Dehai

Goolgule.com: የአለቃ ጸጋየ በርሄና የህላዊ ዮሴፍ ወጎች፤ ከሹመት እስከ ሽረት፤

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Sunday, 26 February 2017

የአለቃ ጸጋየ በርሄና የህላዊ ዮሴፍ ወጎች፤ ከሹመት እስከ ሽረት፤

February 26, 2017 10:31 am By Editor
  • የህወሓት-እስራኤል ቀጣይ የፖለቲካ ቁማር!

አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ለህወሓት/ኢህአዴግ ቁልፍ የስጋት ምንጩ የዲያስፖራዉ የተቃዉሞ ጎራ ነዉ፡፡ የድህረ-ምርጫ 97 ዉርስ ዕዳ የሆነዉ የዲያስፖራዉ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንደ ሀገር ቤቱ ሁሉ በዘዉግ ፖለቲካ የሚታመስ ቢሆንም በጋራ ጠላት (ህወሓት/ኢህአዴግ) መዉደቅ ላይ ያለ አንዳች የልዩነት መስመር ይስማማል፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ ሀገር ቤት ያሉት የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከሚያሰሙት ጩኅት በላይ ከባህር ማዶ የሚሰማዉ ሹክሹክታ እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡ የህዝብ ድምጽና የዲያስፖራዉ የተቃዉሞ ፖለቲካ መሳ ለመሳ መሄድ የቆላ ቁስል ሆኖበታል፡፡ እናም የዲፕሎማሲ ታርጋን እንደ ሴራ ፖለቲካና ድርጅታዊ ጠቀሜታነት አብዝቶ ለመጠቀም የጨዋታዉን ህግ ያሻሻለ ይመስላል፡፡

የዲያስፖራ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት በማይካድ ደረጃ አይሎ በመዉጣቱ ወትሮዉንም ጥንቃቄ ይደረግበት የነበረዉ የአምባሳደሮች ሹመት ቁልፍ ቁልፍ በሆኑ ሀገራት የህወኃት ሰዎች አለያም ለድርጅቱ ቀይ ምንጣፍ ሊጎትቱ ለሚችሉ የኢህአዲግ አባል ድርጅቶች ዉስጥ አባላት መሆን እንዳለባቸዉ የህወሓት ነባር ታጋዮች የማይሻር ህግ ነዉ፡፡

አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ብረት አከል ሁለገብ ትግል (ገጠር-ከተማ የሚያዳርስ የተጠና የትግል ስልት) በሚሹ ኃይሎችና በወታደራዊ ዕምቃ ሥልጣናቸዉን ሊያጸኑ በወሰኑ መንግስታዊ ሽፍቶች መሀከል የሚዋልል ፍትጊያ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ ሆኗል፡፡

የሰላማዊ ትግል ጀምበር ባዘቀዘቀባት ኢትዮጵያ፤ ከወራት በፊት ተራዛሚነት ባሳየ መልኩ ለተቀጣጠሉት ህዝባዊ አመጾች የሞራልና የሎጀስቲክ ድጋፎችን በተናጠልና በግብረ-ኃይል ደረጃ በማድረግ የዲያስፖራዉ ሚና ላቅ ያለ ነዉ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት ያለ መታከት እንቅልፍ አጥቶ ይሰራበት የነበረዉ ጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ በድካሙ ልክ አልሆንለት ብሏል፡፡ ይህን አዉዳሚ ጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳዉን በማክሸፍ ረገድ የዲያስፖራዉ ሚና ከነችግሩም ቢሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይም በሀገር ቤት የሚታየዉን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶችን ረገጣ ለምዕራቡ ዓለም በማስተጋባት፤ ዘዉግን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በማስረጃ አስደግፎ በማጋለጥ፤ “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ!” የሚለዉን ህወሓታዊ “የዘዉግ ኢኮኖሚክስ” ገመና አደባባይ ላይ በማስጣትና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት የዲያስፖራዉ የተቃዉሞ ጎራ ተጽዕኖ ከቃላት በላይ ነዉ፡፡

