World News

BBC.com: ኢትዮጵያ፡ ተማሪዎችን ያስከፋው የትምህርት ሚንስቴር ፖሊሲ ጉዳይ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Saturday, 11 November 2017

ኢትዮጵያ፡ ተማሪዎችን ያስከፋው የትምህርት ሚንስቴር ፖሊሲ ጉዳይ

ህዳር 11, 2017
ተማሪዎችን ያስከፋው የትምህርት ሚንስቴር ፖሊሲ ጉዳይ
Image copyrightCHRISTOPHER FURLONG

በቅርቡ ከትምህርት ሚኒስቴር የወጣው መመርያ እያንዳንዱ የከፍትኛ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪ ተማሪ ከመመረቁ በፊት አጠቃላይ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፈተና እንዲወስድ ያስገድዳል።

በመምህራን፣ በህክምናና በጤና የትምህርት ክፍሎች ብቻ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ይህ የምዘና ማረጋገጫ ፈተና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ውሳኔው እንዳደናገራቸው ሲናገሩ ትምህርት ሚኒስቴር ግን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል የወጣን ፖሊሲ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም ሲል ይገልፃል።

የ5 ዓመት ትምህርት በ1 ቀን ምዘና ?

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ምህንድስና 4ተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ጌታሁን* "የተማሪዎች ብቃት በመጨረሻ ዓመት በሚሰጥ ፈተና አይረጋገጥም" ሲል ይሞግታል።

"ሲጀመር መምህራኑ ጥሩ ትምህርት አያስተምሩም። መመዘን ያለባቸው ተማሪዎች ብቻ ኣይደሉም። መምህራኑ በተሻለ ጥራት ሳያስተምሩ ተማሪ ቢመዘን ባይመዘን ምን ዋጋ አለው?" በማለት ይጠይቃል።

ጌታሁን* እንደሚለው "ብዙ ዓመት ለፍቶ ጥሩ ውጤት ይዞ የሚመረቅ ተማሪ መንግሥት አራትና አምስት ዓመት ጠብቆ ብቃት የለህም" ማለቱ አግባብ አይደለም።

በያዝነው የትምህርት ዘመን መባቻ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ክፍለ-ትምህርት ተማሪዎች አጠቃላይ ምዘና መውሰድ አለመውሰድ ላይ እሰጣገባ ገብተው እንደነበር ቢቢሲ መዘገቡ ይታውሳል።

ጌታሁን* ምዘናውን ቢያልፍም በርካታ ጓደኞቹ በተለይ አንዳንዶቹ 3.8 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያላቸው ጎበዝ ተማሪዎች ወድቃችኋል መባላቻው ምዘናው ላይ ያለውን ስህተት በምሳሌነት ይጠቅሳል።

ሌላኛው የ3ተኛ ዓመት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውተር ምህንድስና ተማሪው ሲሳይ* በበኩሉ "እንኳን አምስት ዓመት ጠብቀን አሁን የተፈተነውም ኣይመጥነንም" ይላል።

በአሁኑ ወቅት ለተግባር ትምህርት ወጥቶ የሚገኘው ይሄው የባህርዳር ዩኒቭርሲቲ ተማሪ ምዘናውን የሚቃወምበት ምክንያት አለው።

"ምክንያቱም የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው በፈተና ሳይሆን ትምህርቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚሰጠው? በምን ዓይነት ሁኔታ ነው እያተማርን ያለነው? የሚሉትን ግምት ውስጥ ማስገባት ሲቻል ነው" በማለትም ይጠይቃል።

"ብዙ ልምድ በሌላቸውና ከተማሪዎች ብዙም በማይሻሉ አስተማሪዎች ነው እየተማርን ያለነው። በዛ ላይ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈን ነው የምንማረው፤ ምክንያቱም ምንም አማራጭ የለንም" በማለትም ያክላል።

ይህ የአብዛኛዎቹ ተማሪዎች አስተያየት መሆኑ የሚናገረው ሲሳይ* "አዲሱን መመርያ መውጣት ተከትሎ "ሁሉም ተማሪ 'ምን ታስቦ ይሆን?' በማለት እየጠየቀ ነው" ሲል ይናገራል። "በአጠቃላይ ተማሪው ደስተኛ አይመስለኝም" ይላል።

ምዘናና የትምህርት ጥራት . . . ?

ትምህርት በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በመንግሥት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ሲሆን በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥርና ወደ ተቋማቱ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ግን "ከዚህ በፊት የሕግ ተማሪዎችን፣ መምህራንና የህክምና ተማሪዎችን ስንመዝን ቆይተናል። በሌሎችም ትምህርት ክፍሎች ይህን አሰራር ነው እንዲቀጥል ያደረግነው፤ አዲስ መመርያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የማይቀር የመንግስት ፖሊሲ መሆኑ በማስረገጥም "ሌሎችም ስለሚቀጥሉና በቂ ዝግጅት ማድረግ ስላለባቸው ነው እንደ አዲስ መፃፍ ያስፈለገን" ይላሉ።

ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንም በተመሳሳይ የብቃት ስርዓት እንደሚመዘኑ አክለው ተናግረዋል።

"ከዚህ በኋላ በሙያው ያልተመዘነ መምህር አይሆንም፣ ዳኛም ሐኪምም አይሆንም፤ ፈቃድም አያገኝም።"

እንደ ዶ/ር ጥላዬ እምነት የተዘረጋው የምዘና ስራዓት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መንገድ ነው።

ኣቶ ታፈረ ቢጠና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ጥራት ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለሙያ እንደሚሉት "ይህ ዓይነቱ አሰራር በተለያዩ የውጭ ሀገራት የተለመደና የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ የሚሰራረበት ነው፤

በአግባቡና በስርዓት ከተተገበረ እጅግ ጠቃሚ ነው" ይላሉ።

አዎንታዊ ሚናው እንደሚያመዝን የሚናገሩት አቶ ታፈረ በተጨማሪ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ እንዲኖር እንዲሁም የእርስ በርስ ፉክክርንም ለማስወገድም ይጠቅማል ብለው ያምናሉ።

"አንድ ተማሪ ባዶ ወረቀት ይዞ እንዳይወጣና የሚገባውን እውቀት ሸምቶ እንደወጣ ለማመሳከር ምዘናው ይጠቅማል። እንዲሁም ደግሞ መምህራኖች ሲያስተምሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የሆነ ግንዛቤ ይፈጥራል" ይላሉ።

ፕሮግራሙ ከአንድ ኣመት በኋላ በ2011 ዓ.ም. በሁሉም የትምህርት ክፍሎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል።

 

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events