Dehai News

Goolgule.com: የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች! “ክፋት” – በሁሉም መስክ!!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 08 June 2017

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች! “ክፋት” – በሁሉም መስክ!!

 

መርዛማ ፍሬ 11፡ የታሪክ መቃብር!

በስሜት በሚነዳ የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ታሪክ አካታችነት ባለው መልኩ በአጎልባች ሚና (ብሔራዊ ተዋፅዖ) መፃፍ እየተገባው ምክንያታዊነትን አስመንኖ የልዩነት ሃረጎችን ብቻ በመምዘዝ በየአቅጣጫው የሚፃፍ መሆኑ ከተካረረ ሙግት ሊፀዳ አልቻለም። መዋቅራዊ ድጋፍ ባለው መልኩ የታሪክ ሙግቱ እየተካረረ በመምጣቱ ብሔራዊ ርዕይ ርቆን የመንደር አጥር እስከመስራት ደርሰናል።

ደርግ በየትኛውም ያህል መጠን አምባገነንና ጨፍጫፊ ሆኖ ቢገኝም የኢትዮጵያን ታሪክ ሲንቅና ሲያንቋሽሽ አልተገኘም። ከቶውንም ለብሔራዊ ርዕይ መፍጠሪያነት እንደግብዓት ተጠቅሞበታል። ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ስሜትን (የጋራ ማንነትን) በመካድ ራሱን ብቸኛ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር አድርጎ የሰየመው ህወሓት፣ የአገሪቱን የረዥም ጊዜ ታሪክ ባለቤትነት አውርዶ በ100 ዓመት የታሪክ ሁነት ውስጥ ለመቀንበብ የሞከረበት መንገድ የታሪክ መቃብር ቆፋሪ ያደርገዋል። እነ መለስ ከበረሃ አዲስ አበባ እንደገቡ በጊዮን ሆቴል በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ዕድሜ 100ዓመት እንደማያልፍና ይህንኑ ጋዜጠኞች “እንደ አዝማሪ” ሲደጋግሙት እንደነበር ሞት እንደ ቡሽ ያስፈነጠረው መለስ ዜናዊ በዕብሪት ተናግሮ ነበር፡፡

በዘውጎች መካከል ደማቅ የልዩነት መስመር ለማስመር የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማስፋትና በመለጠጥ በኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ትከሻ ላይ የፖለቲካ ቁማር መጫወት የህወሓት የተለመደ ተግባር ሆኗል። እጅግ የበዛ የመርማሪነት ልቦና እና ልዩ የሙያ ሥነ-ምግባር የሚጠይቀው የታሪክ ትምህርት የህወሓት ካድሬዎች የዘውግ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ አጀንዳ ሆኗል። የህወሓትን የታሪክ መቃብር ቆፋሪነት ሚና ታከው የወጡ ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች የኢትዮጵያን ታሪክ እስከ ጥገኛ ቅኝ ግዛት ሃተት ድረስ በመለጠጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር የቆመችበትን የታሪክ መንገድ ሲኮንኑ ውለው ያድራሉ።

የኢትዮጵያን ነገሥታት መዝለፍና መሳደብ፣ ባልዋሉበት ማዋል ለዘውጌ ብሔርተኞች የማይናቅ “የፖለቲካ ትርፍ” አለው። ይህን መሰሉን ተግባር ህወሓት ከፊት ለፊትም ሆነ ከጀርባ ሆኖ በማራገብ ስራው ተጠምዶ ይገኛል። ፀጋና መከራ ሞልቶ ከፈሰሰበት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጋራ ማንነቶችን በማሳደግ ብሔራዊ ርዕዮችን መቅረፅ የሚቻልበትንና የአብሮነት ዋልታችን ማፅናት የሚቻልበትን ዕድል እያመከነ ያለው ህወሓት ስለ ሥልጣን የበላይነት የታሪክ መቃብር ቆፋሪነቱን ቀጥሎበታል።

የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃራሪ ትርጓሜዎች ከዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባ ሂደት የተመዘዙ መንታ ሰበዞች ናቸው። ታሪክ የፖለቲካ ፍላጎት ማሟያ ሆኖ እየቀረበ ያለውም ተፃራሪ ትርጓሜዎችን አብዝቶ በመለጠጥ ነው። መደባዊ ይዘት የነበረውን ዘውዳዊውን የጭቆና ዘመን ወደ ዘውጋዊ ጭቆና በመጠቅለል የ“ጨቋኝ” “ተጨቋኝ” ታሪክ ማቀጣጠል የህወሓት የተጠና የፖለቲካ መስመር ነው። በቀደመው ጊዜ እትዮጵያዊያን ለታሪክ ማንነት ፍፁማዊ ወጥ ይዘት በመስጠት የሚነሳ ግንዛቤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ገዥ ሥርዓታዊ መርህ ነበር። ታሪክ እንደሚባለው ዳቦ ባይብስልም እንኳን በትላንት እና በነገ መሀከል ያለ ድልድይ ነው። ህወሓት በታሪክ ጥላቻ የሰከረ ድርጅት በመሆኑ የትላንትና እና የነገ አገናኝ ድልድይ የሆነውን ታሪክ ዛሬ ላይ ወደ መቃብር እያወረደው ይገኛል።

