Dehai News

Goolgule.com: “የነጭ ወያኔዎች” ሥልጣን መልቀቅና የተቀሩት “የዳግም ውልደት” ክህደት:: ህወሃት "ነጭ ወያኔዎችን" እያጣ ነው

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Sunday, 11 December 2016

“የነጭ ወያኔዎች” ሥልጣን መልቀቅና የተቀሩት “የዳግም ውልደት” ክህደት

ህወሃት "ነጭ ወያኔዎችን" እያጣ ነው
usaid-administrator-gayle-smith-is-welcomed-with-the-traditional-ethiopian-greeting-of-popcorn-rest-the-logo-on-the-truck-is-the-psnp-implementer-in-tigray
 

የህወሃትና የአሜሪካ ፍቅር ቀደም ሲል ይወራ እንደነበረው “በመካከላቸው ንፋስ ገባ” ከሚባልበት ደረጃ ባለፈ እየሰለለ መምጣቱን የሚጠቁሙ እውነታዎች እየታዩ ነው። ራሱ ህወሃት ይህንኑ ፍትጊያ የሚያጎሉ ጉዳዮች እያከናወነ ይገኛል። ለልዩነቱ መክረር ፍንጭ እየታየ ነው። ከኦባማ ዘመን ማብቃት ጋር ተያይዞ የቀድሞ ወዳጆቹ የነበሩት “ነጭ ወያኔዎች” ሥልጣን መልቀቅ እውን ሊሆን ሲቃረብ የተቀሩት “በዳግም ውልደት” እየከዱት ነው የሚል መረጃ ሲነገር ይደመጣል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያወጣው መግለጫና ማሳሰቢያ ክብደቱ መጨመሩ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለስልጣናትና ቁልፍ አማካሪዎች፣ እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች ህወሃትን እያብጠለጠሉትና ክፉኛ እየነቀፉት ነው። ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ በውይይት ህወሃት “አደረጋለሁ” እያለ ማጨበርበሩ አሜሪካኖቹን አበሳጭቷል።

ለዚህም ይመስላል “the white woyane – ፈረንጆቹ (ነጮቹ) ወያኔዎች” ለሚባሉት ወዳጆቻቸው ሳይቀሩ “የማይሰሙ፣ የማይታዘዙ፣ ምነው መለስ በኖረ … ” ሲሉ መማረራቸውን እንደሚገልጹ ነው። አንዷ ነጭ ወያኔና የወያኔ ቁልፍ ተሟጋች “አሁንስ የደቡብ ሱዳንን መንግሥት አደረጉን” ስትል ተሰማቷል።

መለስ በG-20 ስብሰባ

መለስ በG-20 ስብሰባ

ነጮቹ ወያኔዎች ከኦባማ አስተዳደር ጋር ተጠራርገው በሚወጡበት የሽግግር ጊዜ ላይ፣ የቀድሞዎቹ ነጭ ወያኔዎች (ጥቁሮችም ሊሆኑ ይችላሉ) እና በቀጣዩ አስተዳደር ኃላፊነት ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ አንዳንዶች “ዳግም በመወለድ” (born again) ሂደት ላይ መሆናቸውን ባልደረቦቻቸው በሹክሹክታ እንደሚናገሩ እየተደመጠ ነው። ይህ የገባው ህወሃት ጦሩን ከሶማሊያ በማውጣት ለማስፈራርት ቢሞክርም አልሆነለትም። እንደቀድሞው “እሹሩሩ” የሚለው አላገኘም። ይልቁኑም ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ቻይና በማዞር የገባበትን ራስ ምታት ይፋ አድርጓል። ለዚሁ የራስ ምታት መድሃኒት ይሆን ዘንድ ከቻይና ጋር ሙሉ በሙሉ በጸጥታና በመከላከያ ጉዳይ ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል።

በሱዳን በኩል ንፋስ እንዳይገባ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ አንዲሁም ከትግራይ ካርቱም የሚዘልቅ የባቡርና የመንገድ ግንባታ ውል ተፈራርሟል። ይህ ብቻ አይደለም ለሱዳን የሚሰጠውን መሬት ጉዳይ አጣድፎ ለመጨረስና ድንበር አካሎ በመፈራረም ህጋዊ ሰነድ ለማዘጋጀትም በስምምነቱ መካተቱን የጎልጉል ምንጮች አረጋግጠዋል።

cairo-egypt-9th-sep-2014-egyptian-president-abdel-fattah-al-sisi-meets-e78fjaበሌላም በኩል የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቅና የግብጹ አል-ሲሲ በቅርቡ ያደረጉት የመከላከያና የኢኮኖሚ ስምምነት አል-ሲሲ ከተሰየሙበት ዓላማ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ጉዳዩ የእነማ እጅ አለበት የሚለው ጉዳይ ህወሃቶችን ጤና እንደነሳቸው ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ። ግብጽ ሱዳንን እንዳትከረብትባቸው ህወሃቶች ለሱዳን ማንኛውንም ነገር ከማድረግና ከመታዘዝ ወደኋላ እንደማይሉ የአብዛኞች ስምምነት ነው።