ላለፉት ሃያ አምስት አመታት ስንሰማዉ ከኖርነዉ እዉነታ አኳያ በዉጭ ሀገራት በአምባሳደርነት የሚሾሙን፣ የደህንነትና የፖለቲካ አታሼዎችን እና የኢምባሲ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ምደባ በጌታቸዉ አሰፋ የሚመራዉ የደህንነት ቢሮዉና ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ የሚሰሩት መሆኑን ነዉ፡፡ ህወሓት ከአናሳ ዘዉግ የተገኘ የፖለቲካ ቡድን እንደመሆኑ መጠን የሰዉ ኃይል ዉስንነት አለበት፡፡ ህወሓት የራሱን ሰዎች በሁሉም ቦታ ለመመደብ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችና የሰዉ ኃይል ዉስንነት ቢያግደዉም በዋናዋና ሀገራት ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አኳያ የራሱን ሰዎች ቢቻል በአምባሳደርነት ቦታ ካልሆነም በኢምባሲ ዋና ጸሃፊነት፤ የፖለቲካና የደህንነት አታሼ ቦታዎች ላይ ማስቀመጥ ለድርድር የማያቀርበዉ አቋሙ ነዉ፡፡

እንዲህ ያለዉን ተሞክሮዉን ይበልጥ ለመረዳት በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አዉስትራሊያ፣ በአዉሮፓ ዋና ዋና ሀገራት (እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ኖርዌ፣ ቱርክ) በኤዥያ (ህንድ፣ ጃፓን፣ቻይና፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሲንጋፖር) በመካከለኛዉ ምስራቅ (የተባበሩት አረብ ኢሜሬት፣ ኳታር፣ሳዉዲአረቢያ፣ ኩዌት፣ እስራኤል) በአፍሪካ (ሁለቱም ሱዳኖች፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ) ባሉ ሀገራት የአምባሳደር ሹመቶችንና በታኮነት የተቀመጡትን ወሳኝ የኢምባሲዉን ሰራተኞች ማንነትና ፖለቲካዊ ስብዕና ማጤኑ ይበልጥ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ ተሹዋሚ አምባሳደሮቹ አንድም የህወሓት ሰዎች ናቸዉ ካልሆነም የድርጅቱ ቀይ ምንጣፍ ጎታቾች መሆናቸዉ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይሆንም፡፡ እዚህ ላይ በአሜሪካና በእንግሊዝ ያሉትን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኞችን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኃይለ ሚካኤል አበራ

ግርማ ብሩን በአምባሳደርነት ሹመዉ ከጽዳት እስከ ኢምባሲዉ ዋና ጸሃፊ ድረስ፣ ከሴፍቲ ማን እስከ ፖለቲካና ደህንነት አታሼዎች ድረስ ከቪዛ ጉዳዮችን ከሚመለከቱ ሰራተኞች እስከ የዲያስፖራ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ የትግራይ ሰዎች ናቸዉ፡፡ፕሮፖጋዲስቶቹ የህወሓት ሰዎች በየቢሯቸዉ የ“ብሄር ብሄረሰቦች”ን ፎቶ ለጥፈዋል፡፡ የክልሎችን ባንዴራ በየቢሮዉ ተፈልጎ አይታጣም፡፡ በስጋ ህወሓት በመንፈስ ደግሞ “ብሄር ብሄረሰቦች” ዉክልና አላቸዉ፡፡ ለንደን ላይ ብርሀነ ሀጎስን የተካዉ የኤፈርትን ንግድ የሚያጧጥፈዉ ኃይለ ሚካኤል አበራ ኢምባሲዉን ከእግር እስከ ራሱ በትግራይ ሰዎች ሞልቶታል፡፡ ይሄዉ ከሰሞኑ በዉጭ አገራት ባሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች የህወሓት 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በከበሮ ድለቃ እየተከበረ እንደሆን በመገናኛ ብዙሃን የዜና ሽፋን ተሰጥቶት እያየን ነዉ፡፡ የብአዴንና የኦህዴድን የምስረታ በዓል ማን ዘወር ብሎ ያያል?

