Dehai News

Dahabshiil long banner 728x90
Eritrea for mobile viewing

(ንአምን ዘለቀ) ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የወደፊት ግንኙነት በጎ የሰነቁ ህልሞች አሸናፊ ሆነዋል

Posted by: Semere Asmelash

Date: Monday, 09 July 2018

ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የወደፊት ግንኙነት በጎ የሰነቁ ህልሞች አሸናፊ ሆነዋል (ንአምን ዘለቀ)

Posted by: ecadforum July 9, 2018

በንአምን ዘለቀ *
Eritrean ladies wearing T-shirt PM Abiy Ahmed's picture on it.

አስመራ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰለ ኤርትራ ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ራእይ በአደባባይ የተናገሩት ከ3 ወር በፊት የጠ/ሚኒስትርነቱን ስልጣን በተረከቡ ጊዜ ባደረጉት ንግግር መሆኑን አስታውሳለሁ። ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የኤርትራን ልኡክ ሲቀበሉ፣ ዛሬ ደግሞ ወደ አስመራ በመጓዝ የጀመሩት ተግባራዊ መንገድ ላለፉት አመታት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ብዙ የለፉበት፣ የደከሙበት ጉዳይ ነው። በህወሓቶች፣ እንዲሁም በማወቅና ባለማወቅ ይህን መልካም ራእይ ለማጠልሸት በተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ቡድኖች በሚደርስባቸው ውርጅብኝ ሳይበገሩ እነዚህ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በየአደባባዩ የተናገሩበት፣ የጻፉበት መልካም ራእይ ተግባራዊ ያደረገ እርምጃ በመሆኑ ከፍተኛ እርካታ የሚሰጥ ነው።

የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ግንኙነት አዲስ ጎዳና ተጀምሮአል፣ ዛሬ የሁለቱ ህዝቦች አዲስ የታሪክ ምእራፍ የጅማሮ ሁለተኛ ገጽ ገልጠናል። ዛሬ ልዩና ታላቅ፣ የወደፊት ትውልዶች በታሪክ ማህደሮች ሆነ በልብ ወለድ ድርሰቶች ጭምር የሚያነቡት፣የሚያከብሩትም ሊሆን የሚችል እለት ነው። በሁለት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ያየናቸው ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖችን ለማየት መብቃት በራሱ ታላቅ ጸጋ ነው። ትልቅ ብስራት፣ ትልቅ ደስታ። እነዚህ ልዩና ታሪካዊ እለቶች እውን እንዲሆኑ ለደከማችሁ፣ ተስፋን ሰንቃችሁ የዛሬዋን ታሪካዊ ቀን ለናፈቃችሁ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ።

ዛሬ ላይ ለተደረሰበት ልዩ ቀን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ መስዋእትነት እነደከፈሉ ግልጽ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የሕወአት አገዛዝ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ገንብቶ የነበረው የጥላቻ ግንብ ለመናድ ብዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ብዙ አይነት ስራዎችን ሰርተዋል፣ ብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ውስጥ ታልፎአል። ልዩ ልዩ ህዝባዊ መድረኮች፣ የተለያዩ ምሁራዊ መድረኮችና ጥናቶች ተደርገዋል፣ ልዩ ልዩ ጽሁፎች በምሁራንና በአክቲቪስቶች ተጽፈው በድህረ ገጾች ለንባብ በቅተዋል። የኢሳት ጋዜጠኞች የኤርትራና የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያቀራርቡ ፕሮግራሞችን ሰርተዋል፣ ልዩ ልዩ ድረ ገጾችም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያጠነጠኑ መጻጽፍትን አስነብበዋል፣ አክቲቪስቶች፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችና አባላት ስለሁለቱ ህዝቦች የወደፊት የጋራ እድል፣ የጋራ እጣ ፈንታ መልካም ራእዮችን በየመድረኩ ተናግረዋል።

በመከባበር ላይ የተመሰረተ የወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት የእነዚህን የተለየ የዘመናት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊና፣ ስትራቴጂካዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ሰላም ከማረጋገጥ አልፎ ከፊታቸው የተደቀኑት፣ በወሳሰብ ላይ የሚገኙ አለም አቀፋዊና ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የተገናኙ የጂኦኤኮኖሚክ፣ በጂኦፓለቲካና ጂኦስትራቴጂክ ነባራዊ ሁኔታዎች (realities) ጋር ስጋቶችን በጋራ ለመቋቋም፣ ከእነዚህ ሚመነጩ የጋራ መልካም እድሎችን ደግሞ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጥቅም፣ የጋራ ብልጽግና፣ የጋራ ደህንነት፣ ጠ/ም አብይ ዛሬ በአስመራ በቤተ መንግስት እንደተናገሩት “የላቀ ትስስር” ወይንም የኤርትራ ፕሬዝደንት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት “ዝ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” (the sky is the limit) ኣንዳሉት ሁሉ በጋራ የሚቋደሱበትን/የሚጋሩበት ሁኔታ የሚያበስር አዲስ የታሪክ ምእራፍ ነው።

ሌላም ሌላም ብዙ ማለት ቢቻልም ሄዶ ሄዶ ዛሬ ላይ ለተደረሰው ውጤት እንዲመጣ በጎ ያለሙና የሰነቁ ህልሞችና ሃሳቦች አቸናፊ ለመሆን በቅተዋል። ባለፉት አመታት ያራመድናቸው ሃሳቦች፡ ራእይና ህልማችን እውን የመሆን ጅማሮውን ለማየት በቅተናል። ብዙ ስራ፣ ብዙ ትግልም ይቀራል። መተማመን፣ መከባብር፣ መተሳስብ፣ በሁለቱም ወገን የአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ የሚያሰላ የብልጣ ብልጥነት ስሌት ትላንት እንዳላዋጣ ተረድቶ ለወደፊቱ ግንኙነታችን ሩቅ አዳሪና ስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ከቅንነት ጋር መጋመድ ከተቻለ፣ በጣም ሩቅ ልንጓዝ እንችላለን። ለዘመናት የተሻገረ ልዩ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ህዝቦች፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ ሽርክና። ለዘመናት የሚዘልቅ።

Dm eri tv subscribe

HDRI Publishers: Book Release - ህያው ደብሪ A Book Hailed As A Game Changer in Eritrean Modern Poetry