Dehai News

Dahabshiil long banner 728x90
Eritrea for mobile viewing

Goolgule.com: ኃይለማርያም ከየት ይለቃል? ያልነበረ “ፓርላማ” ወዴት ይበተናል?

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 28 December 2017

ኃይለማርያም ከየት ይለቃል? ያልነበረ “ፓርላማ” ወዴት ይበተናል?

 

ከወራት በፊት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያስገባውን አባዱላ ገመዳ የኢህአዴግ ሥራአስፈጻሚ ጥያቄውን አጽድቆለታል ተብሏል። ከዚህ ጋር ተከትሎ በቀጣይ ኃይለማርያም ከ“ሥልጣን” ይወርዳል የሚለው ጉዳይ በስፋት በሁሉም ዓይነት ሚዲያ እየተስተጋባ ነው።

በተያያዘ ወሬ አዲስ አበባ ላይ ያለውና ሰሞኑን በመጠኑ ሥራውን መሥራት የጀመረውን “ፓርላማ” ህወሓት ሊበትነው እያቀደ ነው የሚል መረጃ ተሰምቷል። ከዚህ በተጨማሪም ከትግራይና ሌሎች ታማኝ ክልል/ሎች በስተቀር በክልል የሚገኙ ምክርቤቶችን በሙሉ ህወሓት ሊበትናቸው አሢሯል የሚል መረጃ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እየተሰማ ነው።

ከገቢ አንጻር የሰበር ዜና ልክፍት የተጠናወተው ሚዲያ ይህ መሰሉን “መረጃ” ሲያስተላልፍ ከመረጃው ጋር ሕዝብ ማወቅ ያለበት ምንድነው የሚለውን ኃላፊነት የዘነጋው ይመስላል። ኃይለማርያም ደሳለኝ በሟቹ መለስ ተመልምሎ ወደ ሥልጣን መንበር ከቀረበ በኋላ በመለሳዊነት ለመጠመቅ እየተማረ ባለበት ጊዜ ነው “መምህሩ”ን ሞት የቀደመው። መጽሐፉ ተከፍቶ፣ የተጀመረው ምዕራፍ ሳይጠናቀቅ መለስ በማምለጡ ኃይለማርያም እዚያው የተከፈተ ገጽ ላይ ነው ያለው። ለዚህም ይመስላል እንደ ሃይማኖተኛነቱ ለፈጣሪው ዘላለማዊ ክብር መስጠት ሲገባው ለመለስ “ዘላለማዊ ክብር” ሲሰጥ እስካሁን የቆየው።

“ግምገማ!” በተባለው ኢህአዴግ በሚያካሂደው የስድብ ሃይማኖት፤ በተደጋጋሚ ከመስመር የወጡ ከፍተኛ የንቀት ንግግሮች ሲሰነዘሩበት የኖረው ኃይለማርያም ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው ግምገማ፤ “ብቃት የለህም” ተብሎ አሁን በዝግ እየተካሄደ ባለ ዓይነት ስብሰባ ላይ ተሰድቧል። እርሱም በምላሹ፤ መጽሐፍ ማንበብ አልወድም፤ ዕቅድ ማዘጋጀት አልችልበትም፤ ለውጥ ማድረግ ያቅተኛል፤ … በማለት ውንጀላውን አምኗል።

በዚህ ዓይነት የውርደት ህይወት የሌለውን ሥልጣን ይዞ የቆየ ሰው ከሌለው ሥልጣን ላይ ይወርዳል ብሎ በዘገባነት ማጠናቀር ህወሓትን እንደ ኅብረብሔራዊ ድርጅት ቆጥሮ ሥልጣኑን በሐቅ አጋርቷ ብሎ ከማመን ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ህወሓት ኃይለማርያምን ለማንሳት ቢሞክር ወይም ቢያስነሳው አሁን ባለው የፖለቲካ ሂደት ላይ የሚያመጣው ፋይዳ የበረታ አይመስለንም። ምናልባት በደኢህዴን ውስጥ ያለው ተገዢነት በተለይ የኃይለማርያም “መዘምራን” ላይ መጠነኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችል ይሆናል። ኃይለማርያም ገና ከጅምሩ አገሪቱ (እንደ ማኅበር) በኅበረት አስተዳደር (“ኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ”) ትመራለች በማለት ጠ/ሚሩ ይዞት የነበረውን ሥልጣን ሁሉ በክላስተር ሸንሽኖ ራሱን ሥልጣን አልባ አድርጎ የተቀመጠ ነው። አሁን ከሌለው ሥልጣን ሊወርድ የሚችልበት ምክንያት አይታየንም።

ሥልጣን አልባው “ፓርላማ”ም ሆነ የክልል ምክርቤቶች የተባሉት ከሌላቸው የሕዝብ ተወካይነትም ሆነ “ሥልጣን” በህወሓት ይበተናሉ ማለት በፊት ህወሓት በአሳታፊ ፖለቲካ ያምናል፤ የሕዝብ ውክልና በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ነበር ብሎ ካድሬያዊ ዲስኩር ከመስጠት የተለየ አይሆንም። አተነፋፈሱ ብቻ ሳይሆን ሳንባውም በህወሓት የተገጠመለት “ፓርላማ” ሰሞኑን መጠነኛ ጥያቄዎች ሲያቀርብ በመሰማቱ “ሰበር ዜና” መሆኑ ምን ያህል ነው ቁልቁል የወረድነው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው እንላለን። ሚዲያው እዚህ ላይ ቆም ብሎ ራሱን ወሬ ተኮር ነኝ፣ “ክሊክ” ተኮር ነኝ ወይስ አጀንዳ ተኮር ነኝ ብሎ እንዲጠይቅ ሳንጠቁም አናልፍም።

ስለዚህ የሚናገረው፣ የሚወስነው፣ የሚያስበው እየተመጠነ፣ እየተሰፈረ ሲሰጠው የነበረው ኃይለማርያም “ከሥልጣን ይወርዳል” ማለት ህወሓትን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይመስለናል። ከሌሎች አገራት ፓርላማዎች ጋር በእኩል ስያሜ የመጠራት ብቃት የሌለው የኢህአዴግ ሸንጎ (ፓርላማ) እና የክልል ምክርቤቶች ይበተናል (“ዲዞልቭ” ይደረጋል) ማለት እንደ አገር የሌለንን አለን በማለት ለህወሓት/ኢህአዴግ ክብር መስጠት ነው።

ሕዝባዊው እንቅስቃሴ የህወሓት አፈና፣ ጥርነፋ አልበግረው ብሎ እዚህ ደርሷል። ከዚህ በፊት እንደዘገብነው የህወሓት የገጠር መዋቅር ፈርሷል ትውልድ አምጿል፤ በቃኝ ብሏል። ከዚህ በኋላ በድጋሚ የሚወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይሠራም። በጥልቅ መታደስ ያመጣው “ውጤት” በጥልቀት መበስበስ ነው። ከዚህ በኋላ ኃይለማርያም ከሌለው ሥልጣን ቢወርድ፣ “ፓርላማ”ው ቢበተን የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ስለዚህ ሚዲያው ከክሊክ ተኮርነት ወጣ ብሎ ከስሜትና ከምናባዊ አስተሳሰቡ ነቅቶ አጀንዳ የማስያዝ ሥራ ላይ ቢጠመድ ለአገር የሚበጅ ይመስለናል። ሕዝብ በቃኝ ብሏል፤ ትውልድ አምጿል!

Dm eri tv subscribe

ERi-TV, Eritrea: Year In Review - Main Diplomatic Achievements