ከላይ ለማሳያነት በተጠቀሱት ሀገራት የሚመደቡት አምባሳደሮች ካልተጻፈዉ ቀዳሚ ሥራቸዉ አንዱ ለህወሓቱ ግዙፍ ድርጅት ኤፈርት የሚሆኑ የንግድ ልዉዉጥ ጉዳዮችን ማመቻቸት ሲሆን፤ በግልጽ ከተጻፈዉ ቀዳሚ ሥራቸዉ አንዱ ደግሞ እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ዲያስፖራዉን ቢቻል በአብዮታዊ ዴሞክራሲዉ “የዲያስፖራ ፖሊሲ” እንዲጠመቅ በማድረግ የድርጅቱን ማህበራዊ መሰረት ማስፋት ካልሆነም በዲያስፖራዉ መካከል የዘዉግ ክፍፍል በመፍጠር ኃይሉን ማዳከም አምባሳደሮቹ፣ የፖለቲካና የደህንነት አታሼዎቹ የሥራ አፈጻጸም ከሚገመገምባቸዉ ነጥቦች በቀዳሚነት ይጠቀሳል (እንደየ ሀገራቱ የዲያስፖራ የኃይል ሚዛን ቢለያይም)፡፡

የህላዊ ህልውና ማክተም

የመለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ የተፈጠረዉን የዲፕሎማሲ ክፍተት ለመድፈን በየዓመቱ መጨረሻ ወር ላይ በህወሓቱ ኢሳያስ አማካኝነት የዉጭ ገዳዮችን በሚከታተለዉ የደህንነት ቢሮዉ ዲፓርትመንት ሪፖርት አቅራቢነት በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስተባባሪነት መካሄድ የጀመረዉ የአምባሳደሮች ዓመታዊ ስብሰባ ቀዳሚ አጀንዳ “የጽንፈኞችን ኃይል ለማምከን የተደረጉ ጥረቶችን እና ልማታዊ ዲያስፖራ ለመፍጠር የተሰሩ ተግባራት” የተመለከቱ ጉዳዮችን በስፋት ይቃኛሉ፡፡ ቀናት በሚወስደዉ በዚሁ ስብሰባ የየኢምባሲዉ አምባሳደሮች በመዋቅር ደረጃ ከነርሱ በታች የፖለቲካና የደህንነት አታሼ ሆነዉ በተመደቡ የህወሓት ሰዎች ከፍና ዝቅ እየተደረጉ ይገመገማሉ፡፡ እንዲህ ያለዉ ግምገማ በብርቱ ከደረሰባቸዉ አምባሳደሮች ቀዳሚዉ ህላዊ ዮሴፍ ይገኝበታል፡፡

ህላዊ ዮሴፍ

ህላዊ ዮሴፍ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ሆኖ ከተሾመ አንስቶ ሁለት ዋና ዋና ተልዕኮዎችን ማሳካት ይጠበቅበት ነበር፡፡ የእስራኤል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻት በተለይም ከኤፈርት ጋር (የብአዴኑን “ጥረት” እንርሳዉ) የሚሰሩበትን ዕድል መፍጠር አንደኛዉ ተልእኮዉ ነበር፡፡ ሁለተኛዉ ተልዕኮ ደግሞ በእስራኤል የሚኖሩ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያንን (ቤተ እስራኤላዊያንን) የዲያስፖራ ፖሊሲ በማጥመቅ መዋዕለ ንዋያቸዉን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ ማግባባት ጎን ለጎን ከቅርብ አመታት ወዲህ በቤተእስራኤላዊያን ዘንድ እየተስተዋለ ያለዉን የአንድት ሃይሉን በገንዘብ የመደገፍ ስሜት ማስተንፈስ የህላዌ ዮሴፍ ቁልፍ ተልእኮዎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኢምባሲ ዉስጥ ሶስተኛ ተልእኮም አለ፡፡ እስራኤል እንደ መንግስት ህወሃት እንደ ድርጅት በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከሞሳድ ጋር የሚሰሯቸዉ ተግባራት አሉ፡፡

እስራኤልና አሜሪካን ሶማሊያ ዉስጥ ከመሸገዉ የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ለመጠበቅ በዉክልና የሚዋጋዉ ህወሃት ለዚህ ዉለታዉ ከቴክኖሎጂ አቅም ጋር በተያያዘ የደህንነትና ስለላ (በተለይም ከሽብተኝነት ጋር በተያያዘ) እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትና ስለላ የተመለከቱ ስልጠናዎች ለህወሃት ምልምሎች ይሰጣል፡፡ የስልጠና ተሳታፊዎችን የስልጠና ሂደቱን የሚከታተለዉ በኢምባሲዉ በኩል የደህንነት አታሼ ቡድን አለ፡፡ ህላዌ ይህን ጉዳይ ዳር ቁሞ ከመታዘብ የዘለለ ሚና አልነበራዉም፡፡

