Dehai News

(አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት) በትግራይ ክልል አመራሮች በኩል የጦርነት ቅስቀሳና የሰራዊት ዝግጅቶች ካሉም በአስቸኳይ እንዲቆሙ የአማራ ክልል ምክርቤት በአጽንዖት መክሯል፡፡

Posted by: Semere Asmelash

Date: Thursday, 07 March 2019

በአማራና በትግራይ ወንድማማች ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ መልካም ግንኙነት ውስጥ ልዩነት በመፍጠር ወደ ጦርነት የሚያስገባ ጸብ አጫሪነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው የአማራ ክልል ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

በትግራይ ክልል አመራሮች በኩል የጦርነት ቅስቀሳና የሰራዊት ዝግጅቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የአማራ ክልል ምክርቤት በአጽንዖት መክሯል፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2011 ዓ.ም(አብመድ) የምክር ቤቱ 5ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ከየካቲት 26 እስከ 29/2011 ዓ.ም እየተካሄደ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ የወሰናቸውን ዐበይት ጉዳዮች በተመለከተ የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው እንደተመላከተው ከትግራይ ክልል ጋር እየተፈጠረ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ምክር ቤቱ በዝርዝር ገምግሟል፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች በታሪክ፣ በባህል፣ በኃይማኖትና ሀገርን በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ እንዳላቸው ምክር ቤቱ መገምገሙን አቶ አሰማኸኝ አመላክተዋል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት፣ ጸብም ሆነ መቃቃር እንደሌለና አብረው የኖሩና የሚኖሩ መሆናቸውን ምክር ቤቱ በአጽንዖት መገምገሙንም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቦቹ ጥረው ግረውና ለፍተው የሚያድሩ፣ ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነታቸው ወደፊትም የሚዘልቅ መሆኑን እምነት እንዳለው ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያሉት አቶ አሰማኸኝ፡፡

በአማራና በትግራይ ወንድማማች ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ መልካም ግንኙነት ውስጥ ልዩነት በመፍጠር ወደ ግጭትና ጦርነት እንዲገቡ የሚደረግ ማንኛውም ትንኮሳ፣ ማንኛውም ጸብ አጫሪነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው ምክር ቤቱ መወሰኑንም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር አንዳንድ አካላት የሚያሳዩት ድርጊት በምክር ቤቱ ተቀባይነት እንደሌለውም ተገምግሟል፡፡ ከትግራይ ክልል አመራሮች በኩል የጦርነት ቅስቀሳዎች፣ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት፣ ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ሰራዊት የማቅረብ እና አንዳንድ ፀብ አጫሪ አካሄዶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፤ ከዚህ ድርጊታቸውም እንዲታቀቡ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

በትግራይ ክልል የመሸገው፣ በተለይ በለውጡ የተገፋው፣ ስልጣኑን ያጣው፣ ዘራፊው ቡድን፣ ጦርነት ለመቀስቀስ ቢፈልግ እንኳ ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሎ ይመለከተዋል የሚል እምነት እንደሌለው ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው፡፡ 
ከእርስ በርስ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም ያለው ምክር ቤቱ የትግራይ ሕዝብ ለመሸጉትና ሕዝብን መከታ አድርገው ለሚንቀሳቀሱት ጥሪና ትንኮሳ ምንም አይነት መልስ ባለመስጠት ሰላም ወዳድነቱን በተግባር እንዲያስመሰክር ምክር ቤቱ ማሳሰቡን አቶ አሰማኸኝ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በኩልም ግጭት ከሚፈጥሩ ትንኮሳዎችና የትግራይ ሕዝብን ስጋት ላይ ከሚጥሉ ፀብ አጫሪ ንግግሮች ማንኛውም አካል እንዲቆጠብ፣ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች ለሰላም ፈላጊው የአማራ ሕዝብ እንደማይመጥኑትና ይህን በሚያደርጉ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ምክር ቤቱ መወሰኑም ተመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ሰላም ለመጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የአማራን ሕዝብ ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ






EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events