Dehai News

TGIndex.BlogSpot.de፡ የመንግስቱ ሃይለማርያም “ዛሬም ድረስ ያልተፈታ” እንቆቅልሽ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Saturday, 12 August 2017

የመንግስቱ ሃይለማርያም “ዛሬም ድረስ ያልተፈታ” እንቆቅልሽ

 
ነሓሰ 12, 2017
 
 
    ዶክተር ስንታየሁ ካሳ የተባለች የዳላስ ከተማ ነዋሪ፤ ስለ አባቷ የጻፈችውን መጽሃፍ አንብቤ ከጨረስኩ ጥቂት ሳምንታት አለፉ። አባቷ ኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም ይባላሉ። በግእዝ አቆጣጠር በ1971 ኤርትራ ላይ ልዩ ስሙ መዕድነ በተባለ ቦታ በጦርነት ህይወታቸውን አጥተዋል። የጻፈችው መጽሃፍም በዚሁ ጭብጥ ዙሪያ ነው።
 
      የዶክተር ስንታየሁ መጽሃፍ እንደሚጠበቀው ሴት ልጅ ለአባቷ የሚኖራትን ተፈጥሯዊ ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነው። ስለ አባቷ ከልጅነቷ ጀምሮ የሳለችውን የሰው ልጆች ሁሉ ስለአባታቸው የሚኖራቸውን በጎ ገጽታ የሚያንጸባርቅ መጽሃፍ ነው። ስንታየሁ መጽሃፉን ለመጻፍ ስትነሳ ምንም ይሁን ምን ስለአባቷ አሉታዊ ነገር ለመስማት ዝግጁ አልነበረችም። ስለዚህ የታሪኩን ፍጻሜ በምትመኘው መንገድ ለመቋጨት ብዙ ደክማለች።ስለ አባቷ የተነገሩ ጥሩ ነገሮችን ሁሉ ሰብስባለች። ስለ አባቷ የተነገሩ የመሰላትን ደካማ ጎኖች ሁሉ ደግሞ ለማስተባበል ሞክራለች። 

      በርግጥ ይህ የሚጠበቅ ነበር። ከዚህ   ቀደም ደረጀ የተባለ የጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ልጅም በተመሳሳይ ስሜታዊ ሆኖ የጻፈውን መጽሃፍ አንብበናል። ምንም ማለት አይቻልም። ልጆች አባታቸውን እንደ መልአክ መውደዳቸው ተፈጥሯዊ ነው። ማድረግ የሚቻለው በመስመሮች መካከል እውነቶችን መፈለግ ብቻ ነው።
 
      የዶክተር ስንታየሁን ጥራዝ በጥንቃቄ አንብቤዋለሁ። የኮሎኔሉ ሴት ልጅ ብዙ ደክማለች። ወደ ሃራሬ ደውላ ከኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር ሳይቀር ቃለመጠይቅ አድርጋለች። እና በመጨረሻ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያምና ጄኔራል ገብረክርስቶስ ቡሊ በአሻጥር አባቷን እንደገደሉባት አመነች። አንባቢ ይህን አንዲያምንላትም በጣም ጥረት አድርጋለች። መቸም በኔ በኩል መንግስቱ ሃይለማርያምን አጥብቄ ስለምጠላው ባምንላት ደስ ይለኝ ነበር። ግን አላሳመነችኝም። መጽሃፉን አንብቤ ስጨርስ መንግስቱ ሃይለማርያም ኮሎኔል ካሳ እንዲገደሉ ምንም አሳብ እንዳልነበረው ለመረዳት ቻልኩ።
 
      መንግስቱ በጻፋቸው መጻህፍትም ሆነ በንግግሮቹ ብዙ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ነግሮናል። መንግስቱ ጨካኝ፣ ነብሰ ገዳይ፣ ክፉ ነበር። ብዙ ወጣቶችን ቀርጥፎ በልቷል። በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት ይቻላል። ኮሎኔል ካሳ ገብረማርያምን ግን ሆን ብሎ አልገደላቸውም። ውሸት ምን ያደርጋል? መንግስቱ ነፍሰ ገዳይ ስለነበር ብቻ የተገኘውን ግድያ ሁሉ እላዩ ላይ መለጠፍ ተገቢ አይመስለኝም።ስለ ኮሎኔል ካሳ አሟሟት ስትጠይቀው መንግስቱ እንዲህ ሲል መለሰ፣