ያም ሆኖ “የእስራኤል ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በሚገባ አልሳብክም፤ ለኤፈርት ይህ ነዉ የሚባል የገበያ ትስስር አልፈጠርክም፤ በቤተእስራኤላዊያን ዲያስፖራዎች መዋዕለ ንዋያቸዉን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ ማግባባት አልቻልክም፤ በተለይም በ2008ዓም ሃምሌ ወር ላይ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ በባህር-ዳር ከተማ በተከበረዉ የዲያስፖራ ቀን ከእስራኤል የመጡት ዲያስፖራዎች ሰባት ብቻ ነበሩ፡፡ በአንጻሩ ቴልአቪቭና ጎንደር ከተማን ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ቴልአቪቭ የትምክህተኞችና የፀረ- ሰላም ሃይሎች ማዕከል ስትሆን አንተ ቢሮህን ዘግተህ ልቦለድ ታነብ ነበር” በሚሉ ቅስም ሰባሪ ክሶች በመዋቅር ደረጃ የበታቾቹ በገቢር ግን አለቆቹ በሆኑት የኢምባሲዉ የፖለቲካና የደህንነት አታሼዎች ተገምግሞ በእነ ጌታቸዉ አሰፋ ይሁንታ ሰጪነት በኃይለማርያም ደሳለኝ ፈራሚነት ከአምባሰደርነቱ ተነስቷል፡፡ በምትኩም የምንግዜም የበላዩ የህወሃቱ አለቃ ፀጋዬ በርሄ ተሹሟል፡፡

“የህላዌ አዕምሮ ኢህአፓ ላይ ቁሟል፡፡ ከዚህ በኋላ አዕምሮዉን ለግጥም እንጂ ለፖለቲካ ሊያዉለዉ አልቻለም” የሚሉት የኢህዴን የቀድሞ ታጋዮች፤ የመጠሪያ ስሙን ከፍቅሩ ዮሴፍ ወደ ህላዊ ዮሴፍ ከቀየረ በኋላ ከርዕዮተ ዓለማዊ ምልከታ ይልቅ የግጥም ተመስጦዉ በረታ፡፡ በድህረ ደርግ የመጀመሪያዉ አዲስ ዓመት ማግስት የህላዊ ብቸኛ ወንድም በአዲስ አበባ አንድ ጥግ ቦታ ላይ ራሱን አጥፍቶ ተገኘ፡፡ ህላዊ ከዚያች ቀን ጀምሮ ግድየለሽና ዝርክርክ ሰዉ ሆነ፡፡ አልኮልን ዋኘበት፡፡ ሲጋራን ከብዕሩ በላይ ጨበጠ፡፡ በበረከት ስምኦንና በጥቂት ጓዶቹ ጥረት ህይወትን በሹፈት፤ ፖለቲካን በአስመሳይነት ቀጠለ፡፡

ለዚህም ይመስላል የርጅና ዘመኑ አስቀድሞ የመጣ፡፡ በአምባሳደርነት ግዜዉ የኢየሩሌምን ገዳማት አዘዉትሮ ይጎበኝ ነበር፡፡ ቴልአቪቭ ዉስጥ በሚገኘዉ አዲስ አበባ ሬስቶራንት በተደጋጋሚ  ከሚገኙ ደንበኞች ቀዳሚዉ እርሱ ነዉ፡፡ በህወሃት ሰዎች አጠራር “በአዝማሪ ድግስ/ኮንሰርት” መታደም ነፍሱ ነዉ፡፡ ጠርሙስ ባይወረወርበትም አሽሙር ተወርዉሮበት ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡ ቢሮዉ ዉስጥ በአዳም ረታ የልቦለድ ስራዎች መዝናናት ይወድ የነበረዉ ህላዌ፤ “የስንብት ቀለማት” እና “መረቅ” የተሰኙ የደራሲዉ ስራዎች ቢሮዉ ጠረጴዛ ላይ አይጠፉም፡፡

