World News

Satenaw.com: ካዘመመው ሀውልት በስተጀርባ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Wednesday, 15 March 2017

ካዘመመው ሀውልት በስተጀርባ

(ቬሮኒካ መላኩ)

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታና የፓርቲዎች የሃይል አሰላለፍ ግራ የሚያጋባ ሆኗል ። በአለፉት 25 አመታት ህውሃቶች በመከላከያና በደህንነት ተቋማት ውስጥ ይዞታውን ያረጋገጠ ሌላ ድርጅት ህውሃትን ፂሟን ይዞ ጎትቶ መጣል እንደሚችል በመረዳቷ እነዚህን ተቋሞች ላለፉት 25 አመታት በሞኖፖል ተቆጣጥረው ይዘውታል ።


ህውሃቶች ለአመታት በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ያለቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ሌላም ዋስትናም ነበራቸው ። ይሄ ዋስትና በህውሃት አምሳል ተጠፍጥፈው የተፈጠሩት እህት ድርጅት የሚሏቸው ብአዴን ፣ ኦህዴድ እና ደኢህደን የተባሉት ድርጅቶች ናቸው።

ይሄ የምትመለከቱት ሃውልት የመለስ ዜናዊ የትውልድ ቦታ የተተከለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃውልት ነው። ሃውልቱ እየፈራረሰ ስለሆነ ከውድቀት ለመከላከል ሶስት እንጨቶች ባላ ሆነው ደግፈውት ይገኛል። የመለስ ሃውልት ህውሃትን ሲወክል ሶስቱ ደግፈው የቆሙት እንጨቶች ብአዴንን ፣ኦህዴንንና ደኢህዴንን ይወክላሉ ።

አድዋ የሚገኘው የመለስ ሃውልት ለመውደቅ ማዝመም እና የደገፉት ሶስት እንጨቶች ማሸብረክ ህውሃት እና ሎሌዎቹ ድርጅቶች የተጋረጠባቸውን የጊዜውን የፖለቲካ ሁኔታ አመላካች ሆኖ ይታያል ። ህውሃት መለስ ዜናዊ ከሞተ በኋላ የርእዮተ አለም ድርቀትና የድርጅቱን የበላይነት ለዘለቄታው የሚያስጠብቅ የሃይል ሚዛን ምክነት ገጥሞታል ።

የኢጣሊያው ወራሪ ሃይል በባንዳነት በማገልገል በኢጣሊያን የኢትዮጵያ ተወካይ የወረዳ አስተዳዳሪ የተሾሙት የግራዝማች አስረስ የልጅ ልጅ መለስ ዜናዊ ተንኮለኛ ቢሆንም ከአያቱ የኢጣሊያን የሮማውያን ዘመን የከፋፍለህ ግዛ ” Devide et Impera “ስልት በደንብ ያጠና እና ኢትዮጵያ ውስጥ በደንብ ተግብሮ ውጤታማ የሆነ ሰው ነበር ።


መለስ ዜናዊ በዚህ ፖሊሲው የህውሃትን የበላይነት ካረጋገጠ በኋላ በ1992 የራሱን ጓደኞች ከህውሃት በመጠራረግ የበላይነቱን አረጋገጠ ። ችግሩ የመጣው መለስ ዜናዊ በድንገት ከሞተ በኋላ ነው ። ህውሃት ውስጥ የመለስን ያክል ተንኮል እያፈለቀ ሎሌ የሚጠፈጥፍ ሰው ባለመገኘቱ ፓርቲው መወዛወዝ ጀመረ ። ይሄን የተመለከቱት ፓርቲዎች አይናቸውን መግለጥ ጀመሩ ። ነገር ግን ህውሃት መፍረክረክ ቢጀምርም ደህንነቱንና መከላከያውን ይዞ ስለነበር ለማገገም ቻለ ። ብዙም ሳይቆይ በመላው አገሪቱ ድብልቅልቅ ያለ አመፅ ተከተለ ።

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አመፅ መቀስቀሱን ተከትሎ ብአዴንና ኦህዴድ እንደከዱት በመገንዘብ ቀልጠፍ ብሎ ህውሃት እርምጃ መውሰድ ጀመረ ። በሲቪል አስተዳደሩ ያልተማመነው ህውሃት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አደርጎ ለክፉ ቀን ያዘጋጀውን መከላከያ ሰራዊት አገሪቱን እንድመራ አደረገ ። የሃይል ሚዛኑን እንዳጣ የተረዳው ህውሃት የበፊት ታማኝ አሽከሮቹን አንበርክኮ ይቅርታ የሚያስጠይቅ ሌላ አጋር ፍለጋ መራወጥ ጀመረ።

በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘውና ሰፊ ስትራቴጅክ ቦታ የያየዘው የሱማሌ ክልል በህውሃት የቀረበውን የፖለቲካ ጨረታውን አሸነፈ ።

የ 8ኛ ክፍል ተማሪ የነበረውና የቀድሞው የመብራት ሃይል ቆጣሪ አንባቢ የነበረው የሱማሌው ክልል ፕሬዚደን አብድ ኢሌ ለህውሃት እጅግ ተመራጭና ያዘዙትን ለመፈፀም አይኑን እንደማያሽ የተረጋገጠ ነው ።

በዚህም መሰረት ህውሃት ለአብድ ኢሌ የማስጀመሪያ ፊሽካዋን ስትነፋ የአብዲ ኢሌ በጥብቅ የሰለጠኑ ጨካኝ ልዩ ሃይሎች ከሱማሌ ክልል ጋር የሚጎራበቱ የኦሮሚያ ወረዳወችን በአጭር ጊዜ በመውረር በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን በመግደል የሱማሌክ ክልል ባንድራን ሰቀሉ።

የህውሃት የበቀል ብትር ያሳመመው ኦህዴድ ከህውሃት የተሰነዘረበትን በትር መቋቋም አልቻለም ። አይኑ እያየ ህዝቡ በጠራራ ፀሃይ ማለቁን የተዳው ኦህዴድ አቅሙን ገምቶ ህውሃትን ይቅርታ ጠየቀ ።

ህውሃት በኦህደድ ላይ የሰራውን የፖለቲካ ጨዋታ ቶሎ ብሎ የተረዳው ብአዴን በራሱ ላይ የታቀደው ሴራ ከመፈፀሙ በፊት ማእከላዊ ኮሚቴውን ጠርቶ ከተወያየ በኋላ በይፋ በአሳፋሪ ሁኔታ ይቅርታ ጠየቀ ። ለጊዜው አስቀያሚው የፖለቲካ ድራማው በዚሁ ተዘጋ ።

መፃኢ ሁኔታዎች

ህውሃት ለጊዜው በፓርቲዎች መካከል የነበረውን የፖለቲካ turmoile ንጠቱን በበላይነት የተቆጣጠረው ይመስላል። 95 በመቶ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ህውሃት የሚመራውን ኢህአድግ የተባለ መንግስት አንቅሮ ከተፋው ቆይቷል ። ህውሃት የአናሳ (minority) መንግስት በመሆኑ ህዝቡን ሊገዛ የሚችለው በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ነው ። አፈሙዝና አናሳ የሚመራው መንግስት ደሞ ለጊዜው ያለ ይመስላል እንጅ ዘላቂ አይደለም ። ይሄ አጠቃላይ መርህ ነው። ህውሃት ከዚህ መርህ ውጭ የሚሆንበት እድል አይኖረውም ።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events