Dehai News

ገጽ-መጽሓፍ: “ሻዕቢያ”-ድህረ-ቀይ ኮከብ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 05 October 2017

“ሻዕቢያ”-ድህረ-ቀይ ኮከብ

ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------

ጥቅምቲ 5, 2017 ዓም ፈረንጂ

Kein automatischer Alternativtext verfügbar.


===ድህረ-ቀይ ኮከብ===


የቀይ ኮከብ ዘመቻ በሽንፈት ከተቋጨ በኋላ የዘመቻውን መጀመር በከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ያበሰሩት የመንግሥት ሚዲያና ፕሬሶች በዝምታ ተዋጡ፡፡ በኤርትራ ምድር ስለሚካሄድ ወታደራዊም ሆነ ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ደፍሮ የሚናገር ጠፋ፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻም ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በሰኔ 20/1984 ተሰረዘ (የዘመን አቆጣጠሩ እንደ አውሮጳ ቀመር መሆኑን አትርሱ)፡፡

አንዳንድ ጸሐፍት ዘመቻው እንደታቀደው በድል ቢደመደም ኖሮ ሻዕቢያ ከኤርትራ ምድር ይነቀልና ኤርትራም በማያሻማ ሁኔታ የኢትዮጵያ አካል መሆኗ ይረጋገጥ ነበር ይላሉ፡፡ ሌሎች ግን ይህንን አባባል ይቃወማሉ፡፡ “የኤርትራ ችግር በሰላማዊ መንገድ እስካልተፈታ ድረስ የሻዕቢያ መጥፋት ብቻውን የኤርትራን ኢትዮጵያዊነት አያረጋግጥም” በማለትም ያክላሉ፡፡ ታዲያ ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት የተደረገው ጥረት በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከወታደራዊ እርምጃ በስተቀር የሰላሙን መንገድ መከተልን እንደ አማራጭ አልወሰዱትም፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት በራስ ተነሳሽነት ያደረጉት ጥረት ከግብ ሳይደርስ የቀረው ሊቀመንበር መንግሥቱ ችግሩን በወታደራዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት በመወሰናቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የሀገርና ህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ኮ/ል ተስፋዬ ወልደሥላሤ በግላቸው ያደረጉት የሰላም ጥረት በሊቀመንበሩ ግትርነት እንደተሰናከለባቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡


፠፠፠፠፠፠


በመጋቢት ወር 1975 አንዳንዶች “ጸጥተኛው ዘመቻ” በማለት የሚጠሩት ወታደራዊ ኦፕሬሽን ተጀምሮ ነበር፡፡ ዘመቻው “ጸጥተኛ” ተብሎ የተጠራው በህዝብ ሚዲያ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ስላልተደረገለት ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ የተካፈለው የወታደር ብዛት በቀይ ኮከብ ጊዜ ከነበረው እጅግ በጣም ያንሳል፡፡ የዘመቻው ትኩረትም ከከረን ከተማ በስተሰሜን ያለችው “ሐልሐል” የተሰኘች ስትራቲጂካዊ መንደር ነበረች (“ሐልሐል” በ1969 የጀብሃ እውቅ ኮማንደር የነበረው ዑመር እዛዝ የሞተባት መንደር ናት)፡፡ በዘመቻው የአብዮታዊ ሰራዊት ሀይሎች የሻዕቢያ ተዋጊዎችን አሸንፈው ለማባረር ችለዋል፡፡ ሆኖም በሻዕቢያ ላይ የደረሰው ሽንፈት የአማጺውን ቅስም ለመስበር የሚችል አልነበረም፡፡

በ1984 የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራዊት በታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ቁጥር ጨምሮ ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት መታወጁ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ዙር ዘማቾች በጥር ወር 1984 ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያ ገብተዋል፡፡ ታዲያ ሻዕቢያም አልሰነፈም፡፡ መከላከልንና ማጥቃትን እያፈራረቀ የመንግሥት ሰራዊትን አስጨንቆ ይዞአል፡፡ ይባስ ብሎም የአብዮታዊ ሰራዊት አዛዦች ባልጠበቁት መንገድ የውጊያ ቀጣናውን ፊት ወደማይታወቅበት የምዕራብ ኤርትራ ቆላማ መሬት አስፋፍቷል (በቀድሞ ጊዜ በዚህ ግንባር ጀብሃ እንጂ ሻዕቢያ ተዋግቶ አያውቅም)፡፡ በተለይም በሱዳንና ኤርትራ ድንበር ላይ የምትገኘውን የተሰነይ ከተማን በመቆጣጠር የመንግሥት ሀይሎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት ከተማዋን በአውሮፕላን ደጋግሞ ቢደበድባትም ከሻዕቢያ ሊያስለቅቃት አልቻለም፡፡ እንዲያውም በአንደኛው ድብደባ ላይ ከፍተኛ የአብራሪነት ልምድ ያካበቱትና በሰሜን አሜሪካ (አሪዞና ስቴት) የሰለጠኑት እውቁ አብራሪ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በሻዕቢያ አየር መቃወሚያ ተመትተው ለመማረክ በቅተዋል (እኝህ ኮሎኔል በሻዕቢያ እጅ ለስድስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደርግ መንግሥት ከስልጣን ሲወገድ በምህረት ተለቀዋል፤ በ1998 የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲቀሰቀስ እንደገና ዘምተው በአየር ላይ በመመታታቸው በሻዕቢያ ተማርከዋል)፡፡ በሌላ በኩል በሀምሌ ወር 1984 ሻዕቢያ የጋሽና ሰቲት አውራጃ ዋና ከተማ የነበረችውን ባሬንቱን በመቆጣጠሩ ምዕራባዊው የኤርትራ ክፍል በአብዛኛው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር፡፡