በክህደት የታጀበው የታሪክ ምርኩዝ የህዝባዊ ታሪክ ፀሃፊያንን እውቀት በዘውግ ተኮር “ፍርዳቸው” የተነሳ ብኩን ሲሆን አስተውለናል። ስለ ዘውገና ታሪክ ለመፃፍ የተነሱ የታሪክ ፀሐፍት ከዘውግ አጥር መሻገር አቅቷቸው በአደባባይ ዘዉጌ ወገንታኝነታቸውን ሲያውጁ ታዝበናል። ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ ይዘው የሚነሱ የታሪክ ፀሐፍት ታሪክን  የዘውግ ፖለቲካ ገበያ አድርገውታል። የህወሓትን የታሪክ መቃብር ቁፋሮ ተከትሎ በአደባባይ እየታየ ያለው የታሪክ ስካር “ደፋሩን” ወደ እብሪት፣ ስሜታዊውን ደግሞ ወደ ጭፍን የዘውግ አክራሪነት እንዲሳብ አድርጎታል።

የኢትዮጵያን የነገ ተስፋዎች የናደው ህወሓት የአገሪቱን (ጥንታዊ) የህዝብ መስተጋብር፣ ግዛታዊ አንድነት እና ቀጣይ ታሪክ አደጋ ላይ ጥሎታል። ተጨባጭ የታሪካችን ፍሰት ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቆም የበዛ የህይወት መስዋትነት ተከፍሏል። እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጠመዝማዛ የታሪክ መንገድም አልፈናል። በብዙ መስዋዕትነት የተገኙ በጎ ፍሬዎችን (ጉንደት፣ ዶጋሌ፣ አምባላጌ፣ አድዋ ድሎችን) በጋራ ማክበርና ማወደስ ተስኖን፣ የማህበራዊ ትስስሮሻችን በአያሌው ላልቶ፣ አገራዊ አንድነታችን አደጋ ላይ የጣሉና ከሥርዓታዊ መልሶ ማዋቀር (የህወሓትን ጭቆና በጋራ ከመሻገር) ይልቅ መበተን (መገንጠል) ላይ ያጠነጠኑ ተፃራሪ የዘውግ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንደ አሸን በመፍላታቸዉ አገሪቱን የመበተን ጫፍ ላይ አድርሷታል።

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ መስመር ዜጎችን በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሙያና መሰል ዘርፎች በማደራጀት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር የሰርክ ተግባሩ ነው። በከተሞች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማህበራት ሥም በማደራጀት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያው ሲያደርግ ቢስተዋልም የታሪክ ባለሙያዎችን በማህበር ለማደራጀት አልደፈረም። ህወሓት የቀደመውን የኢትዮጵያን ታሪክ በበጎ ጎኑ መስማት የማይሻ የታሪክ መቃብር ቆፋሪ ድርጅት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ መስመር (ቀኖና) መሰረት ሊስትሮዎች እና አነስተኛ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን፣ የጉልበት ሰራተኞችን ሳይቀር በማህበራት ባደራጀበት ሁኔታ የታሪክ ባለሙያዎች በማህበር እንዲደራጁ እና የታሪክ ጥናት ሙያ መስክን እንዲያስፋፉ ለማድረግ የሚያስችል ፈቃድ ነፍጓል። የታሪክ ባለሙያዎችም ራሳቸውን በየቤተ መፅሐፍቱ ከመቅበርና የውጭ አገር ፌሎውሺፕ ከማሳደድ በተሻገረ ይህ ነው የሚባል ተግባር ሲፈፅሙ አልታየም።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አገሪቱ አንድም የታሪክ ጥናት ላይ የሚያተኩር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር መፅሔት (journal) የላትም። የታሪክ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ እንደ መርሐ – ግብር መስጠት ያቆመባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ናቸው። በአንጋፋነቱ የሚታወቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን በመቀበል ካቆመ ሁለት የትምህርት ዘመናት አልፈዋል። ህወሓት እንደ አቅጣጫ ይዞት ያለው ነገር የታሪክ ትምህርትን በመደምሰስ በልዩነት ውስጥ ብቻ የሚባክን አልቦ-ታሪክ ትውልድ መፍጠር ነው። ለታሪክ ጥናት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች በሌሉባት ኢትዮጵያ፣ ታሪክ የፖለቲካ ፍላጎት ማሟያ ሆኖ ሲቀርብ እየታዘብን ነዉ። ከዚህም አልፎ ታሪክን እና ተረትን በመቀላቀል የታሪክን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሃብት ሲያራክሲ ይታያል። የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ታሪክ ላይ ያለን የተዛባ ምልከታ ውጤት ነው። የአገር ምስረታ ሂደቶችን አብዝቶ መኮነን እልፍ ሲል ደግሞ ጉዳዩን እስከ ጥገኛ ቅኝ ግዛት ድረስ በመለጠጥ ከአብሮነት ይልቅ የመበተን (መገንጠል) ደወሎችን በየጊዜው መስማት የዛሬዋን ኢትዮጵያ ይበልጥ የሚገልፃት ሁነት ሆኗል።

የህወሓት የታሪክ ጥላቻ መንስኤ ከኢትዮጵያ ጥላቻ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የታሪክ መቃብር ቁፋሮው መንፈሳዊና ቁሳዊ የታሪክ ሃብቶችን ከማራከሱ በላይ አብሮነታችን የሚሸረሽር የስጋት ምንጭ ሆኖ ቀርቧል። በታሪክ ጥላቻ የሰከረው ህወሓት የኢትዮጵያን እንደአገር የመቀጠል ህልውና ቅርቃሮ ውስጥ ከቶታል።

የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና ከአደጋ ማውጣት የሚቻለው ከጥልቅ ትቅቅፍም ሆነ ከተካረረ የታሪክ ውግዘት በፀዳ መልኩ የአገሪቱ ታሪክ ሙያው በሚጠይቀው ሥነ-ምግባር መሰረት ከፖለቲካዊ ውገና በራቀ መልኩ ለሙያው መርሆዎች መታመን ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ታሪክን ለታሪክ ሙያተኞች ብቻ መተው ግድ ይላል። ከዚያ በፊት ግን በአገራዊና በታሪክ ጥላቻ የሰከረው ህወሓት ለታሪክ በቆፈረው ጉድጓድ መቀበር ይኖርበታል።

መርዛማ ፍሬ 12፡ የማህበራዊ ዕሴቶች መውደም!

ኢትዮጵያ እንደአገር ፀንታ የቆየችው በነገሥታቱና በገዥዎች ኃይል (ብቻ) ሳይሆን ህዝቡ በማህበረ-ኢኮኖሚ ትስስሮሹ የፈጠረው ድርና ማግ የማይበጠስ በመሆኑ ነው። ዘውግና ኃይማኖትን የተሻገረው ማህበራዊ ትስስሮሽ ኢትዮጵያን እንደ አገር አፅንቶ ያቆያት ቢሆንም በበታችነት ህመም የሚሰቃየው ህወሓት በጥላቻ ፖለቲካ እየተመራ የህዝቡን አብሮነት እና ማህበራዊ መስተጋብር ለመበጣጠስ ብዙ ርቀት ተጉዟል – በተለይም በከተሞች!

ምንም እንኳ መደባዊ ልዩነት የነበረ ቢሆንም በከተሞች የነበረው የህዝብ አሰፋፈር ዘውግና ኃይማኖትን ያላማከለ ጥብቅ ትስስር የሚታይበት ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ከተማን እንደማሳያ ብንወስድ በየሰፈሩ የነበረው ማህበራዊ ትስስሮሽ ራሱን የቻለ ማህበራዊ ወጌሻ ነበር። ኃይማኖታዊና ዘውጋዊ የልዩነት መስመሮች ሳይገድቡት ማህበራዊ ትስስሮሹን ከፍ አድርጎት የነበረው አዲስ አበቤ ከምርጫ 97 በኋላ “የልማት ተነሽ” በሚል የህዝቡን የቀደመ ማህበራዊ ትስስሮሽ ብጥስጥሱን አውጥቶታል።

ህወሓት ይህን ያከናወነው የቀደሙ የከተማ ነዋሪዎች የፈጠሩት ማህበራዊ ትስስሮሽ ለህዝባዊ እምቢተኝነቶች ጉልበት መሆናቸውን ምርጫ 97 ላይ በመረዳቱ ነው። እዚህ ላይ ሟቹ መለስ ዜናዊ “ደሃ ከአዲስ አበባ ይወጣል” ያለበትን ደሃ-ጠል ንግግሩን ሳንዘነጋ መሆኑ ልብ ይላል።

የአዲስ አበባ የቀደሙ ሰፈሮች በልማት ሥም መፍረሳቸው ቀጥሏል። ለተነሽዎቹ ተገቢ ካሳ ካለመስጠቱም በላይ በአዲስ አበባ ዳርቻ ቦታዎች ላይ እየተገነቡ ባሉ ኮንደሚኒየም መንደሮች እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ እንዲሁም በጥርጣሬ የሚተያዩ “ጎረቤቶች” ተፈጥረዋል።

ለብዙዎቻችን እንደዋዛ የሚታየው “የቡና ጠጡ”  ሥነ-ሥርዓታችን ላይ በእናቶቻችን ይነሱ የነበሩ ማህበራዊ ጉዳዮች የህብረተሰቡ ማህበራዊ ወጌሻ (Social Therapy) ሆነው ያገለግሉ ነበር። ይህ ማህበራዊ ወረት በተጠኑ የፖለቲካ ሴራዎች “ነበር” ወደ መባል ደረጃ ላይ ደርሷል። “ቡና ጠጡ” የሚለዉ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓታችንም የአገዛዙ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ የወል ባህላችን ሲያራክሰዉ እያየን ነዉ።

በ“ልማት ሥም” ተነሽ የሆኑ ነባር ነዋሪዎችን ብትንትን አድርጎ በማስፈር፣ ኃይማኖታዊ ልዩነቶችን በማክረር በተለይም በክርስትና እና በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መካከል “አክራሪ ሙስሊም”፣ “አክራሪ ክርስቲያን” በሚል ፍርጃ እና በዘውጎች መካከል የጥርጣሬ መንፈስ በመፍጠር የአብሮነት እሴቶችን በማውደም ላይ ተነጥሎ የቆመ የከተማ ነዋሪ ለመፍጠር ህወሓት የሴራ ፖለቲካው ላይ ተጠምዷል። ዛሬ ላይ የጉርብትና እርሾ በሌለው መልኩ በርን ዘግቶ መቀመጥ በበዛበት አዲስ አበባ ዘውጋዊ ማንነትን ከተንተራሱ ማህበራዊ ግንኙነቶች በተሻገረ መልኩ ሰዋዊ ጉርብትና ነጥፏል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዘውጋዊ ማንነት ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ቀርቧል።

