉት የመቀሌ ሹማምንት፣ ያሰቡት ባይሳካላቸውም የጣናው ሞገድ ቤተሰቦች ላይ ካደረሱት የአካል ጉዳት በተጨማሪ በሥነ-ልቦና ረገድ ማሸበሩ ተሳክቶላቸዋል የሚሉት የባህርዳር ከነማ የደጋፊዎች አመራር በያዝነው ሳምንት ውስጥ ጉዳዩን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ በባህርዳር ከተማ እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

ማንነት ተኮር የሆኑ አፀያፊ ስድቦችን እና የድንጋይ ውርጅብኝ የወረደባቸው የጣናው ሞገድ ቤተሰቦች እሁድ ረፋድ 3፡00 ሰዓት ላይ በድንጋይ ዉርጅብኝ መስታወታቸዉ የደቀቁትን የኮንትራት መኪኖቻቸዉን መጠነኛ የቴክኒክ ጥገና አድርገዉ በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ታጅበው መቀሌ ከተማን ለቀው ጉዟቸውን ወደ ባህርዳር አድርገዋል። በየደረሱበት የአማራ ክልል ከተሞች ላይም ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸዉ የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር አመራሮች የሰጡን መረጃ ያመለክታል።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዕለቱ ጨዋታ ዋና ኮሚሽነር ስለጨዋታው በሚያቀርቡት ሪፖርት ተመርኩዞ የዲሲፕሊን ቅጣት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። ዕብሪተኞቹ የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ያሰሟቸው የነበሩ የማንነትን ክብር የሚነኩ ስድቦች፣ ዘለፋዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ከተቀመጡ ክልከላዎች አንዱ የሆነዉን “ዘርና ብሄር ላይ ያነጣጠሩ ስም ማጥፋቶች (ስድብ) እና ጥቃት ማድረስ የሚለዉን ህግ ሚተላለፍ ነዉ። በርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “በምርጦቹ ዘር” የሚሰራ አይደለም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ከፌዴሬሽኑ ብዙም እንደማይጠብቁ ይናገራሉ። ይሁንና   በባህርዳር ከነማ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በድምሩ በ25 የጣናዉ ሞገድ ቤተሰቦች  ላይ ያደረሱት የአካል ጉዳት መቀሌ ከነማን ከዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሊያሰናብተው የሚገባ ጥፋት መፈፀሙን አስተያየት የሚሰጡ የስፖርት ጋዜጠኞች ይናገራሉ። ሆኖም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ይህን ውሳኔ የመወሰን በራስ መተማመን አቅም የለውም ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አልጠፉም።

ከቅሪላው ጉዳይ ጀርባ ግን ሁላችንም እንደ አገር፣ እንደዜጋ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ አለ። የትግራይ ማንአህሎኝ የብሄርተኝነት ስሜት በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ሳይቀር ዕብሪታዊ ድርጊት ማሳየቱ፣ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የደከሙና የዋተቱ ነገሥታትን ሥም እየጠሩ ማንቋሸሹ፣ ለድጋፍ የመጡ ደጋፊዎችን በድንጋይ ቀጥቅጦ መላክ፣… ወዘተ መሰል ዕብሪታዊ ድርጊቶች ከትግራይ ክልል ውጪ በተለይም በአማራ ክልል በትልልቅ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ትግራዋያን ላይ መዓት እየጠሩባቸው እንደሆነ ልብ ያሉት አይመስልም። ይህን መሰል ዕብሪታዊ ድርጊት የሚኮንን አንድም ትግራዋይ ልሂቅ አለመኖሩ ደግሞ ትግራዋያን በጅምላ እየጎሰሙት ያለ የዕልቂት ነጋሪት እንዳለ ይጠቁማል በማለት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ይናገራሉ።

አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ “ጦር ሰሪ ነኝ” የሚለው የህወሓት ዕብሪት አማራ ክልል ላይ ተንፍሷል በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡ በቀደመዉ ዓመት ህዝባዊ አመጽ 11,674 ትግራዋያን ጎንደርና አካባቢውን ለቀው ወደ ትግራይ ማፈግፈጋቸውን ለአስተያየታቸው ዋቢ አድርገው ከሚጠቅሷቸው አንዱ ነው። የጣናው ሞገድ ላይ ለደረሰው ዕብሪታዊ ድርጊትም በቅርቡ ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን የሚሉ ድምፆች ከአማራ ወጣቶች በኩል እየተደመጠ ነው። አገሪቱም በጊዜ ሂደት ራሷን ለርስ በርስ ጦርነት የምታመቻች ብቸኛ አገር ትመስላለች።

ደርግ በሥልጣን ላይ በነበረበት ዓመታት ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ለእግር ኳስ ግጥሚያ የሚመጡ ቡድኖች ልዩ ጥበቃ ይደረግላቸው ነበር። ውድድሮቹ በሚካሄድባቸው ስቴዲየሞች ከፍተኛ ውጥረት የመንገሡ እና ጨዋታው ከኳስ ይልቅ “ጦርነት” የሚካሄድበት ቢመስልም በዚህ መልኩ የማንነትን ክብር የመዝለፍና የኢትዮጵያን ነገሥታትን የማዋረድ ደረጃ አልተደረሰም ነበር። ጦርነቱ እየከፋና ሁኔታዎች እየተባባሱ በሄዱበት ጊዜ ግን መስመር የመልቀቅና ጽንፍ የመያዝ ክስተቶች አልነበሩም ማለት አይቻልም። ይኸው ሁኔታ ከአገሪቷ ፖለቲካ ጋር ተቀላቅሎ የፍጻሜውን ጅማሬ አሳይቶ የኤርትራ መለየት እውን አድርጓል።

በመቀሌው ክስተት የታየው ከህወሃት/ኢህአዴግ የ26 ዓመታት የግፍና የዘር አፓርታይድ አገዛዝ በኋላ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ነው። ለአንድ ዘር (ዘውግ) የበላይነት ሲተጋ የኖረው ህወሃት “የልፋቱን” ውጤት በአደባባይ እየሰበሰበ የመጣበት ሁኔታ በየዕለቱ እየታየ ነው። በጓዳ፣ በምሥጢር የሚነገሩ ነገሮች የአደባባይ “ምሥጢር” ሲሆኑ ሕዝብ እየተመለከተ ነው። በጎጥ እየተቧደኑ ከማኅበራዊ ሚዲያ የቃላት ዘለፋ እስከ ኳስ ሜዳ ድብድብ የሚደረገው ሁሉ እንደ ህዝብ አብረን ለመኖር የማንችልበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የመድረሳችን አንዱ አመላካች ነው። በጣም በፍጥነት ዕልባት ካልተደረገለት፣ በተለይም ከትግራይ ተወላጆች በኩል፣ ምናልባትም የመጨረሻው መጀመሪያ ሊሆን ይችላል! ያስፈራል!!


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events