      “አንዳንዶቹ የተረፉት ሰዎች እንደነገሩን….ዛሬም ድረስ ያልተፈታ…ብዙዎቻችን የምንለው የጠላት ቃኚ እዛ ሄዶ በድንገት የኛን ጦር በማየቱና ጦሩን ቀስቅሶ በዚያ ተመልሰው ሄደው ናቅፋን ተቆጣጠሩት ነው የሚሉን። አንዳንዶች ደግሞ ‘ሻእቢያ መጀመሪያውንም ቢሆን እኮ እዛው ነበር’ ነው የሚባለው። ብዙዎቹ ግን፣ ‘ኖ! ሻእቢያ እዚያ አልነበረም። የነበረው ሌላ ቦታ ነው።’ ይላሉ። ይህን የመሰለ አወዛጋቢ ነገር አለ። ያም ሆነ ይህ በመረጃ ስህተትም ይሁን በሌላ ምክንያት እነ ኮሎኔል ካሳ…ባላሰቡትና ባልጠበቁት ነገር ጉዳት ደረሰባቸው። አብዛኛው ሰራዊት ተሰውቶ፤ በጠቅላላ መሪዎቹ ሞተው ያ ውጊያ በዚህ አይነት ሁኔታ፣ በጣም ባሳዘነና መሪር በሆነ ሁኔታ አከተመ።” (ገጽ 369)
 
      የኤርትራ የሰነድና ምርምር ማእከል “መፈፀምታ” (ፍጻሜው) በሚል ርእስ በ2016 ባሳተመው ዳጎስ ያለ መድበል ላይ የጄኔራል ፊሊጶስ ወልደዮሃንስን ትረካ ይዟል። በጄኔራሉ ትረካ ከኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም ጋር ስለተደረገው ውጊያ በዝርዝር ተርኳል። መንግስቱ ሃይለማርያም “እስከዛሬም ድረስ ያልተፈታ እንቆቅልሽ” ሲል የገለጸው ጉዳይ በመጽሃፉ ውስጥ በዝርዝር ቀርቧል። አስደናቂው ጉዳይ የኮሎኔል ካሳ፣ የጓደኞቹና  የሰራዊታቸው አሟሟትና መደምሰስ ለመንግስቱ ሃይለማርያም ብቻ ሳይሆን፤ ለጄኔራል ፊሊጶስ አለቆች ጭምር አስገራሚ እንቆቅልሽ የነበረ መሆኑ ነው። ኮሎኔል ካሳ ተገድሎ መዕድነ ኮረብታ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፊሊጶስ በራዲዮ ሲገልጽላቸው፣ በወቅቱ ቀጥታ ጉዳዩን ይከታተል የነበረው አሊ ሰይድ አብደላ ፊሊጶስ መሳሳቱን አምኖ ነበር።ፊሊጶስ አሊ ሰይድ አብደላን ለማሳመን የኮሎኔል ካሳ አስከሬን ከሚገኝበት ኮረብታ ላይ የሚገኙ ታጋዮች ሁለት አብሪ ጥይት እንዲተኩሱ በሬድዮ አዘዘ። እንዲህም ሆኖ የበላይ አካላቱን ሳያሳውቅ ፊሊጶስ የፈጸመውን ጀብዱ አለቆቹ ማመን ተቸግረው ነበር። መንግስቱ ሃይለማርያም “ዛሬም ድረስ ያልተፈታ” ያለው እንቆቅልሽ በፊሊጶስ ትረካ ላይ በዝርዝር ቀርቧል።

         የኮሎኔል ካሳ ሴት ልጅ ይህን ትረካ ባለማንበቧ ብዙ መላ ምት ውስጥ ገባች። መንግስቱን ያለሃጢአቱ ጠረጠረችው። ደርግ በወቅቱ በእቅድ ደረጃ ስህተት አልፈጸመም። በፊሊጶስ ይመሩ የነበሩት የብርጌድ 44 አባላት ግን ሊታመን የማይችል ጀብዱ በመፈጸማቸው ኮሎኔል ካሳና ጓደኞቹ ህይወታቸውን ለማጣት በቁ። ፊሊጶስ “ጦርነት ከስነ እውቀት በላይ ስነጥበብ ነው” በሚል ርእስ ለንባብ ያበቃውን ትረካ ወደፊት ከትግርኛ ወደ አማርኛ ትርጉሜ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
Dm eri tv subscribe

ERi-TV, Eritrea: Ethiopia Welcomes President Isaias Afwerki, July 14, 2018 - Part 1

Hdri Media Books on Amazon.com
visit hdrimedia.com