ደስታና መከራን እንደሰው በጉርብትና ትስስር ከመካፈል ይልቅ አካባቢያዊ ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረገ “ማህበራዊ” ግንኙነት ገንግኗል። የንግድ ትስስሩ ዘውጋዊ መረብ የተዘረጋለት ሆኗል። በክርስትና እናትና አባትነት፣ በአይን አባትነት፣ በዕድር መረዳጃ ማህበራትና መሰል ማህበራዊ ሁነቶች ጥብቅ ትስስር የነበረው የከተማ ነዋሪ የአንድነት መስመሮች እየሰለሉ የልዩነት ሃዲዶች ተበራክተዋል። አዲስ አበባ አለም አቀፍ ከተማ ብትሆንም እንደ ዜጋ የከተሜ ባህሪ የሚንፀባረቅባቸው ሰዎች ውስን ናቸው።

የመረዳጃ ማህበራት ሳይቀር በዘውጋዊ ማንነት ስር የተቀነበቡ ድኩማን ማህበራት ሆነዋል። ለእርስ በእርስ መረዳዳትና መተጋገዝ መትጋት ቀርቶ ቋንቋ ተናጋሪነትን መመዘኛ ያደረገ የማህበረ-ኢኮኖሚ ትስስር ተዘርግቷል። በጊዜ ሂደትም እንደ አገር የነበሩን ማህበራዊ ዕሴቶች እየጠፉ ሄደዋል። ይህን የታዘበው የዘመናችን ባለቅኔ በዕውቀቱ ሥዩም፡-

“ሕዝብ እየጠበበ ዕድር እየሰፋ

የሚያቀባብር እንጅ የሚያኗኑር ጠፋ”

ሲል የማህበራዊ ዕሴቶቻችንን መውደም በግጥም መልኩ አመሳጥሮ ነግሮናል።

በከተሞች የሚስተዋለው ሰብዓዊ ንጥፈት የማህበራዊ ዕሴቶቻችን መውደም ምልክት ነው። እንደ አገር ያቆሙን ማህበራዊ ትስስሮሻችን እየተሸረሸሩ ዘውጋዊ ሃዲዶች እየሰፉ መሄዳቸው እንደ ዜጋ ሊያሳስበን ይገባል። የአገዛዙ ጌጥ የሆኑት ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎች፣ ህሊናቸውን የሸጡ ሙያተኞች የሚፈፅሙት ድርጊት፣ ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑ ወንጀሎች፣ … ሁሉ የማህበራዊ ዕሴቶቻችን መውደም ምልክቶች ናቸው። በዚህ ሁሉ ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ውስጥ ለፀፀትም ሆነ ለእርምት ዝግ የሆነው ህወሓት ለሥልጣን የበላይነቱ ማህበራዊ ቀውሱን ማፋፋሙን ተያይዞታል።

ጥልቅ የሆነ የትላንት ድምሰሳ እና የተቻከለ የዘውግ ፖለቲካ ምልከታ ያለው ህወሓት፣ ማህበራዊ ዕሴቶቻችንን አፍራሽ በሆነው የሴራ ፖለቲካው የውድቀት ጉዞውን ተያይዞታል። ውድቀቱም የብቻው አለመሆኑ እንደአገር ያሳስበናል። የግንቦት ሃያን መርዛማ ፍሬዎች ለማርከስ በኢትዮጵያዊ ስሜት እንደዜጋ ትውልዳዊ ኃላፊነትን መውጣት ግድ ይላል።

መርዛማ ፍሬ 13፡ የተቋም መኻንነት!

ኢትዮጵያ የአገረ-መንግሥት (ግዛት) ምስረታዋን በዳግማዊ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ከሞላ ጎደል አጠናቅቃ ነበር። አገሪቱን እንደ አገር የሚያስቀጥሏትን እና ዓለም አቀፋዊ ሞገስ የሚፈጥሩላት   ተቋማትን መፍጠር ግን ተስኗታል። ከዳግማዊ ምኒልክ ጅምር የተቋማት ምሥረታ ጀምሮ ከአንድ ክፍል ዘመን (100 ዓመት) በላይ ተጉዘን ይህ ነው የሚባል አርያነት ያለው ተቋም መመስረት አልተቻለም። አገዛዙ በቀደመው ግዜ ለመቆመ ዳዴ ይሉ የነበሩ ተቋማትን ከቶውንም ከወታደራዊ  ደርግ በላይ አብዝቶ መደቆሱን  ተያይዞታል። “ዴሞክራሲን በጎ ትሩፋት ለአገሪቱ አስተዋውቄአለው” እያለ የሚመፃደቀው ህወሓት፣ የአገሪቱን ተቋማት ጭራሽኑ በማምከን የሚስተካከለው  ገዥ ኃይል ያለ አይመስልም።

