አዲስ አበባ ፣ (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን ለቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ቻይና የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጉብኝታቸውን አጠናቀው አሰብ ገብተዋል።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰብ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሰብ ወደብንና ከአሰብ ወደብ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን 71 ኪሎ ሜትር መንገድ የጎበኙ ሲሆን፥ መንገዱ አገልግሎት ለመስጠት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገምግመዋል።
የአሰብ ወደብን በተመለከተም ወደቡ ላይ የተወሰኑ የማስተካከያ ስራዎች ከተከናወኑ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላም የምጽዋን ወደብ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለት ቀናት የኤርትራ ጉብኝታቸው ወደ አስመራ የሚያቀኑ ሲሆን፥ በቅርቡ ሁለቱ ሀገራት በገቡት ስምምነት አፈፃፀም ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።።
የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ከረጅም ጊዜ በኋላ በዛሬው ዕለት ምጽዋ ወደብ ላይ መልህቋን ትጥላለች ተብሎ ነው የሚጠበቀው።