በእነዚህና መሰል ድርጊቶቹ ለተከታታይ ሁለት አመታት “C” በስንብት ዘመኑ ደግሞ “D” የተሰኘ አሸማቃቂ የአምባሳደርነት ዉጤቱን ተቀብሎ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡ ህላዊ ከዚህ በኋላ የህይወት ዘመን አለቆቹ የህወሃት ሰዎች ቢፈቅዱለት ከነሠራዊት ፍቅሬ፣ ቴዎድሮስ ተሾመ ፣ሙሉአለም ታደሰ…ጋር ፈርሾ የሮማንስ አድቬንቸር ፊልም ስክሪፕት እና ባሩድ ባሩድ የሚሸቱ ግጥሞችን እየጻፈ ማምሻዉን ደግሞ በቀኝ እጁ ቮድካ በግራ እጁ የኮንከር ካርታዉን ታቅፎ በዝምታ ሞቱን ቢጠብቅ አይጠላም፤ ፈቃጅ የለም እንጂ! ከወራት በኋላ በብአዴኑ “ጥረት ኮርፖሬት” የቦርድ አባልነት ዉስጥ አልያም በኢህአዴግ ጽ/ቤት በኩል ብቅ እንደሚል እንጠብቃለን፡፡

የአለቃ ፀጋዬ በርሄ ሹመትና ቀጣይ የቤት ሥራዎች

ጸጋዬ በርሄ

ከስድስተኛ ክፍል ትምህርቱና ከድቁናዉ አቋርጦ 1968ዓም ላይ ደደቢት በረሃ የተገኘዉ የቤተክህነት ሰዉ – ፀጋዬ በርሄ፡፡ ከዓለማዊ ትምህርቱ ይልቅ መንፈሳዊ ትምህርት ላይ የገፋ ሰዉ ነዉ፡፡ አለቃ ጸጋዬ በርሄ ሰባት ዓለማዊ መጽሃፍትን ባያነብም ሰባት ጊዜ ዳዊት ደግሟል፡፡ “አለቃ” የሚለዉ “የማዕረግ” ስሙም ከቤተክህነት ትምህርቱ ጋር ተያይዞ ኮሚኒስት ጓዶቹ ሲያላግጡበት ያወጡለት ስሙ ነዉ፡፡

አለቃ ጸጋዬ በርሄ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባይጀምርም ዛሬ ላይ በቢዝነስ አድሚስትሬሽን (MBA) የሁለተኛ ዲግሪ “ባለቤት” ነዉ፡፡ ጸጋዬ በርሄ ከትምህርት አኳያ ልክ እንደ ነጭ ወረቀት ንጹህ ነዉ፡፡ ከሴራ ፖለቲካ አኳያ ግን የሚናቅ ሰዉ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አለቃ ጸጋዬ በርሄ የሽማግሌዉ ስብሃት ነጋ ዋርሳ መሆኑ ነዉ፡፡ የስብሃት ነጋ እህት ቅዱሳን ነጋን አግብቷል፡፡ ተንኮሉም ቢሆን ከአምቻ ጋብቻ ዉህድ የተገኘ ይመስላል፡፡ ድንቁርናዉም እንደዛዉ፡፡ ጸጋዬ ላይ የተቀለዱ ቀልዶች ግነት ቢታይባቸዉም ከእዉነታዉ ብዙ የራቁ ግን አይደሉም፡፡ ለአብነት አለቃ ጸጋዬ በርሄ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት እያለ ዮሃንስ ቤተመንግስት ዉስጥ መለስ በሚመራዉ ስብስባ ላይ ጣልቃ እየገባ ሲያስቸግር መለስ በቁጣ ስሜት “አለቃ ጸጋዬ የስብሰባዉን ህግ ታከብር እንደሆነ አክብር ካልሆነ ግን ይሄን ስብሰባ በእንግሊዝኛ ነዉ የማደርገዉ” ብሎ አሸማቀቀዉ እየተባለ የሚወራዉ ቀልድ የሰዉዬዉን ነጭ ወረቀትነት ለማመላከት ነዉ፡፡