ወረቀት ላይ የሰፈሩ ህግጋትና በተጨባጭ ያለው አሰራር ፍፁም ለየቅል በሆነባት ኢትዮጵያ ተቋማቱ በቁጥር በርከት ያሉ ቢመስሉም ወጥ በሆነ የህወሓት የፖለቲካ ፍላጎት የታፈኑ መኻን ተቋማት ተፈጥረዋል። ለአገራዊ ችግሮቻተን የጋራ መፍትሄ ማመንጨት አለመቻላችን ከተቋም እጦት ጋር ይያያዛል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የግብርና መስክ ምርምርና ሌሎች  ማህበራዊ ግልጋሎቶች አቅርቦት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት  የግፍ ማዕከል፣ የፖለቲካ ድራማ መድረክ መሆናቸው ከዚህም አልፎ ተቋማቱ በካድሬዎች  መሞላታቸው፣ በአገራዊ፣ አካባቢያዊ ብሎም በአህጉራዊ ጉዳዬች ላይ ጥናትና ምርምሮችን የሚያድርግ የሙያተኞች ስብስብ (think-tank) አለመኖሩ፣ በየዩኒቨርሲቲዉ ተሰሩ የሚባሉ ጥናትና ምርምሮችም የመምህራኑ ኑሮ መደጎሚያ መሆናቸዉ፣…አገሪቱ በተቋም መኻን የተጠቃች ለመሆኗ አስረጅ ምሳሌዎች  ናቸው።

በሕግ አውጭና የፍትህ ተቋማት፣ ሚዲያ፣ ፖለቲካ ፖርቲ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ቢሮክራሲ፣ የሲቪል  ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ አገራዊ የሽምግልና እና የዕርቅ ተቋማት በዘላቂነት ኖረውን አያውቅም ። አሉ የሚባሉት ተቋማትም ከህወኃት የፖለቲካ መስመር ጋር የተጣበቁ፣ የጥቅመኘነት ፖለቲካ አራጋቢዎች ናቸው። ከቀደም ጀምሮ ወታደራዊው መንግስት የንጉሳዊ ሥርዓቱን፣ ህወሓት ደግሞ የደርግን ተቋማት ሙሉ በሙሉ በማፈራረሱ የተከማች ዕውቀት እና የዳበረ ተቋማዊ አሰራር  ርቆናል። በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በኢኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲዎች፣ በወታደራዊና በደህንነት ጉዳዩች ወ.ዘ.ተ ላይ የሚያተኩሩ (ሙያ ተኮር) ገለልተኛ ተቋማት ባለመኖራቸው አማራጭ ዕይታዎችን ርቀውን በአንድ ጠቅላይ አምባገነን የወንበዴ ቡድን የፖለቲካ ፍላጎት መነዳት የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ሆኗል። ነፃ ተቋማት ተፈጥረው ማየት የማይሻው አገዛዝ ፣ የአገሪቱን ተቋማት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ላይ የተገደበ ነው። የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ይህን መስሉን ሁነት (ተቋማትን መኻን ማድረጉን) ለማገዝ የወጣ “ህግ” መሆኑን ልብ ይሏል።

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የትኛውም ተቋማት ላይ ረዣዥም የቁጥጥር እጆቹን የዘረጋው ህወሓት፤ መንግሥታዊ ተቋማቱን የሚመሩ አካላትን መመልመያ መስፈርቱ በሙያዊ ብቃት/ችሎታ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት ነው። በተቋማቱ ውጥስ የተዘረጋው የ1፡5 የጥርነፋ አደረጃጀት ተቁማቱ ከህዝባዊና አገራዊ አገልግሎት የተነጠሉ እና የሃሳብ ድርቀት የሚስተዋልባቸው ረብ የለሽ ተቋማት  ሆነዋል። በአሰራር ደረጃ ህዝባዊ ዝንባሌ የሌላቸው የአንድ ፖለቲካ ፖርቲ ፍላጎት ማስፈፀምሚያ ከመሆን በተሻገረ የአዲስ አስተሳሰብና አሰራር አዋላጅ መሆን ያልቻሉ መኻን ተቋማት ናቸው።

በተቋማቱ ላይ ምሁራዊ ድባብን አፍዝዞ ካድሬዊ አሰራርን ያነገሰው አገዛዝ፣ ተቋማቱን ወጥ በሆነ ተዋረዳዊ የዕዝ ሰንሰለት ጠርንፎ ይዟቸዋል። ሩብ ክፍለ ዘመንን የተሻገረ የሥልጣን ላይ ቆይታ  ያለው ህወሓት በአገሪቱ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተቋም መገንባት አልቻለም። ህወሓት ሥልጣን ላይ እስከ ቆየ ድረስ የተቋማቱ መኻንነት ቀጣይነት ይኖረዋል።

መርዛማ ፍሬ 14፡ “ሕግ” የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ!

ህወሓት “የሰመረለት” አምባገነን ድርጅት ቢሆንም ከአቻው ደርግ ለየት የሚልበት ሕግን ለአገዛዙ  ፍላጎት ማርኪያ እንዳሻው የሚጠቀምበት አዲስ ሁኔታ መፍጠሩ ነው። አምባገነኖች በራሳቸው “ሕግ ነን” የሚሉ ቢሆንም ህወሓት ከዚህ የተለየ መንገድ መርጧል። ባልተጻፈ ሕግ ዜጎችን ከማስር ጀምሮ ካሰሩ በኋላ “ሕግ” ማውጣት፤ በተጠርጣሪ ዜጎች ላይ የሃሰት ክስ ከመመስረት እስከ ሃሳዊ  መረጃና ማስረጃ (የሰው፣ የሰነድ) ማሰባሰብ ድረስ ያሉ ሂደቶችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ህግን መጫወቻ አድርጎታል።

