Dehai News

(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ኤርትራ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Monday, 09 July 2018

ኢትዮጵያና ኤርትራ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራረሙ



አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ወደ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚመልሱ ስምምነቶችን ተፈራረሙ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተለያዩ ስምምነቶችን በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

መሪዎቹ ሃገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባና አስመራ በመክፈት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር፣ የሃገራቱ አየር መንገዶች ወደ መዲናዎቻቸው እንዲበሩና የስልክ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲሁም የወደብ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነትን በፊርማቸው አፅድቀዋል።

የስምምነቶች መፈረምም በሃገራቱ መካከል የጥላቻን በር በመዝጋት አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አስመራ መግባታቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና እና የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት ለክብራቸው የእራት ግብዣ አዘጋጅተው ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሠላምና ልማት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በፍቅር ፈርሷል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀዋል።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events