Dehai News

Satenaw.com: ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት በሙሉ ድምጽ አጸደቀ ፤ የባድመንና የዛላንበዛን ቡሬን ቦታዎች ለኤርትራ ለመስጠት ተስማማ። (መግለጫው)

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Tuesday, 05 June 2018

 

ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት በሙሉ ድምጽ አጸደቀ ፤ የባድመንና የዛላንበዛን ቡሬን ቦታዎች ለኤርትራ ለመስጠት ተስማማ። ሕወሃት ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት በመቀሌ ወስኖ የመጣውን አጀንዳ በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ አጸድቆታል። መግለጫም ወጥቷል። ከመቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ወጣቶች የሞቱበትና ለኢትዮጵያ ተወስኗል ተብሎ የተነገረለት ባድመና የድንበር አከባቢዎች በሙሉ ለኤርትራ ይመለሳሉ። መግለጫውን ይዘናል።

ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
(የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት የተላለፈ ጥሪ)

Watch:

https://www.youtube.com/watch?v=2ku-cyF5Q1I

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሚከተለዉን ጥሪ አስተላልፏል።

ለኢትዮጵያችን እድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ ከግለሰብ የወደፊት የማደግና መለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም አይነት የልማትና የዲሞክራሲ አላማዎችን ማሳካት አይቻልም፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ የመኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መሃከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም ሃገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡ በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በድምሩ ላለፉት 20 አመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት ለህዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው፡፡ይህን ባለማድረጋችን በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዉናል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን፡፡ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን፡፡

በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል፡፡

ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን የሀገራችን ፖሊሲም አጠናክረን እንደምንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡

የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት
ግንቦት 28/2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤

 

 


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events