ህወሓት ሩብ ክፍለ ዘመን በተሻገረ አገዛዙ በርካታ ሕግጋትን አውጥቷል። እንደ ሌሎች አምባገነን አገዛዞች ሕግ አልባ አይደለም። ይህ ልዩ ያደርገዋል። አይዞህ ባይ እና ድርጎ ሰፋሪዎቹ  ምዕራባዊያኑ በፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞጋች የህብረተሰብ ክፍሎች፣ … ላይ የሚያካሄደውን ወከባና የእስር ዘመቻ በተመለከተ ሲጠይቁት “ሕግ ስለተላለፉ ነው” የሚል ምላሽ በተደጋጋሚ  ሲሰጥ ታይቷል። “ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የአገሪቱ ሰላምን የማረጋጋት መንግሥታዊ ኃላፊነት አለብኝ” የሚለው ህወሓት፣ ለዘፈቀደ የጅምላ እስሩ እና የአደባባይ መንግሥታዊ ፍጅቱ ለአለም  አቀፉ ማህበረሰብ “ሕጋዊ” ሽፋን ሲሰጠው ይስተዋላል። እልፍ ሲልም “ችግራችን የአፈፃፀም ነው” በማለት የአደባባይ ወንጅሉን ለማንፃት የሃሰት ካባ ይደርባል። የፖለቲካ ነክ ተከሳሾች ሕጉ የትም እንደሚያደርሳቸው  እየታወቀ ህወሓት እደፈለገ በሚያሸከረክረዉ “ሕግ” ዙሪያ እንዲከራከሩ ያደርጋል።

በ“ሸብርተኘነት ወንጀል” የተከሰሱትን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞጋች የህብረተሰብ ክፍሎች፣… ወዘተ የክስ ጉዳይ ሳንዘነጋ ከዚህ ወጣ ያሉ ጉዳዩችን መመልከት ይቻላል። ለአብነት ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ የወጡትን ሕጎች ስንመለከት በሕግ ደረጃ በጣም የሚገርሙ ናቸው። ያልወጣ የሕግ አይነት የለም፤ የአዋጭነት (feasibility study)፣ የኬሚካል አጠቃቀም፣ የአፈር ብክነት መከላከል፣ የአየር ንብረት መከላከል፣ … በተመለከተ የተቀመጡ ሕግጋት አስደናቂ  ናቸው። ሕግጋቱን ከውጭ ለሚያያቸው ግሩም ናቸው። ግን አንዳቸውም አይተገበሩም።

የፀረ-ሽብር ህጉ እና የተሻሻለው የፕሬስ አዋጅ በዋናነት ግልጽ የመብት ጥሰት የሚፈጽሙ ሸውራራ ህግጋት ናቸው። ህወኃት በየዘርፉ ማውጣቱና ለእያንዳንዱ አረመኔያዊ ድርጊቱ  “ህግን” መከታ/ሽፋን ማድረጉ የተለየ የወንበዴ ስብስብ ያደርገዋል።

ምንግዜም ቢሆን “ሕግ” የሚለው ኃይለ-ሃሳብ ለህወሓት የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ ነው። ህወሓት ሁሌም ቢሆን አፋኝና የሰመረለት ህግጋቱን እንዴት እንደሚያራክሳቸው በደንብ ያውቅበታል። በፍርድ ቤቶች በኩል የተጨፈለቀው የዳኞች ነፃነት ለህወሓት የረከሰ የፍትህ ሥርዓት ዋነኛ አስረጅ ምሳሌ ነው።

ኢ-ፍትሃዊነትን በፍትህ ካባ የከለለው ህወሓት ሕግን የጥላቻ ፖለቲካ ማራመጃው አድርጎታል። በዚህም ለህወሓት “ሕግ” የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ ነው። ነገሩ ግሪካዊው ፈላስፋ ፕሌቶ “ፍትህ ኃይለኞችን ለመጠበቅ የተቋቋመች መገልገያ መሳሪያ ነች” እንዳለው ነው። የህወሓትን  አፋኝና የይስሙላ ህግጋትን በመጣስ ሕግና ፍርድን በእጅ መጨበጥ አማራጭ የሌለው የመፍትሄ መንገድ ሆኖ ቀርቧል።

መርዛማ ፍሬ 15፡ “ኪራይ ሰብሳቢነት”!

ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል ያልተገባ የኢኮኖሚ ጥቅም በማጋበዝ ብቻ የሚተረጎም ሳይሆን ከዚህም ባለፈ የፖለቲካ ጥቅም ትስስር (ኔት ወርክ) እና አካባቢያዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ የሥልጣን መደጋገፍንም የሚጨምር የትርጉም ይዘት አለው። የአገዛዙ የፖለቲካ መሃንዲሶች ለማመን በሚከብዱ የሙስና መረቦች በመተብተባቸው በህዝቡ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጥልቅ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ የተፈጠሩ ህዝባዊ አመፆች የአደጋው አንዱ ገጽታ ነው። ሁለተኛው የአደጋው መልክ ደግሞ ባለሥልጣናቱ እንደ ቡድን በሚዘረጉት የሙስና መረብ ከጥቅም ትስስራቸው ጋር በተያያዘ እንደመንግስታዊ መዋቅርም ሆነ እንደ ድርጅት የሚመጡ ግምገማዎችን በጋራ የሚመክቱበት (እየመከቱ ያለበት) እንዲሁም ባለሥልጣናቱ የራሳቸውን የቡድን አባል ወደ ተሻለ የሥልጣን ከፍታ ለማውጣት የሚያደርጉት ርብርብ የቡድን ፍላጎት የሚታይበት በመሆኑ ፍላጎቱ ከሌላው ቡድን ጋር የሚጋጭ ከሆነ በዚህ መሀከል የሚፈጠረው ልዩነት ከሥርዓቱ አልፎ ለአገርም አደጋ የሚሆንበት ዕድል ይኖራል።

