World News

Zehabesha.com: በ”ጽናት” ቀመር የዜሮ ድምር ጨዋታው ማን ያሸንፋል፤ ሻቢያ ወይንስ ወያኔ?

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Saturday, 22 July 2017

በ”ጽናት” ቀመር የዜሮ ድምር ጨዋታው ማን ያሸንፋል፤ ሻቢያ ወይንስ ወያኔ?

መስቀሉ አየለ

ሻቢያ ከደርግ ጋር ባደረጋቸው እልህ አስጨረሻ ጦርነቶች እንደታየው አንድ ግዜ ተዋግቶ የያዘውን መሬት እስከመጨረሻው አልለቅም በሚል ግትር ዘይቤ የሚገብረው እምብዛም የሰው ሃይል አልነበረም። ይህ በደንብ የተፈተነበት ሃቅ ነው። በአንጻሩ ደርግ ሲከተለው የነበረው አካሄድ ተቃራኒውን ሲሆን አንድ ግዜ በምንም አይነት ዋጋ ከፍሎ የያዘውን ገዥ መሬት መልሶ ባመልቀቅ እስከመጨረሻው መዋደቅ ላይ ስለሚጸና ከሻቢያ አንጻር ሲታይ የደርግ አሰላለፍ ያን ያህል በማጥቃትና በማፈግፈግ ላይ የተመሰረተ ነበር ለማለት አያስደርፍርም።

ደርግ አለ የተባለውን ጦር በከፍተኛ ብሄራዊ ስሜትና ወኔ ለመያዝ የማጥቃት እርምጃውን ሲጀምር ሻቢያ ግን ሁኔታው የከበደ ከመሰለው ግዜ ሳያጠፋ ያለውን ሁሉ ሸክፎ ቦታውን ጥሎ ይሄድ ነበር።ምክንያቱም በአሉ ግርማ እንዳለው “ኤርትራ ውስጥ የሚደረገው ትግል በሰው ልጆችና በተፈጥሮ መካከል ነው”። መሬቱ ገዳይ ነው። በረሃው ደምን እንደ ሽሮ የሚያፈላ ነው። በዛ ቦታ ላይ ለአመታት ቀርቶ አንድ ቀን ውሎ ማደር በጋለ ብረት ምጣድ ላይ ተቀምጦ ስለ ትዕግስት መልካምነት እንደመስበክ ነው። የደርግ ጦር ደግሞ በአመዛኙ ከመሃል አገር የሚመጣ እንደመሆኑ ለእንዲህ አይነት የአየር ጠባይና የመሬት አቀማመጥ ባይተዋር ነው። በዚያ ላይ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ላይ የተገነባ በመሆኑ የሻቢያን ጦር እንደ ባእድ አገር ጠላት የሚያይ አልነበረም እና በኤርትራ ብሄርተኝነት ስሜት ተጠምቀው ካደጉ ሰዎች ጋር ለመዋጋት ተመጣጣኝ እልህ ነበረው ማለት አይቻልም። በዚያ ላይ በኮዳ ግጣም እየተለካች በምትጠጣ ጥርኝ ውሃ ተወስኖ እስከጉልበቱ ድረስ በተሸመቀቀ የወታደር ጫማ ታፍኖ በዚያ በረሃ ውስጥ ለተወሰነ ግዜም ቢሆንም ጸንቶ መቆየት በራሱ ቀላል ፈተና አልነበረም። ስለሆነም በምንም የወጋ ክፍያ ቢሆን አንድ ግዜ ገዥውን መሬት ከያዘ ቦሃላ ለተወሰነ ግዜ ያህል ባለበት እንዲከርም ሻቢያ ሆነ ብሎ ይተወዋል። በሂደት ግን የበረሃው ክብደት የደርግን ጦር ውስጥ ውስጡን እንደሚያከስለው ግልጽ ነበር። ከዚያም ወታደሩን ለማማረር ሃላፊነት በማይሰማቸው ጀነራል ተብዬዎች የሚሰራው ሸፍጥ ተደማምሮ የወታደሩ ጽናቱ የሚወርድበት የሆነ ነጥብ ላይ ሲደርስ ጠብቆ ሸቢያ ድንገት ይመጣና በጣም ቀላል በሚባል መስዋእትነት መልሶ ቦታውን ይቆጣጠረዋል። ለሻቢያ የአቸናፊነት ቁልፉ ነጥብ በአደገኛ ገዥ መሬትና በከባድ በረሃ ውስጥ ውሱን በሆነች ውሃ ጸንቶ መቆየት መቻልና በተራዘመ ጦርነት ማዳከም ዋነኛ የጦርነት ዶክትሪኑ ሆኖ ቆይቷል።የንጉሱን ዘመን ሳንቆጥር በደርግ የአስራ ሰባት አመት የጦርነት ዘመን ናቅፋን ለመቆጣጠር የተደረጉ ስድስት ዘመቻዎች ያልተሳኩትበትን ኩነት ለማየት የበአሉ ግርማ በደማም ብዕሩ ከልቡ ውስጥ በሚቀዳ የደም ቀለም ኦሮማይ ላይ ጽፎት ካልፈው ትውስታ በላይ ሄዶ መግለጥ አይቻልም። ሻቢያ መንግስት ከሆነ ቦሃላ የአገሪቱን ብሔራዊ ገንዘብ “ናቅፋ” ብሎ መሰየሙ የኤርትራን ብሄርተኝነት ለማዳን በናቅፋ የተከፈለውን መራራ ጽናት ህያው ታሪክ አድርጎ ለመዘከር መሆኑ ግልጽ ነው።

