Dehai News

ጉድ ሳይሰማ መስከረም ኣይጠባም

Posted by: Brhane Woldu

Date: Tuesday, 04 May 2021

መስከረም ለመጥባት ጉድ መስማትን ልማዱ ኣደረገው እንበል። መስከረም ከመጥባቱ በፊት ከሰማነው ጉድ ኣንዱ ዲና ሙፍቲ ስለ ኤርትራውያን የተናገሩት ዐይን ያወጣ ውሸት ነው። “እያንዳንዱ ኤርትራዊ ዜጋ” ኣሉ ኣጅሬው ዲና “እያንዳንዱ ኤርትራዊ ዜጋ ኤርትራ ነጻነትዋን በማግኘቷ ደስተኛ ኣይደለም! የኤርትራን የነጻነት ቀን ለማክበርም ኣይፈልግም፤” ኣሉና ኣረፉት፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባነት ለረጅም ዓመታት የሰሩና ዛሬ ደግሞ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ቃል ኣቀባይ ሆነው ሳለ በኣቅራቢያቸው ስለሚገኘው የኤርትራ ሕዝብ ሓቁን የማያውቁት ሆነው ነው? ወይስ ሓቁን እያወቁት ለመዋሸት? መዋሸቱስ ለምን ዓላማ? ማንን ለማስደሰት? ማንንስ ለማሳዘን? ሁሉም ግን የሚያስተዛዝብ ነው። “ትልቅ ሰው “ተበላሽቶ ቅራሬ እንኳ ሳይሆን ሲቀር ምነው ኣያስተዛዝብ! ያም ሆነ ይህ ሰውየው ዳግመኛ እንዳይቀሉ እነሆ ሓቁን ይጎንጩት ።

ለኤርትራውያን ከሁሉም በዓላት በላይ ትልቁን ቦታ የሚይዘው፥ ኤርትራ ነጻነትዋን ያገኘችበት እኤኣ ግንቦት 24 ወይም ብግእዝ ኣቆጣጠር ግንቦት 16 ቀን ነው። የኤርትራ ሕዝብ ለረጅም ዓመታት መራራ ትግል ኣካሂዶ፥ ጎልያድን የመሳሰሉ ጠላቶቹን ከነኣይዞህ ባዮቻቸው ተናንቆ በማሸነፍ ነጻነቱን የተጎናጸፈበት ዕለት ስለሆነ። ይህንን ዕለት ለማክበርም በየውጭ ሃገሩ የሚኖረው ኤርትራዊ ሳይቀር በየዐመቱ በኣእላፍ ወደኤርትራ ይተማል። በርካቶች ከሩቅ ሃገራት ከኣመሪካ ከኣውስትራልያ ወዘተ የመጓጓዣና ለሌሎች ወጭዎቻቸው በሺ የሚቆጠር ዶላር ከፍለው ግንቦት 24ን ኣክብረው በነጋታው ወደ መጡበት የሚመለሱ በርካታ ኤርትራውያን መኖራቸው ፡ ብዙ ታዛቢዎች የሚደነቁበትና ኤርትራዊ ምን ያህል ለነጻነቱ ቀናኤ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ምናልባት በተለያየ ምክንያት ወደኤርትራ ለመምጣት ያልቻሉ ኤርትራውያን በያሉባቸው ሃገራት የኤርትራን የነጻነት ቀን ግንቦት 24ን በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል። ዲና ሙፍቲ የወያነ ኣምባሳደር ሆነው ባገለገሉባቸው ሃገራት በነበሩበት ወቅት ይህንን ኣይውቁም ኖሯል? ብለን ብንጠይቅና ፥  በታላቅ ውሸትነት በተመዘገበው ኣባባሎ ተገርመን፥ “ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ!” ብንልስ እንደመዳፈር ይቆጠርብን ይሆን? ?