በዚህ የአጣብቂኝ ፖለቲካ ውስጥ ነው አሜሪካ እየከረረች የመጣችው። ለአንዳንድ ቁልፍ ዲፕሎማቶች ቅርብ የሆኑ የጎልጉል መረጃ አቀባዮች እንደሚሉት “ዳግም መወለድ ለነጮቹ ወያኔዎች ብቻ ሳይሆን ለዋናዎቹ ወያኔዎች በዚህ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ነው”፡፡ ባለፈው ረቡዕ አሜሪካ ያወጣቸውን አዲሱን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ዜና ከአሜሪካ ሬዲዮ ወስደን ለአንባቢዎች እንዲመች እርማት አድርገን  ከዚህ በታች አቅርበነዋል። ማስጠንቀቂያው በተዘዋዋሪ መንገድ የአስቸኳይ አዋጁን አንሱ የሚል ይመስላል።

አሜሪካ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አራዘመች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ላሰቡ ዜጎች ያሰራጨው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ከዚህ ቀደም ጥቅምት 11 ቀን የወጣውን የሚተካ ሲሆን ምክንያት ያለውንም ይፋ አድርጓል። መንግስት በበኩሉ ጉዳዩን በቀጥታ ባይቃወምም አሁን አገሪቱ መረጋጋቷን አስታውቋል።

አሜሪካ የጉዞ ማስጠንቀቂያዋን አራዘመች

“መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል” ነገሪ ሌንጮ

በኢትዮጵያ ከህዳር 2008 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰው ፀረ-መንግሥት አመፅና በተጨባጭ የሚታየው የፀጥታ ሁኔታ ወዴት እንደሚያመራ ለመተንበይ አስቸጋሪ እንደሆነ አዲሱ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አመልክቷል። ማስጠንቀቂያው አያይዞም የአሜሪካ ኤምባሲ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አገልግሎቶች በመላ ሃገሪቱ በየወቅቱ ያለማስጠንቀቂያ ስለሚቋረጡና ሙሉ በሙሉም ስለሚዘጉ ሁኔታው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹን የመርዳት አቅሙን እንደሚያደናቅፍ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ያወጣው የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ አብራርቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች አማራጭ የግንኙነት ዘዴዎች እንዲኖሯቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ያሉበትን አድራሻ ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው እንዲያሳውቁ የጉዞ ማስጠንቀቂያው መክሯል፡፡

መንግሥት ሰላማዊ ሰልፎችን ለመበተን ሰዎች ላይ በቀጥታ ሊተኩስ እንደሚችል፣ በሰላማዊ መንገድ ለመካናወን በሚጠሩ ሰልፎች የኃይል ምላሽ እንደሚሰጥና ሰልፎቹ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ወደ ሁከት ሊለወጡ እንደሚችሉ ዜጎቹ አስቀደመው በማሰብ እንደ አስፈላጊነቱ ጥንቃቄ እንዲወስዱ ያዘዘው ይህ የጉዞ ማስጠንቀቂያ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች የደኅንነት ሁኔታቸውን በመከታተል አስፈላጊ ከሆነም ፈጥነው ከሃገር መውጣት የሚያስችላቸውን የአደጋ ጊዜ ዕቅዶች እንዲያመቻቹ መክሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ነገሪ ሌንጮ “መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል፤ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው ማስታወቂያ ግን የራሱ አቋም በመሆኑ ለአሜሪካ መንግሥት እንተወዋለን” በማለት የተለሳለሰ ምላሽ ዜናውን ላጠናቀረው የቪኦኤ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ምላሽ ሰጥተዋል።

የህወሃትና የነጭ ወያኔዎቹ ቀጣይ ግንኙነት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ከላይ የተጠቀሱት የተወሰኑ ፍንጮች በአንድ መልኩ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን አሜሪካ የግል ጥቅሟን ከማስጠበቅና ህወሃት ደግሞ ለጌቶቹ የመታዘዝ ግዴታው ከማሸርገድ ባህርዩ ጋር ተጣምሮ ህልውናውን ለማስቀጠል ሲል በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ አዳዲስ ነጭ ወያኔዎችን በውትወታ (ሎቢ) ለመመልመል የመሞከሩ ጉዳይ መዘንጋት የሌለበት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በአሜሪካ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይላት ጉዳዩ ካለቀ በኋላ የተቃውሞ ሰልፍ ከመውጣት ይልቅ ካሁኑ በፊናቸው የውትወታ ሥራ እንዲደርጉ ለጎልጉል አስተየታቸውን የሰጡ ያሳስባሉ፡፡ (መግቢያ ፎቶ: የወያኔ ቀንደኛ ደጋፊ የUSAID በኢትዮጵያ ሃላፊ ጌይል ስሚዝ (በመኪናው ላይ የሚታየው ምህጻረ ቃል “ማረት” – ማኅበረ ረድኤት ትግራይ) – Photo: David Kahrmann USAID Ethiopia)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events