Dehai News

Ethsat.com: በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በበርካታ ከተሞች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Wednesday, 13 September 2017

በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በበርካታ ከተሞች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው

ESAT DC Daily News Wed 13 Sep 2017

 

https://ethsat.com/2017/09/esat-daily-news-amsterdam-september-132017/

(ኢሳት ዜና–መስከረም 3/2010)በምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በበርካታ ከተሞች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

አጠቃላይ የተቃውሞ ሰልፍም እንዲደረግ በኦሮሞ ወጣቶች ጥሪ መተላለፉ ተሰምቷል።
ዛሬ በሀረርና በድሬዳዋ ተቃውሞ ተጀምሯል። የስራ ማቆም አድማም ተመቷል።

በድሬደዋ ወታደሮች በብዛት መግባታቸው እየተነገረ ነው።በአወዳይ ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል መንግስት ግጭቱ ቆሟል ሲል መግለጫ ሰጥቷል።
ግጭቱ ቀጥሏል። የቀውስ ቀጠናው አድማሱን አስፍቷል።

በህወሀት መንግስት ልዩ ድጋፍ የሚደረግለትና በአብዲ ኢሌ አስፈጻሚነት የሚዘወረው የሶማሌ ልዩ ሃይል ከኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከፈተውን ጥቃት ለመመከት በኦሮሞ ተወላጆች በኩል የተጀመረው የመከላከል እርምጃ አከባቢውን ወደለየለት ቀውስ እንዳይከተው ስጋቱ ተጠናክሯል።

በዛሬው ዕለት በተለያዩ የምስራቅ ሀረርጌ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ትላንት ተቃውሞውን በጀመሩት በደደርና አወዳይ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
በአወዳይ ብቻ ከ10 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በደደርም የትላንቱን ጨምሮ 5ሰዎች በግጭቱ ህይወታቸው ማለፉን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በመላው ኦሮሚያ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ በመግለጽ ትግሉን በህቡዕ የሚመሩት የኦሮሞ ወጣቶች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዛሬው ዕለት የተካሄዱት ተቃውሞዎች ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር ግጭት የተፈጠረባቸው ሲሆን በባቢሌ የኦሮሚያ ፖሊሶች በሰልፈኞች ላይ መተኮሳቸውን ከአካባቢው የኢሳት ዘጋቢ ገልጿል።

በድሬዳዋ በመልካ ጀብዱና አንዳንድ ቀበሌዎች የስራ ማቆም አድማ ተደርጓል። የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። ሱቆች ተዘግተዋል።
በሌላ በኩልም የሶማሌ ልዩ ሃይል አባላት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚፈጽሙትን ግድያ በመቃወም የሃረር ከተማ ነጋዴዎች ዛሬ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አድማ እያደረጉ ነው።

ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ጭር ብላ ውላለች። ከትላንት ጀምሮ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወደ ሀረር ከተማ በመግባት ላይ ሲሆኑ ዛሬም በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል ወጥተው ሀረር ከተማ ገብተዋል።
የመከላከያ ንብረት የሆነ ታርጋ ቁጥሩ “መከ 47187” ኦራል መኪና ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ጭኖ ከ15 ደቂቃዎች በፊት ሃረር ከተማ መግባቱን የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ በቅርበት እየተከተታለ የሚገኘው ዘጋቢያችን ገልጿል።

በጅጅጋ ፖሊሶችና የክልሉ ባለስልጣናት ያደራጁዋቸው ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የኦሮሞ ተወላጆችን መታወቂያ በማየት ወደ ማጎሪያ ቦታ ወስደዋቸዋል። የሶማሌ ተወላጆች የኦሮሞ ወገኖቻቸውን በመደበቅ አጋርነታቸውን እየገለጹ ነው:፡
በካራሚሊ በህወሀት ታጣቂዎች 3 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ 5 የሚሆኑት መቁሰላቸው ታውቋል።

በሌል በኩል በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የተምታቱ መግለጪያዎችን መስጠቱን ቀጥሏል። በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ግጭቱ መቆሙንና መንግስትም መቆጣጠሩን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ዛሬ በህወሀት ልሳን ሬዲዮ ፋና ቀርበው ሁለት የመንግስት አመራሮች በደደር መገደላቸውን ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱን ተናግረዋል። የተባባሰውን ግጭት ሲደብቅ የከረመው መንግስት በመጨረሻም ማመኑ ነው የተገለጸው።

 

Dm eri tv subscribe

Eritrean Memorial Day ምዓልቲ ስዉኣት ኤርትራ

Hdri Media Books on Amazon.com
visit hdrimedia.com