ሌላው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየሰማነው ያለነው ጉድ ደግሞ “የምረጡኝ ቅስቀሳ” በማካሄድ ላይ ያሉ ኣንዳንድ  “የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ነን” ባዮች ስለ “ባሕር በር” የሚያሰሙት ድንፋታ ነው። መቸም የኣፍሪካ ዲሞክራሲ ኮሜዲ ወይ ትራጀዲ ወይም ሁለቱም የሚስተናገድበት ተውኔት ነው። ይህ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ተውኔትም ሁለቱን የያዘ ሆኖ ኣግኝተነዋል። “መርጣችሁ ኣራት ኪሎ ኣጼቤተመንግስት ካስገባችሁን የባሕር በር ባለቤት እናደርጋችኋለን” የሚለው ከመድረክ የማያልፍ የሽሮ ድንፋታ የኮረኮሩንን ያህል ሲያስቀን፥ ኢትዮጵያ ከንደዚህ ዓይነቶቹ ሓቅን ማየት የማይችሉ፥ ከሰላም ይልቅ ሁሌም ጦርነትን የሚመኙ ተስፋፊዎችና ኣሜኬላዎች የሚፈጠሩባትና  የሚበቅሉባት መከረኛ ሃገር መሆኗን ስናስብ ደግሞ ሳያሳዝነን ኣልቀረም።

እነዚህ የለብለብ ፖለቲከኞች ይህንን እርኩስ ምኞታቸውንና የዛገ ፍላጎታቸውን መድረክ ላይ ከማውጣታቸው በፊት “በባሕር በር” ስም ኣጤ ሃይለ ስላሴ፥ ደርግና ወያኔም ጭምር ከሰላም ይልቅ ጦርነትን በመምረጣቸው ኢትዮጵያ በከንቱ የከፈለችውን ሰብዓዊና ማቴርያላዊ ዋጋ መለስ ብለው ኣይተውታል ወይ? ይህ በኣስከፊነቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የተመዘገበ፥ ሃገሪቷንም ተፈጥሮ ጸጋውን ሳይነፍጋት ሁሌም በረሃብና በኋላ ቀርነት እንድትዳክር  ያደረጋት ርካሽ ኣስተሳሰብ  ሆኖ  ሳለ ፥ እነዚህ ቅንጡ ፖለቲከኞች ሊደግሙት መመኘታቸው ጅልነት ነው ወይስ እብደት? በእነዚህ “ተምረናል” “ዲግሪ ሰቅለናል” በሚሉና ፥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሚኖሩ ይህ ኣስተሳሰብ ሲደግም ሁለቱም የነሱ ገላጭ ነው። ጅልነቱም እብደቱም።

ጎመን ጨማቂዋ ኢትዮጵያዊት እናት በንደነዚህ ዓይነቶቹ የተስፋፊነት በሽታ ኣንጎላቸውን ባነወዛቸው ጅሎችና እብዶች ሰበብ ልጆችዋን እስከ መቼ ነው እንድትገብር የሚፈረድባት። ዛሬም እንደትናንቱ “የዛሬን ተውልኝ እንጂ ከንግዲህ ኣልወልድም” ብላ ማሕጸኗን እንድትረግም ነወይ ፍላጎታቸው? ለወግ ለማእረግ በቅተው የወላጆቻቸ ጧሪ ቀባሪ መሆን የሚገባቸውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ለእልቂት ማጨትና በባሕር በር ስም ያለ እዳቸው እዳ ማሸከም ለምን ኣስፈለገ? ደግሞ የሰላሙ ኣማራጭ እያለ። ኣዎን በተለይ የኤርትራን ህዝብ መርቶ ለድል ያበቃውና ኤርትራን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በዓለም ኣቀፍ ሕግ መሰረትም የመሬቷን፥ የሰማይዋንና የባሕር በሮችዋን ልዑላውነት ያረጋገጠው  ሻዕቢያ (ህዝባዊ ግንባር) ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ ፡”የባህር በር ጉዳይ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ደም መፋሰስ ምክንያት መሆን የለበትም” የሚል ጽኑ ኣቋም በመያዝ ስለወደቦች ኣጠቃቀም ዘመኑ የሚፈቅደውን የሰልጠነ ኣቋሙን በተደጋጋሚ ሲይሳውቅና በተግባርም ሲይሳይ ቆይቷል።  