አለቃ ጸጋዬ ህወሓት ረግጦ በሚገዛት ኢትዮጵያ በዋናነት በድሀረ መለስ ከታዩት ፖለቲካዊ አፈናዎች ጀርባ እጁ አለበት፡፡ በመለስ ጊዜም ቢሆን የህወሃት ክፍፍልን ተከትሎ በተፈጠረዉ  የኃይል አሰላለፍ የመለስን ቡድን በመደገፍ የእግረ ረጅሙን ሰዉዬ (ገብሩ አስራት) ወንበር የተረከበ፤ በክልሉ ዉስጥ አኩራፊ እንጂ አንድም ተቃዋሚ እንዳይፈጠር ተግቶ የሰራ፤ የኢዲዩ እና የደርግ ርዝራዥ ናቸዉ ያላቸዉን የትግራይ ሰዎች “ባዶ ስድስት” የተባለ እስር ቤት ያለ ምክንያት በማጎር ያሰቃየ፤ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) መሪ የነበረዉ ፍሰሃ ኃይለማርያምን (ቀደም ሲል የህወሃት ሰዉ ነበር) ኤርትራ በረሃ ላይ በደህንነት ሰዎች ሲገደል ግድያዉን ካቀነባበሩት ግንባር ቀደም ሰዎች አንዱ አለቃ ጸጋዬ በርሄ ነበር፡፡

በድህረ መለሷ ኢትዮጵያ የአለቃ ጸጋዬ ስዉር የአፈና እጆች የከሸፈዉን የአንዳርጋቸዉ ፅጌን የግድያ ሙከራ (ኢሳት በዶክመንተሪ መልክ ሰርቶታል) በማቀነባበር፤ አንድነት ፓርቲን በትእግስቱ አወሉ በኩል እንዲሰነጠቅ በማድረግ፤ ሰማያዊ ፓርቲን በማስተንፈስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ዉስጥ ገብቶ በመፈትፈት፤ መተማ ላይ የተፈናቀሉትን የትግራይ ሰዎች ድራማ በማቀነባበር፤ የወልቃይትን ጉዳይ ይበልጥ በማወሳሰብ ረገድ ሰዉዬዉ እጁ ረጅም ነዉ፡፡ደብረጽዮን የሚያከብረዉ፤ ጌታቸዉ አሰፋ የማይንቀዉ ሰዉ – አለቃ ጸጋዬ በርሄ አሁን ለየት ያለ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ተሿሚ ሆኗል፡፡ በዚህ ሹመቱ ህላዊ ዮሴፍ ልቦለድ እያነበበ ያበላሻቸዉን ስራዎች ከኢምባሲዉ ነባር የህወሃት ተሿሚዎች ጋር ሆኖ ማስተካከል ይኖርበታል፡፡

  • ለኤፈርት የንግድ አጋር መሆን የሚችሉ ኩባንያዎችን ማፈላለግ
  • የቤተ እስራኤላዊያንን የከረረ የአንድነት ስሜትና ድጋፍ ማስተንፈስ
  • ሞሳድ ለህወሃት የሚሰጠዉን የደህንነትና ወታደራዊ ስልጠናዎች ሂደት መከታተል የአለቃ ጸጋዬ ተጠባቂ ተልዕኮዎች ናቸዉ፡፡

አለቃ ፀጋዬ ከትግረኛ እና ግዕዝ በመጠኑም ቢሆን ከአማርኛ ቋንቋ በስተቀር ሌላ ቋንቋ ጆሮውን  ቢቆርጡት አይስማም፡፡ የአለቃ ፀጋዬን የቋንቋ ችግር ቀድሞ የተረዳው የጌታቸው አሰፋ የደህንነት መስሪያ ቤት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ ከሚሰሩት ሁለት የፖለቲካና ሶስት የደኅንነት አታሼዎች በተጨማሪ ለሁለቱም ዘርፍ ሁለት ሁለት ተጨማሪ ሙያተኞች ከአለቃ ፀጋዬ ጋር ወደ እስራኤል እንዲጓዙ አድርጓል፡፡

