Dehai News

ሳተናው / ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመሸምገል አሜሪካ ቁርጠኛ ናት - በኢትዮጵያ እየተከሰቱ የሚገኙ የፀጥታ ችግሮች ኢኮኖሚያዊ መነሻዎች አሉዋቸው

Posted by: Semere Asmelash

Date: Thursday, 16 November 2017


አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ በኢትዮጵያ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ኢኮኖሚያዊ መነሻ አላቸው አሉ

By ሳተናውNovember 16, 2017 

የቀድሞው የኢትዮጵያና የኤርትራ አምባሳደርና አሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ኃላፊ ዶናልድ ያማማቶ
ብርሃኑ ፈቃደ
  • ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመሸምገል አሜሪካ ቁርጠኛ ናት ብለዋል
የቀድሞው የኢትዮጵያና የኤርትራ አምባሳደር፣ የአሁኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ኃላፊ ዶናልድ ያማማቶ፣ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ የሚገኙ የፀጥታ ችግሮች ኢኮኖሚያዊ መነሻዎች አሉዋቸው አሉ፡፡ አገሪቱ ከሶማሊያ የሚቃጣባት የሽብር አደጋም አሳሳቢ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ያማማቶ ሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በስልክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች በሪፖርተር ተጠይቀው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ስለሚታዩ ችግሮች ሲያብራሩም፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በአገሪቱ የፀጥታ ችግሮች ላይ አሜሪካ አብራ እየሠራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች ከመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣ ከሥራ አጥነትና ከኢኖሚያዊ ዕድሎች አኳያም እንደሚታዩ አስረድተዋል፡፡ በተለይ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የገጠማቸው ፈተና ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተማረና ብርቱ የወጣት ኃይል በብዛት የሚገኝባት አገር በመሆኗ፣ ይህንን የኅብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ ብሎም ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ለመንግሥት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአገሪቱ በሚታየው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በተለይም የጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን የተመለከቱ የዴሞክራሲ መብት ጥያቄዎችን በተመለከቱ ጉዳዮች፣ በትግራይና በኦሮሞ ብሔሮች፣ እንዲሁም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ሆነ ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር አሜሪካ ስትወያይ መቆየቷን አምባሳደር ያማማቶ አስታውቀዋል፡፡ 
የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይን በተመለከተ አሜሪካ ሁለቱን አገሮች ለማነጋገርና ለማስማማት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በውኃ ችግር ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ቀድሞ በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት የሚችሉ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት በአንድ አንድ ጊዜ እንኳ ለማምረት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሐረር ያሉ በዓለም ተወዳጅ የሆነ የልዩ ጣዕም ቡና አምራች አካባቢዎች ወደ ጫት ምርት እያተኮሩ መምጣታቸውን አሜሪካ እንደምትገነዘብ አብራርተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በተለይም በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥዋል፡፡ በወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሚመራው አካል፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙትን የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ አንጃ የሚመሩት የቀድሞውን የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻርን እንዳነጋገሩ ዶናልድ ያማማቶ አስታውሰው፣ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ግን ጊዜው አይደለም ብለዋል፡፡
በኒጀር በቅርቡ የተከሰተው የአሜሪካ ወታደሮች ግድያም ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ በኒጀር ለወታደራዊ ሥልጠና በተመደቡ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስለተገደሉ ወታደሮች መንግሥታቸው በማጣራት ላይ እንደሚገኝና ምርመራው በመካሄድ ላይ በመሆኑም ማብራሪያ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ባሉ የፀጥታና የደኅንነት፣ የፖለቲካና መልካም አስተዳደር፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ለመምከር በየዓመቱ በሚጠራው የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የምክክር መድረክና የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ የአሜሪካ ውጭ ሚኒስትር  ሬክስ ቲለርሰን ለ37 አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ግብዣ ማቅረባቸውን አምባሳደር ያማማቶ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 37 አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በመላክ ከሐሙስ ኅዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ስብሰባ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
ከአሜሪካ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክና የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ኦፊሰሮች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅት ቃል የተገባባቸው እንደ ፓወር አፍሪካ፣ ትሬድ አፍሪካ ያሉትን ጨምሮ አሜሪካ በሕግ ያፀደቀችው ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን እንደሚቀጥሉ ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡ ከሰሞኑ ስብሰባም አዳዲስ አፍሪካን የተመለከቱ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕቅዶች በአሜሪካ መንግሥት ይፋ ሊደረጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
ሪፖርተር



7ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 7 - ERi-TV Documentary

Dehai Events