የኤርትራው ፕሬዚደንት ኣቶ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ባንድ ወቅት  የባሕር በርን በሚመለከት ተጠይቆ የሰጠውን መልስ  ያስታውሷል። እንጠቅሳለን፦

“እኤኣ በ1991 ዓ/ም ኤርትራ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ የምጽዋና የዓሰብ ወደቦች እንደድሮው ለኢትዮጵያ ኣገልግሎት መስጠታቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ ወደቦቻችንን በነጻ እንድትጠቀምበት የፈቀድነው፥ እንደ ኣንድ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ስትራተጂ ስለምናየው ነው። ኢትዮጵያ በዚያን ግዜ ትከፍለው የነበረ ቀረጥና የኣገልግሎት ክፍያ ስማዊ ነበር። ይህንንም እራሳቸው ኢትዮጵያውያን የሚመሰክሩት ሓቅ ነው። የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብለን ኢትዮጵያን በዶላር ማስከፈልን ኣስበነው ኣናውቅም። ይህንን ሁሉ እናደርግ የነበረው ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ስትራተጂካዊ እንጂ ታክቲካው ኣይደለም ከሚል እምነት በመነሳት ነው። ወያነ በኤርትራ ላይ ጦርነት ባወጀበትና  ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ባጋጠመበት ግዜ ሳይቀር፥ እርዳታ ሰጭዎች በዓሰብ ወደብ እርዳታ ለማስገባት ጥያቂ ባቀረቡበት ወቅት እኛ ኣልተቃወምንም። ምክንያቱም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን በወያነ ኣበሳ እንዲጎዱ ፍላጎቱ ስላልነበረን። ለሕዝብ ምንም ዓይነት ርህራሄ የሌለው ወያነ ግን ይህን ሃሳብ ኣልተቀበለውም። የወደቦችን ጉዳይ ከዓቅሙ በላይ እያሳደጉ ፖለቲካዊ መልክ ማስያዝ እርባና የለውም። ስለወደቦቹ ልኡላውነት ማውራት ደግሞ ሌላ ኣርእስት ነው። ወደቦችን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው ትብብር ግን ገደብ የለሽ ነው፤ “ የጥቅሱ መጨረሻ

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረው ወዳጅነትና ሰላም የወደቦቹን ኣጠቃቀም ብቻ ሳይሆን በብዙ መስኮች የሚደረጉ ትብብሮችን የሚያጎለብት ነው። ይህ በመከባበርና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት፥ ለሁለቱ ሃገራት ብቻ ሳይሆን፥ በቀጣይ ጦርነትና ቀውስ የሚናጠውን የኣፍሪካውን ቀንድ የሚያረጋጋ ብሎም ወደ ሰላም፥ የጋራ ብልጽግናና እድገት ጎዳና የሚመራ ነው።

በተከታታይ የኢትዮጵያ ገዥዎች የጦርነትና የተስፋፊነት ፖሊሲ ምክንያት ለእልቂትና ለውደመት ተዳርገው የቆዩትና  ለዓመታት በስጋት እንዲኖሩ  ተፈርዶባቸው የነበሩት የሁለቱ ሃገሮች ሕዝቦች፥ የሰላም ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ከኣጥናፍ እስከ እጥናፍ ወደ ኣደባባይ ወጥተው ያሳዩት ደስታና ድጋፍ  ምን ያህል ሰላም ጠምቷቸው  እንደነበር ማሳያ ነው።