በዚህ አግባብ የህወሓት የበላይነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለኢሕአዴግ እንደ “ግንባር” ኪራይ ሰብሳቢነት የድርጅቱ አደጋ ሆኗል። ‹የግንባሩን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት ነው› የመባሉ እውነታም ከዚህ የመነጨ ነው። በተለይም የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ዘውግን መሰረት ያደረገ ቡድንተኝነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ አደጋው ጠባብነትን መታያው አድርጎ እዚህም እዚያም እየታየ ነው። በቀጣይ ይህን ተከትሎ የሚፈጠረው ችግር ከአገዛዙ ስብስብ አልፎ ለአገርም (የእርስ በእርስ ጦርነት) የከፋ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም። በተለይም በመከላከያና በፖሊስ (የፌዴራልና የክልል) ሰራዊቱ ያለው አድሏዊ የሹመት ሁኔታና የከፋ ሙስና ከዘውግ ፖለቲካዉ ጡዘት አኳያ ራሱን የቻለ የጊዜ – ቦምብ ማለት ነው።

አገዛዙ “ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገል ጥረት እያደረኩ ነው” እያለ ዲስኩሩን ቢያሰማም፣ ችግሩ ከመባባሱ ውጪ ጠብ ያለ ለውጥ በአደባባይ ሊታይ አልቻለም። እጅግ አስደንጋጭ የሙስና ሪከርዶች በ“ተወካዮች ምክር ቤት” በኩል በሪፖርት መልኩ ሲታለፍ ማየት የሚደንቅ አይደለም። አቅም አልባነት መታያው የሆነው የአገሪቱ “ጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ በአደባባይ “ሙስና አለ! ነገር ግን ማስረጃ የለንም!” ሲል የተናገረው ጉራማይሌ ንግግር ሙስናና አገዛዙ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም መንታ ገጽታ ለመሆናቸው አስረጅ ምሳሌ ይሆናል። በተለይም በመሬትና በፍትህ አስተዳደር እንዲሁም በመንግሥት ንብረት ግዢና ሽያጭ፣ ታክስ ተኮር ጉዳዮች ላይ እየታዩ ያሉ ግልፅ የሥልጣን መባለጎችን ስናስተውል አገሪቷን እንደ “መንግስት” እያስተዳደራት ባለው አገዛዝ ላይ እምነት እንድናጣ ያደርገናል።

በ2008ዓ.ም የሥራ ዘመን የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ለ”ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት ሃያ አምስት የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ህጋዊነት የሌለው የንብረት ግዢና ሽያጭ ማካሄዳቸውን፣ ሥራቸውን የለቀቁ ሰራተኞች በሌሉበት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ደመወዝ እንደተከፈላቸው፣ ያለ ጨረታ የኮንስትራክሽን ግንባታ ሥራዎች ለተለያዩ ተቋራጮች እንደተሰጠ፣ ህጋዊ የደመወዝ ጭማሪ ላልተደረገላቸው ሰራተኞች በህገ – ወጥ መንገድ ተጨማሪ ክፍያ የከፈሉ መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን፣… ሪፖርቱ ያመለክታል። በዚህም እንደ አገር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተመሳከረ ሒሳብ መኖሩን ይጠቁማል። ሪፖርቱ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን (ዩኒቨርሲቲዎችን) ብቻ የሚመለከት ነው። በመንግስት የልማት ድርጅቶችና በየክልሉ ያለውን ምዝበራ ከዚህ ሪፖርት አኳያ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የንብረት ግዢና ሽያጭ ችግር አለባቸው፣ ህጋዊ የፋይናንስ አሰራር አልተከተሉም በሚል በሪፖርቱ የጠቆማቸው መንግስታዊ ተቋማት አመራሮች በህግ ሲጠየቁ አላየንም።

በርግጥ በአገዛዙ ቤት ፖለቲካን እንጅ የህዝብን ገንዘብ መስረቅ የአገዛዙ አንዱ ገጽታ ነውና የተለየ እርምጃ አይጠበቅም። ይሁንና እነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ከገንዘብ ባለፈ የፖለቲካ ፍንገጣ ያሳዩ ቀን ‹ፋይላቸው› ከመሳቢያ መውጣቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ረገድ የዛሬውን “ፓስተር” የትላንቱን  “ማርክሲስት” ታምራት ላይኔን፣ የፈርዖናዊ ዕብሪት ባለቤት የነበረውን ስየ አብርሃን፣ ሴት አውሉን መላኩ ፈንታን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።

