Dehai News

(የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሚደረገውን የገቢና ወጪ ንግድ ለመቆጣጠር ህግ እየተረቀቀ ነው

Posted by: Semere Asmelash

Date: Saturday, 03 November 2018

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሚደረገውን የገቢና ወጪ ንግድ ለመቆጣጠር ህግ እየተረቀቀ ነው

አዲስ አበባ-በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ያለውን የገቢና ወጪ ንግድ ለመቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ነዳጅን ጨምሮ በተወሰኑ ዕቃዎች ላይ ገደብ እየተደረገ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል።

በአገሮቹ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት በሁለቱ መንግስታት በተደረሰ የሰላም ስምምነት መሰረት ድንበሮች ተከፍተው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጀምሯል።

በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ የገቢና ወጪ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር የገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ነው።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትንም ሆነ ወደ ኤርትራ የሚላኩትን ዕቃዎች ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ እየተረቀቀ ነው።

በዚህም ወደ አገር የሚገቡትም ሆነ ወደ ኤርትራ የሚላኩ ዕቃዎች ከሌሎች አገሮች ጋር እንደሚደረገው የንግድ ልውውጥ የቀረጥ ስርዓት ይዘረጋል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የህግ ማርቀቅ ሥራ እንደተጠናቀቀ በፍጥነት ወደ ተግባር ለመግባት በሚኒስቴሩ በኩል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብርሃቱ መለስ እንዳሉት አሰራር እስከሚዘረጋ ድረስ በድንበር በኩል የሰዓት እና የዕቃ ዓይነቶች ላይ ገደብ ተጥሏል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የንግድ ልውውጥ ስምምነት በመንግስታት ደረጃ ለማድረግ የሚያግዝ መረጃም በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከፌደራልና ከትግራይ ክልል መንግስት ተቋማት በተውጣጡ ሙያተኞች መረጃ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

የባለሙያዎቹን መረጃ መሰረት በማድረግ የድንበር ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።

ኢትዮጵያ የአሰብንና የምፅዋ ወደብን መጠቀም እንድትችል በሁለቱ መንግስታት መካከል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
https://www.ena.et/?p=24320#

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events