ይህንን ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያለውን በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የወዳጅነትና የሰላም ግንኙነት መደገፍና ማጎልበት ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። ለህዝቦቻቸው ብልጽግናና ለሃገራቱ እድገት የማሰብና የመቆርቆር መታያና ማረጋገጫ ነው ቢባል ማጋነን ኣይደለም። “ከዚህ ውጭ ስልጣንና ሓይሉን ከሰጠኸን የባሕር በር ባለቤት እናደርግሃለን” ለሚለው የጥቂት ጀብደኞችና ሕልመኞች ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጆሮኣቸውን ያውሳሉ ይሁንታቸውን ይሰጣሉ ብሎ መጠበቅ በዚህ ጽሑፍ ደግመን ደጋግመን እንደገለጽነው ጅልነትም እብደትም ነው። በኤርትራ በኩል በተግባር የተረጋገጠው የሰላም ኣማራጭ እንደጸሃይ ደምቆ እየታየ ሳለ፥ ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ እንቅልፍ እንዳጡበት ጉዳይ በማቅረብ፥ “የባሕር በር” እያሉ መደንፋት በማንኛውም መመዘኛ ምክንያታዊ ሊሆን ኣይችልም።

ይህንን ስጋት ይልሆነውን ጉዳይ ቅምጥሎቹ እንጭጭ ፖለቲከኞች  እንደምርጫ ኣጀንዳ ማቅረባቸው፥ ለ30 ድፍን ዓመታት በወያኔ የተዘራው መርዝ ኢትዮጵያ ላይ የጋረጠውን ስጋት ለማየት እስከማይችሉበት ድረስ፥ የተጠናወታቸው የተስፋፊነት በሽታ ምን ያህል እውር እንዳደረጋቸው ማሳያ ነው።

Ø  ዛሬ በኢትዮጵያ የሃገር ፍቅር ወደ መንደርነት ፍቅር ዘቅጦ፥ በዚህ በሰለጠነ ዘመን  የገጀራ፥ የቆንጨራ፥ የመጥረቢያነ  የቀስት ፖለቲካ ይዘወተራል። በዚህም ሰበብ መተማመንና መደማመጥ ጠፍቶ ኢትዮጵያ ህዝቦችዋ እርስ በርሳቸው እየተፋለሱ በየቀኑ የንጹሓን ደም የሚፈስበትንና ሬሳ በገፍ የሚቆጠርበትን ትራጀዲ እያስተናገደች ነው። ኢትዮጵያ በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ፥ በሰላም ኣድሮ በሰላም መነሳት ለዓመታት እንደተለዩት ዘመድ የሚናፈቅባት፥ እንደኣገር መቀጠልዋና ኣለመቀጠልዋ ጥያቄ በሆነበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች።

 

Ø  ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት የተትረፈረፈባት ከራስዋ ኣልፋ ለሌሎችም የምትሆን ሃገር ናት። ቢሆንም ህዝቦችዋ ከድህነት፥ ከረሃብ፥ ከስራእጥነት ፥የውጭ እጅ ከማየትና ከሁሉም ዓይነት መከራና ስቃይ ሊገላገሉ ኣልቻሉም። ለዚህ ጠንቅ ከሆኑት ምክንያቶች ኣንዱና ወሳኙ ተከታታይ ገዝዎች - የተከተሉት የጦርነትና የመስፋፋት ፖሊሲ መሆኑ የሚያከራክር ኣይደለም። ይህንን ፖሊሲኣቸውን ለማራመድና ለማሳካት ደግሞ በተከታታይ ስልጣን የያዙት ገዝዎችዋ የሓያላን መንግስታት ታማኝ ኣገልጋዮች በመሆን ትከሻቸውን ለኣተላ ተሸካሚነት ኣመቻችተው፥ ኣካባቢውን በቀውስ ሲያምሱት ቆይተዋል።

 

Ø  ዛሬ ሓያላኑ ታማኝ ኣገልጋያቸው የነበረው ወያነ ባላሰቡት መንገድ ድባቅ ተመቶ ግብኣተ መሬቱ መፈጸሙ ስላስደነገጣቸውና፥ ተመቻችተው የሚጋልቡበት ኣገልጋይ የማግኘት ዕድል መንምኖ ስለታያቸው፥ የተለያየ ምክንያት በየእለቱ እየፈበረኩ እጅ ለመጠምዘዝ ሲውተረተሩ እየታዩ ነው።