ይኽ የሻቢያ የጽናት ቀመር ከሌሎች ደርግን ከገጠሙት ውስጣዊና አለማቀፋዊ ቅራኔዎች ጋር ተደማምረው በተራዘመ ጦርነት ውስጥ አዳክመው ለውድቀት ዳርገውታልና ሽቢያዎች ጽናትን እንደ አይዲዮሎጅ ውስዶታል ማለት ይቻላል። ለዚህም አንደኛው መገለጫ ሸቢያዎች አስመራ ገብተው መንግስት ከሆኑም ቦሃላም እንኳን እንደ ወያኔ ቡችሎች ወደ ዘረፋው ዝሙቱና መጠጡ አለመሄዳቸው ነው። ሻቢያ እንደ መንግስት ወታደራዊ አገዛዝ ነው ቢባልም መሪዎቹ ዛሬም ድረስ የሚኖሩት የደሃውን ህዝብ ኑሮ በመሆኑ እነርሱን በሌብነትና ይኽን በመሰለው ክህደት መክሰስ አይቻልም። ዛሬ አንድ የሻቢያ ጀነራል ቤት ጎራ ቢሉ “ሰሞኑን የመብራት እጥረት ስላለ እንጀራ እንዳትጋግሩ ተብለናል እና ይቅርታ” ብለው ለእንግዳው እራት ቂጣ እንደሚያቀርቡት ሁሉ ዛሬ ስመጥሩውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 አዜብ ጎላ የተባለች ቀፋፊ እንደ ግል አህያዋ ጫትና እንጀራ ስትጭንበት፣ ቴድሮስ አድሃኖም ቲማቲም ሲነግድበት ለሚያይ ኢትዮጵያዊ በአንጻሩ ሻቢያዎች ዛሬም ድረስ ምን ያህል ጽናትን እንደ ማተብ እንዳሰሩት በቀላሉ ይረዳዋል።