ስኳዱን አጠናክሮ የተጓዘው አለቃ ፀጋዬ “ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠር ፖለቲካውን ይቆጣጠራል” በሚለው ህወሃታዊ መመሪያ መሠረት ለግዙፉ ኤፈርት የንግድ ኢምፓየር ተጨማሪ ግብአት  ለመፍጠር በቻለው መጠን መትጋቱ ይጠበቃል፡፡ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ (ከሱር ከንስትራክሽን ጋር)፤ በመድኃኒት ምርት (ከአዲስ የመድኃኒት ፋብሪካ ጋር)፤ በእርሻ መሳሪያዎች (ከህይወት ሜካናይዜሽን ጋር) በቴክኖሎጂ ዘርፍ (ከኮምፒዉተር ኔትወርኪንግ ቴክኖሎጅ ሶሉሽን ጋር) እንዲሁም በ“ትዕምት” ስር ካሉ ሌሎች በዝባዥ የንግድ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩ የእስራኤል  ባለሀብቶችን በማፈላለጉ ረገድ የአለቃ ፀጋዬ ስኳድ ድርጅታዊ ተልዕኮ ይሆናል፡፡

በእስራኤል የሚኖሩ አብዛኞዎቹ ቤተ እስራኤላዊያን እጅግ ጥብቅ የሆነ የአንድነት ስሜት ያላቸውና የታወቀውሞ ጎራውን የሚደግፉ ናቸው፡፡ ኢሳት በተደጋጋሚ የገቢ ማስባሰቢያ አካሂዶ ከማያፍረባቸው ከተማዎች አንዷ ቴልአቪቭ ነች፡፡ ቤተ እስራኤላዊን በእስራኤል ውስጥ ያላቸው የአንድነት የፍቅር ስሜት ከሌላው አለም ለየት ያለ ነው፡፡ አብዛኞዎቹ ከአንድ አካባቢ (ከጎንደር) የሄዱ በመሆኑ በዘውግ የመከፋፈል ተጋላጭነታቸው ወደ ዜሮ የወረደ ነው፡፡

ቤተ እስራኤላዊያን ከቆይታ ብዛት በወታደራዊ መስክ እስከ መኮንንና የመስመር ኃይል መሪነት የደረሱ፤ በእስራኤል የሀገር ውስጥ የደህንነት መስሪያ ቤት “ሽንቤት” የደህንነት ኦፊሰር የሆኑ፤ በትህምርትና በንግድ የተሳካላቸው፤ በፖለቲካዉ መስክ የካዲማ ፓርቲ አባል በመሆን በእስራኤል  ፓርላማ “ክኔሴት” የፓርላማው ምክትል አፈጉባኤ የሆነውን ሸሎሞ ሞላን ጨምሮ በሊኩድ ፓርቲ በአመራር ደረጃ ቤተ እስራኤላዊያን አሉ፡፡

የጠንካራ ኮሚኒቲ ባለቤት የሆኑት ቤተ እስራኤላዊያን፤ የድህነት ጉዳይ ሆኖ እስራኤል ቢኖሩም ልባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነች በኩራት ይናገራሉ፡፡ ቤተ እስራኤላዊያን ሀገር ቤት ባለው  ጨቋኝና ዘረኛ አገዛዝ ሁሌም እንደተከፉ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ስልፎችን በማዘጋጀትና ለተቃዋሚው ኃይል የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የከረረ ተቃውሟቸዉን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

የጥንቱን ሰለሞናዊ ትርከት እንተወውና እስራኤል በአመዛኙ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት የተለሳለሰና ጥቅም ተኮር ነው፡፡ በኃይለሥላሴ ጊዜ ጽዮናዊነነትን አስታክካ ግንኙነቷን በይፋ  የጀመረችው እስራኤል፤ ጽዮናዊነነትን በአደባባይ “ማህበራዊ አደንዛዥ ዕጽ” እያለ ይነቅፍ የነበረው ደርግ ሲመጣም እርሱን ሳትዘልፍ የሽምቅ ተዋጊዎቹንም ሳትደግፍ በተለሳለስ መልኩ መንግሥቱ ኃይለማርያም ያበደበትን “ዘመቻ ሰለሞንን” አሳክታለች፡፡

ህወሓት ማዕከላዊ መንግሥቱን በተቆጣጠረ በወራት ልዩነት ባዘጋጀው የሽግግር መንግሥት ጉባኤ ላይ በተጋባዥነት የፍልስጤሙን ነፃ አውጪ መሪ ያሴር አራፋትን ሲጋብዝ፤ እስራኤል የደንቡን  ያህል ተቃወመች አንጂ አኩርፋ አልቀረችም፡፡ የማታ ማታም የደኅንነት አቅምን ከማሳደግና  የቴክኖሎጂ አቅምን ከማጎልበት አኳያ የሞሳድ ድጋፍ የተገለጠለት ህወሃት ከእስራኤል ጋር በፍቅር ወደቀ፡፡