ታዲያ  የኢትዮጵያ ሕዝቦችና  ደጉን ለማምጣት የሕይወት መስዋእትነት በመክፈል ላይ ያሉ ቁርጥ ልጆችዋ “የባሕር በር” እያሉ ከሚያላዝኑት ቀበጥ ፖለቲከኞች የሚጠብቁት  እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በሚመለከት ለሚነሱት ለሚከተሉት ጥያቄዎች ያላቸውን መልስ ነው። ከዚህ ውጭ በባሕር በር ቅዠታቸው የሚማልል ልብ፥ የሚያውሱት ጆሮም የላቸው።

v  በወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ተቋም ለበስ ሆኖ በየቦታው የተንሰራፋውን ዋልታ ረገጥ ኣስተሳሰብ ወደ መሃል ኣምጥቶ መተማመንን በመፍጠር ሕዝቦችዋ በሰላም፥ በወንድማማችነት የሚኖሩባት፥ ልዩነቶቻቸውን በውይይትና በመተሳሰብ የሚፈቱባት፥ ሰዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው ድህነትና የኢኮኖሚ ኋላቀርነት ተቀርፎ ለህዝቦችዋ ብቻ ሳይሆነ ለኣካባቢዋም የምትተርፍ ወዘተ ሃገር ሆና እንድትቀጥል፥ ግዜው የሚጠይቀውን ውድ ዋጋ ለመክፈል እነዚህ ቅንጡ ፖለቲከኞች ዝግጁ ናቸው ወይ? “ከላም ኣለኝ በሰማይ” በላይ የተሻገረ የሚጨበጥና የሚዘገን ፖሊስ ኣላቸው ወይ?

 

v  ዛሬ በተለይ ከወያኔ ውድቀት በኋላ ምዕራባውያን (ኣሜሪካና ተከታዮችዋ) ኣጅ ጠምዝዘው በኣካባቢያችን ቀውስን ፈጥሮ ቀውሱን መልሶ ለማስተዳደር ያላቸውን ዓላማ  ለማስቀጠል ሁሉንም ዓይነት የተጽእኖ  ሴራዎች በመሸረብ ላይ ናቸው፥ እነዚህን ሴራዎች ለመመከትና ለማክሸፍ፥ እንዲሁም የሃያላኑ የተለመደ ሎሌነትን ወጊድ ብለው ኢትዮጵያ የማንኛዎቹም ጉዳዮችዋ ብቸኛ ባላቤት የሆነችና ሙሉ የውሳኔ ነጻነት ያላት ሃገር እንድትሆን ለማድረግ ወኔውና ድፍረቱ ኣላቸው ወይ? በተለይ ይህንን ጥያቄ የምናነሳው “የባሕር በር” እያሉ የሚያላዝኑት ፖለቲከኞች ኣሜሪካኖችንና ምዕራባውያኑን “ኣትራቁን፥ ደግፉን” በማለት ሲለምኑና ሲማጸኑ በመስማታችን ነው።

እነዚህ ከፖለቲካ ኣቡጊዳ ያልደረሱ ፖለቲከኞች “የባሕር በር “ እያሉ ማላዘን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑን ተረድተውና፥ ዛሬ በኤርትራና በኢትዮጵያ መሃከል የተፈጠረውን ወዳጅነት መተሳሰብ በምንም ተኣምር ሊያቆሙት እንደማይችሉ ተገንዝበው ሰልፋችውን እንዲያሳምሩ እንመክራለን። ከዚህ ባለፈ “ኢትዮጵያ የፈለገችውን ትሁን ፥ የከፈለችውን ዋጋ ትክፍል ፥የባሕር በር ባለቤት ካልሆንን ሞተን እንገኛለን” የሚሉ ከሆነ፥ እንደዚህ ዓይነቱን የሽሮ ድንፋታ ብዙ ግዜ የሰማነው ስለሆነ መልሳችን ቀላል ነው። “እንኳን ለሙቅ ለገንፎም አንደነግጥ!!” የሚል።

ለኤርትራና ለኤትዮጵያ ሕዝቦች ሰላምና ብልጽግና!

ሰናይ ሳሙኤል


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events