“ወያኔን ሱሪ ያስታጠቀው ሻቢያ ነው” ያለው መንግስቱ ሃይለማርያም ነው። እውነቱን ነው። ወያኔ ምንም እንኩዋን ዛሬ ጉራና የበታችነት ስሜት ተጋግዘው ባደባባይ የቁራ ጩኸት ቢያስጮኹትም እውነታውን በልቡ ስለሚያውቀው ከባድመ ጝጭት ጀምሮ እርቅ ፍለጋ በእንብርክክ ሲማጸን መኖሩንና ከአገራት አልፎ ሃይሌ ገብረስለሴን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎችን፣ ሰዎቹ ሲያልቁበት ደግሞ በደላላ(ስሙን ሲያጣፍጡት ኤጄንሲ እንዲሉት) ሳይቀር አማላጅ ሲልክ እንደኖረ እናውቃለን። መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዎርጊስ እንኳን ባቅማቸው “ሸኣቢያ ቢፈቀደልኝ እዛው ድረስ ሄጀ እማጸነው ነበር” ያሉት ከታች የሽንት ቤት መቀበያ የተገጠመለት ዊልቸር ላይ ተቀምጠው ቀናቸውን እየገፉ ባለበት ሁኔታ ነው።

ዛሬ ወያኔ ከሰማይ በታች ቀረኝ የሚለው አንድ ተስፋ ቢኖር የራሱ የሆነ ሌላ “ጽናት” የሚል ምርኩዝ ላይ ተንጠልጥሎ እንደ ነፍሰጡር ሴ ቀን በመቁጠር ላይ ተጥዶ ውሎ ማደሩ ነው። በወያኔ ስሌት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በረሃ ወርደው ሻቢያን እዚህ ያደረሱት አመራሮች የሻቢያ ከፍተኛ አመራር በሙሉ በ አሁኑ ሰ አት እድሜያቸው ከሰባ በላይ እየዘለቀ ነው። ይህ አመራር ደግሞ መንግስት ከሆነ ቦሃላ የተወለዱት አዲሱ የ ኤርትራ ጀነሬሽን ደግሞ ለሻቢያ የናቅፋ ታሪክ እቁብ ባለመስጠት ድንበር እያቋረጠ ስደትን ዋነኛው መውጫ መንገድ በማድረጉ ዛሬ አዲሲቱ ኤርትራ የ አዛውንቶች አገር ሆናለች። በመሆኑም እንደ ምንም ብለን ኖ ዋር ኖ ፒስ በሚለው መርህ በመጽናትና ሻቢያን በምእራብውያን እርዳታ በማእቀብ ውስጥ እያዳከምን የሚቀጥለውን አምስት እና አስር አመት ያህል አሁን ባለበት ሁኔታ መቆየት ከቻልን ወራሽ አልባው የሻቢያ አመራር በራሱ የተፍጥሮ ህግ ይሞታል፤ ኤርትራንም ያለጦርነት በመውረስና ሌላ የህወሃት ተላላኪ ባንዳ መንግስት በማቆም አስመራ ከተማቸውንና የምጽዋን የባህር ዳርቻወቻቸው ሳይቀር የሸርሙጣ እንደስትሪ እናስፋፋበታለን፤ በዚህም ሲሰማን የኖረውን የበታችነት ቁስል እናወራርድበታለን የሚል ነው።