እስራኤል ለየትኛውም ሀገር በደኅንነትና ወታደራዊ ሥልጠናዎች ዙሪያ ድጋፍ ለመስጠት ቀዳሚ መስፈርቷ ሰብዓዊ መብቶች አለያም ዴሞክራሲያዊ መብቶች የመከበር ያለመከበር ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ከተሳካ ታሪካዊ መሰረት ያለው ጽዮናዊነት ካልሆነም ሽብርተኝነትን በተመለከተ ሀገራቱ ያላችውን የአደባባይ አቋምና መልካዊ ምድራዊ አቀማመጥ መገምገም ይቀላታል፡፡

በዚህ ስሌት ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተመራጭ በተለይም በሶማሊያ ጸረ አሜሪካ-እስራኤል የሆነው አልሸባብ አከርካሪ አለመስበር፤ በኤርትራ ምጽዋ ወደብ ላይ ኢራን፤ ሳውዲ አረቢያና ግብጽ የጦር ቤዝ ለመመስረት ያላቸው ወታደራዊ ፍላጎት፤ የየመናዊያን የርስ በርስ ጦርነት እና ኢራንና የሳውዲ አረቢያ በየመን የውክልና ጦርነት መጀመራቸዉ በዚህ ክፍተት  የሚፈጥረው ኃይል ያሳስባት እስራኤል ኢትዮጵያን አጥብቃ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ መቼም አከራሪ የጽዮን ብሄረተኛው ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ጉብኝት በጠብታ መስኖ ልማት ዙሪያ ለመፈራረም እንዳልመጣ ግልጽ ነው፡፡

የህወሃት የደህንነት መስሪያ ቤት አቅም ይበልጥ እየፈረጠመ መምጣት ግብአቱ ከአሜሪካና ከእስራኤል የሚሻገር አይደለም፡፡ በተለይም በብርጋዴል ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ የሚመራው የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) የታቀዋሚ ፓርቲ መሪዎችን፣ የጋዜጠኞችን፣ የአክቲቪስቶችን፣ የተጽዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶችን እና የታዋቂ ግለሰቦችን የዕለት ተዕለት የስልክ ግንኙነት በመጥለፍ፤ የኢይሜል እና የፌስቡክ አካውንታቸውን በመስበር መረጃዎችን ሲበረብር ውሎ የሚያድርበት የአቅም ምንጭ ከእስራኤል-አሜሪካ የተገኘ ነው፡፡

አለቃ ፀጋዬ፤ ቤተ እስራኤላውያን የአንድነት ኃይሉን የታወቀውሞ ጎራ የሚደግፉበትን ብሄራዊ ስሜት ማስተንፈስ የሚሳካለት ባይመስልም፤ የግዙፉን ኤፈርት የንግድ ኢምፓየር ይበልጥ ለማስፋትና በሞሳድ በኩል ለህወሃት ምልምል የደኅንነት ሰዎች የሚሰጠውን ስልጠና በምልክት ቋንቋ ቢሆን ተደግፎ የሥልጠናውን ሂደት ለመከታተል አይሰንፍም፡፡

የሀገር ቤቱ ህዝባዊ ተቃውሞ አይሎ ህወሓት ወደ መቃብር ቢወርድ እስራኤል አለቃ ፀጋዬን አሳልፋ ባትሰጥም ዴር ሱልጣን ገዳም ውስጥ የብህትውና ህይወት እንዲኖር ፈቃድ የምትነፍገው አትመስልም፡፡ ማን ያውቃል አለቃ ፀጋዬም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተካውን ዳዊት አንስቶ  ይደግመው ይሆናል፡፡ እስከዚያዉ ግን እስራኤል አንደ መንግሥት ለብሔራዊ ደህንነቷ፤ ህወሃት እንደ ድርጅት ለልዕለ ዘዉግ የበላይነት ወዳጅነታቸው ይቀጥላል፡፡


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events