ሻዕቢያ ምዕራብ ኤርትራን በመቆጣጠሩ በሱዳን ካሉት ደጋፊዎቹና ኤርትራዊያን ስደተኞች ጋር እንደ ልብ የሚገናኝበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ በተለይ የኤርትራ እርዳታ ማህበር (Eritrean Relief Association-ERA) የተሰኘው ድርጅት ሻዕቢያ በሚቆጣጠራቸው ክልሎች ለሚኖሩትና በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እንዳሻው እርዳታ ማቅረብ የቻለው በተሰነይ በኩል ወደ ሱዳን የሚዘልቀው ጎዳና በሻዕቢያ ቁጥጥር ስር ስለዋለ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ERA ለእርዳታ አቅርቦቱ የሚጠቀመው ከፖርት ሱዳን ወደ ሰሜናዊ ኤርትራ የሚያመራውን ረጅም ጎዳና ነው (እንደሚባለው ከሆነ የደርግ ሀይሎች ለኤርትራዊያን ዜጎች እርዳታ እንዳይደርስ አግደው ቆይተዋል፤እርዳታው በERA በኩል እንዲደርስ የተፈለገው ለዚህ ነው)፡፡

====ዘመቻ ባህረ-ነጋሽ====

አብዮታዊው ሰራዊት ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ ለማባረር በቂ ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሐምሌ ወር 1984 ለመልሶ ማጥቃት ተዘጋጀ፡፡ በአንደኛው ዙር የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የተመለመሉ 60 ሺህ ዘማቾችን ጨምሮ ከመቶ ሀምሳ ሺህ የማያንስ የጦር ሰራዊት ለውጊያው ተሰለፈ፡፡ የዘመቻው ፕላን በሶቭየት ህብረት (USSR) ወታደራዊ ኤክስፐርቶች ተዘጋጀ፡፡ ከሶስት መቶ የማያንሱ ታንኮችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ ሆኑ፡፡ ዘመቻውም “ባህረ ነጋሽ” ተብሎ ተሰየመ፡፡

“ዘመቻ ባህረ ነጋሽ” ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ አባርሮ ወደ ሳሕል በረሃ የመመለስ እቅድ ነበረው፡፡ የዘመቻው እቅድ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ ባይታወጅም እንኳ ለዘመቻ በተሰለፈው የሰው ሀይልና በተመደበለት የጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት ከቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ጋር ይስተካከላል፡፡ ሀገሪቷ የነበሯት ምርጥ የጦር መኮንኖችም በአዛዥነት ተሰልፈዋል፡፡ የዘመቻው የበላይ አዛዥ እውቁ የጦር ሰው ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ሲሆኑ በርሳቸው ስር ሜ/ጄ/ ደምሴ ቡልቶ፣ ሜ/ጄ/ አበራ አበበና ሜ/ጄ/ ረጋሳ ጅማ ተሰልፈው ነበር፡፡ የአየር ሀይሉ ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይም ከምርጥ አብራሪዎች ጋር ተሰልፈዋል፡፡

ዘመቻው በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት በሰኔ ወር 1985 ተጀመረ፡፡ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት በከፍተኛ ወኔ ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ እያባረረ በድል ገሰገሰ፡፡ ሻዕቢያ በታሪኩ አይቶት የማያውቅ ሀያል ሰራዊት ገጠመው፡፡ ከ2000 እስከ 4000 የሚሆን ተዋጊ አለቀበት፡፡ በዚህም የተነሳ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ባሬንቱና ተሰነይን ለመልቀቅ ተገደደ፡፡ ለአስራ ስምንት ወራት የገነባው መከላከያ ስላልሰራለት በስልታዊ ማፈግፈግ ስም ወደ ሳህል በረሃ መሸሽ ግድ ሆነበት፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ማንንም ባስደነቀ ፍጥነት እየተጓዘ ከናቅፋ በር ላይ በድጋሚ ደረሰ፡፡ ሆኖም በዚህኛውም ጊዜ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ውጊያውን እንዲያቆም ታዘዘ፡፡