በአንጻሩ ሻቢያ ወያኔን በተመለከተ የሚያይበት የራሱ የሆነ የጽናት መነጸር አለው። ወያኔ አንድ ብሎ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ከገባበት ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ያይበት የነበረው የበቀል ፖሊሲ የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ በባድመው ጦርነት ከወያኔ ጋር ሊቆም አይችልም የሚለው ድምዳሜ ዋጋ ያስከፈለው ቢሆንም ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ በወያኔና በቀሪው ህዝብ መካከል የተፈጠረው የማይሽር የጠላትነት ሸለቆ ይበልጥ ከግዜ ወደ ግዜ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ለይስሙላም ቢሆን ሲያደናግርባቸው የነበሩት ብአዴንና ኦህዴድ መሰል አድርባይ ፓርቲዎች ከህወሃት ቁጥጥር ውጭ እየሆኑ መምጣታቸው፣ ክልሎች እየፈረጠሙ ማእከላዊ መንግስቱ መዳከሙ፣ ከመለስ ሞት ቦሃላ እርሱን የሚተካ ሰው መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን ራሱ ህወሃት ወደ ሶስት የመከፈሉና ይሕ ነው የሚባል ጠንካራ ማእከላዊ አመራር መጥፋቱ በሌላ አነጋገር ኢህዴግ የሚለው ጭብል ወልቆ እርቃኑን የወጣና የበሰበሰ ህወሃት ብቻውን መቅረቱ፤ ገደብ አልባውና የማይጠረቃው ዘረፋና አገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የዘረኛ አስተዳደር መልሶ እራሱን አናሳውን ቡድን ሊበላው እሳቱ መንተክተክ የጀመረበት ሁኔታ ግልጽ እየሆነ መምጣቱ፤ እስከዛሬ የተንጠለጠለበት የሶማሊያ ጸረ ሽብር አጋርነት እቁብ ተበልቶ ያለቀበት ሁኔታና የምእራባውያንን አስተዳደር ቀስ በቀስ ጀርባቸውን የመስጠታቸው ነገር እስንዲሁም ከምንም በላይ ለሁለት አስርተ አመታት የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ ተጋድሎ ማደጋቸውና ነፍጥ ያነገቡት ሃይሎች ጡንቻ ፈርጥሞ ወያኔን ለግዳይ መጥራት መጀመራቸው፣ በዘረኛ አስተዳደሩ ተማሮ ባገኘው አጋጣሚ መሳሪያውን ሸጦ የሚጠፋ ወይንም አርበኞችን እየተቀላቀለ ነፍጡን በራሱ በወያኔ ላይ ማዞር የጀመረን ጦር ተስፋ አድርጎ መኖሩ የፈጠረው ስጋት፣ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስም በራሱ የፖለቲካ ክንፍ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ በወታደር ካባ እድሜውን ለማራዘም የሞከረበት ሁኔታ እንዳልሰራ ግልጽ ሆኖ የወጣበት ሁኔታ ከመኖሩም በላይ ባለፈው በሌላ መጣጥፍ ለማሳየት እንደሞከርኩት ወያኔ ውርባ አመት ሙሉ ሲጠቀምበት የኖረው ግምገማ የሚባለው ችግሩን መፍቻው መንገድ የማይሰራበት ደረጃ መድረሱና ሌላ አማራጭ መፍቴሄ መፈለጊያ መንገድ የሌለው መሆኑ ወያኔን ጠፍጥፎ ለሰራው ሻቢያ ብቻ ሳይሆን እንደ ደቡብ ሱዳን ለመሳሰሉት ትናትን ለተፈጠሩት አገሮች ሳይቀር ግልጽ ሆኗል።

በሌላ በኩል ሻቢያ ከነ ችግሩም ቢሆን በዚህ ሁሉ በአለማቀፍ ማእቀብ ተጠርንፎም ቢሆም እንኩዋን ሸብረክ የማይል ጠንካራ ማእከላዊ አመራር ያለውና በመጠጥና በሃሽሽ ከደነዘዙ የወያኔ ልጆች የተሻለ ተተኪ ያለው በወያኔ፣ በምእራባውያንና በሱዳኑ አልበሽር ሳይቀር ግልጽና ስውር ድጋፍ የሚደረግላቸው ጸረ ሻቢያ ድርጅቶች ደግሞ የትም ሊደርሱ ካለመቻላቸው ጋር ሲደማመር የጽናት ቀመሩ ከወያኔ ይልቅ ለሻቢያ ይበልጥ እንደሚሰራና ወያኔም እንደ ዳይኖስረስ እራሱን በራሱ የሚበላበት ቀን አፍንጫው ስር እየደረሰ እንደሆነ ዛሬ በድፍን ኢትዮጵያ የሚንተከተከው አልገዛም ባይነት ትልቁ አስረጅ ነው።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events