በህወሓት/ኢህአዴግ ቤት፣ ከሁሉም የሙስና አይነቶች ከባዱ ሙስና የመሬት ወረራን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ምዝበራ ዋናው ተጠቃሽ ነው። በዚህ ዘርፍ እየታየ ያለው ሙስና “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል”  እንዲሉ የከፍተኛ አመራሮችን ፈለግ በመከተል ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች “ከድርሻቸው” በላይ በወዳጅ ቤተ ዘመድና በሙታን ስም ሳይቀር የመሬት ወረራውን ተያይዘውታል። የታችኛው አመራር ምዝበራ አይን እያወጣ በመምጣቱ “ኪራይ ሰብሳቢነትን እየተዋጋሁ ነው” የሚለው አገዛዙ፣ ለአስመሳይ ፖለቲካው ማሳያ ይሆን ዘንድ አልፎ አልፎ የታችኛውን አመራር ጭዳ ሲያደርገው ይታያል። ነገሩ ‹የኪራይ ሰብሳቢዎች መተካካት› አይነት ነገር ነው። የበላ ይሻራል። ያልበላ ይሾማል። ሹዋሚውና ሻሪው ህዝብ ሳይሆን የላይኞቹ የህወሓት ቁንጮ አመራሮች ናቸው። የሩብ ክፍለ ዘመኑ የአገዛዝ ተሞክሮም ኡደቱ በዚህ መልኩ እየቀጠለ እንደመጣ አመላካች ነው።

ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በተለይም ሃሰተኛ የመሬት ባለይዞታነት መረጃ በማዘጋጀትና ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ ላላሟሉ ሰዎች በጥቅም ትስስር መሬት የመስጠቱ ሁኔታና የአመራሩ የመሬት ቅርምት ከአዲስ አበባ ከተማ በከፋ መልኩ በሌሎች የክልል ከተሞች እንዳለ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው። በፍትህ አስተዳደር በኩልም አስደንጋጭ የሙስና ተግባር እየተፈፀመ ይገኛል። ከ50 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ በመቀበል በሃሰተኛ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍርደኞችን የለቀቁ የፌዴራሉና የክልል ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን እንዲሁም ከሙስና ጋር በተያያዘ የዳኞችን ክስ/ስንብት መስማት ከዓመት ዓመት እየተለመደ መጥቷል።

እንግዲህ በ“ሕግ በምትመራ” አገር ላይ ከዓመት ዓመት አስደንጋጭ የሙስና ዜናዎችን በሪፖርትም፣ በክስም መልክ እያየንና እየሰማን በመሆኑ “መንግስት” የሚባለው አካል ምን እየሰራ እንዳለ መጠይቅ ግድ ይለናል። የመሬትና የፍትህ አስተዳደርን እንደማሳያ አንስተን እጅግ በጥቂቱ ተመለከትን እንጂ ገቢዎችና ጉምሩክ ላይ እና በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ተቋማት ምን አይነት ጉድ ሊፈፀም እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።

በየዓመቱ ተዝቆ ከማያልቁ መንግስታዊ ጉዶች መካከል እጅግ ጥቂቱን ቆንጥሮ በሪፖርት መልኩ ለ“ተወካዮች ምክር ቤት” የሚያቀርበው የፌዴራሉ ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርት ከአንድ ሰሞን ወሬ የተሻገረ ረብ ያለው ለውጥ አልታየበትም። ከአሳ ነባሪዎች ይልቅ ትንንሽ አሳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ “መረቡን” መጣል የሚያዘወትረው “የፌዴራል የሥነ – ምግባርና የፀረ – ሙስና ኮሚሽን” በአዋጅ የተሰጠው “ሥልጣን” መልሶ በአዋጅ ተገፏል። ኃላፊነትና ተግባሩም ሙስናን በተመለከተ ባነርና በራሪ ወረቀት በማዘጋጀት ተገድቧል።

የፍትህ ሚኒስተር በአዋጅ ፈርሶ “የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ” በሚል በአዲስ መልኩ ተደራጅቷል። አዲሱ አደረጃጀት የሥራ አስፈፃሚውን ገደብ የለሽ የንዋይና የሥልጣን ብልፅግና እየተከታተለ በህግ እንዲዳኝ ከማድረግ ይልቅ፤ ልቅ የፖለቲካ ይሁንታ የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል። አገሪቱ በአስከፊ የህዝብ አመፅ አልፋ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተው፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አካላቸው ጎድሎ፣ ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም ደርሶ በጉይዩ ላይ ተጠያቂ የተደረገ መንግሥታዊ አካል አለመኖሩና አገዛዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምልዓት እየተገበረ ያለው የህዝብ ሃብት ምዝበራ በመቀጠሉ በቀጣይ አገዛዙን የሚያፈራርሰው ህዝባዊ አመጽ ካለ ክቡር መስዋዕትነት ስለመገባደዱ መታመን የሚቻል አይደለም!!

ቀደም ብለው የታተሙት ኣርእስቶች:

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች! (ክፍል 1)

http://dehai.org/dehai/dehai-news/160333

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመሬት ነጠቃና ስደት (ክፍል ሁለት)

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመንግሥት ውሸት፣ የሃይማኖት ተቋማት ውድቀት፣ … (ክፍል ሦስት)

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች — የአንድ ጎጥ የበላይነትና የመበታተን አደጋ!

http://dehai.org/dehai/dehai-news/163170

የሚንተከተከው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢና አንድምታዎቹ!

http://dehai.org/dehai/world-news/161240
 
Dm eri tv subscribe

(Eritrea EmbassyMedia) - President Isaiss Afeworki - Press Conference in Washington DC

Hdri Media Books on Amazon.com
visit hdrimedia.com