የዘመቻ ባህረ ነጋሽ አፈጻጸም ሲገመገም ውጤቱ ጥሩ ሆኖ በመገኘቱ ሊቀመንበር መንግሥቱ ቀጣይ ዘመቻዎችንም በተመሳሳይ ስልት ለማካሄድ ከውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጎአቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዘመቻው ከፍተኛ የሰው ሀይል መስዋእት ሆኖአል፡፡ በተለይ ከአስር ሺህ የማያንሱ የአንደኛው ዙር ብሄራዊ ውትድርና ዘማቾች አልቀውበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያዊያን የጦር አዛዦች ልብ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ጄኔራል ፋንታ በላይ እንደተናገሩት ሊቀመንበር መንግሥቱን ከአመራር ለማስወገድ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ማውጠንጠን የጀመሩት በዘመቻ ባህረ ነጋሽ ወቅት የተከሰተውን የወገን ጦር እልቂት ካዩ በኋላ ነው፡፡ ጄኔራል ፋንታ ሁኔታውን ሲገልጹት እንዲህ ብለው ነበር፡፡

“ሊቀመንበር መንግሥቱ እኛ ያዘጋጀነውን የውጊያ እቅድ ትተው የኛን ወታደሮች እንደ ጭራሮ በሚቆጥሩት የሶቪየት አዛዦች የተዘጋጀውን የውጊያ እቅድ በመቀበል ከፍተኛ መስዋእትነት እንድንከፍል አስደረጉን፤ መስዋዕትነት መክፈላችን ካልቀረም ውጊያውን በጀመርንበት ፍጥነት መቀጠል ሲገባን አለምንም ምክንያት እንድናቆም አዘዙን” (ዘነበ ፈለቀ፣ ነበር ቁጥር ሁለት፣ 2001፣ ገጽ 221)

፠፠፠፠፠፠


ከዘመቻ ባህረ ነጋሽ ፍጻሜ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት በኤርትራ ምድር የሚደረገው ውጊያ ጋብ ብሏል፡፡ በነዚያ ዓመታት ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች አጣዳፊ ለሚሏቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የደርግ መንግሥት የመንደር ምስረታ እና ህገ-መንግሥት ማርቀቅን ለመሳሰሉ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ በነርሱ ላይ አተኩሯል፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ሁለተኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ በማዘጋጀቱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡


ደርግ ያረቀቀው ህገ-መንግሥት በነሐሴ ወር 1979 ጸደቀ፡፡ ኢህዲሪ (የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ተመሰረተ፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ በብሄራዊ ሸንጎ ምርጫ “ፕሬዚዳንት” ሆኑ፡፡ አዲሱ ህገ-መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለኤርትራ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሔ እንደሚሰጠውም ተገለጸ፡፡ ሆኖም ቃል የተገባው ሁሉ የጉባኤ ላይ ልፈፋ ሆኖ ቀረ፡፡ የጦርነት አማራጭ የመንግሥቱ ብቸኛ ምርጫ መሆኑ ሳይውል ሳያድር ታወቀ፡፡ ሆኖም የደርግ አካሄድ የሚያዛልቅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከደርግ ይልቅ መንገዱ ቀና ሆኖ የተገኘው በሚያዚያ 1987 ባካሄደው ጉባኤ ኢሳያስ አፈወርቂን በዋና ጸሓፊነት ለሰየመው ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ነው፡፡ ለሳላሳ ዓመታት በዓላና ናቅፋ በረሃዎች ሲፋለሙ የቆዩት የኤርትራ አማጺያን ለመጨረሻው ግብ የሚያበቃቸውን ወታደራዊ ስልት በተግባር ላይ የሚያውሉበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፡፡ ቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም የኢትዮጵያና ኤርትራን የታሪክ አቅጣጫ ከመሰረቱ የቀየሩ ታላላቅ ፍልሚያዎች የተካሄዱባቸው ነበሩ፡፡ እነዚያ ታላላቅ ፍልሚያዎች ምን ይመስላሉ? በሚቀጥለው ክፍል እናያቸዋለን፡፡

(ይቀጥላል)

ምንጮች
1. Dawit Wolde-Giorgis, “Red Tears”: Famine, War and Revolution in Ethiopia, Red Sea Press, New York 1989
2. David Lamb, “Evil Days: Thirty Years of War and Famine in Ethiopia (1961-1991), Africa Watch Group, New York, 1991
3. Paul B. Henze, “Eritrea’s War”, Shama Books, Addis Ababa, 2002
4. ገነት አየለ፣ “የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች”፣ አዲስ አበባ፣ 1994
5. ገነት አየለ፣ “የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች-ቁጥር ሁለት”፣ አዲስ አበባ፣ 2003
6. ጌታቸው ሀይሉ፡ “ቀያይ ተራሮች”፣ አዲስ አበባ፣ 1993
7. ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፣ “አይ ምጽዋ”፣ አዲስ አበባ፤ 1997
8. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ አዲስ አበባ፣ 1996
9. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር-2”፣ አዲስ አበባ፣ 2001
10. ጌታቸው የሮም፣ “ፍረጂ ኢትዮጵያ”፣ አዲስ አበባ፣ 1993

 
 

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events