World News

Goolgule.com: እነ አል-አሙዲ 70በመቶ ሃብታቸውን በማስረከብ ለመፈታት እየተደራደሩ ነው

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Saturday, 18 November 2017

እነ አል-አሙዲ 70በመቶ ሃብታቸውን በማስረከብ ለመፈታት እየተደራደሩ ነው

 
  • ንጉሥ ሳልማን በቅርቡ ከሥልጣናቸው ወርደው በአልጋ ወራሹ ይተካሉ
  • እስራኤል ከሳዑዲ ጋር የመረጃ (የስለላ) ልውውጥ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አለች

በሙስና እና የመንግሥትን ሃብት አለአግባብ በመጠቀም በሚል በቁጥጥር ሥር የሚገኙት የሳውዲ ልዑላንና ሌሎች ታላላቅ ባለሥልጣናት ከእስር ለመውጣት እስከ 70 በመቶ ሃብታቸውን ለመንግሥት ለማስረከብ እየተደራደሩ መሆናቸው ተሰማ። አል-አሙዲ በ30 በመቶ መቀጠል አሳሳቢ ሆኗል። ንጉሥ ሳልማን ሥልጣናቸውን ለአልጋ ወራሻቸው ሊያስረክቡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሳዑዲ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት የጀመረችው እስራኤል ከሳዑዲ ጋር በሚፈለገው መልኩ ለመተባበር ፈቃደኝነቷን አስታወቀች።

በኢትዮጵያ ላለፉት 26ዓመታት ከግብር ነጻ ንግድ በማካሄድ ኢትዮጵያን ሲዘርፍ የነበረው የህወሓት የቅርብ ወዳጅ አል-አሙዲ በሳዑዲ በቁጥጥር ሥር ከዋለ ጊዜ ጀምሮ ደጋፊዎቹ ብዙ ሲዘግቡለት ቆይተዋል። ከአልታሰረም እስከ ተፈትቷል ሲባልለት የነበረው አል-አሙዲ አሁንም በእስር ላይ ይገኛል። የዜጎቹ ጉዳይ ከምንም የማያሳስበው ህወሓት/ኢህአዴግ በተወካዩ ኃይለማርያም አማካኝነት “መንግሥት የሚቻለውን እያደረገ ይገኛል” በማለት ለአንድ ግለሰብ ያለውን ተቆርቋሪነት ይፋ አድርጓል።

የሳዑዲ ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሳውድ በቅርቡ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ከማቀዳቸው ጋር በተያያዘ የአልጋ ወራሻቸውን መቀመጫ ለማደላደል እና በሌሎች የፖለቲካ ምክንያቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሳዑዲ ልዑላንና ከፍተኛ ባለሥልጣናት አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። ክብራቸውን ከሚነካ የመኝታ ሁኔታ እስከ ስቅየት (ቶርቸር) ደርሶባቸዋል እየተባሉ የሚነገርባቸው ታሳሪዎች ንብረታቸው መንግሥት እንዲቆጣጠረው እንደሚደረግ ባለፈው ሳምንት የሳዑዲው አቃቤ ሕግ መናገራቸው ታወሳል።

ዛሬ (አርብ) ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተሰማው ዜና እንደሚያመለክተው አልጋወራሹ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ሁኔታውን ለማረጋጋትና መስመር ለማስያዝ አቅጣጫዎችን እየቀየሩ መሆናቸው ተሰምቷል። ፋይናንሺያል ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ ታሳሪዎቹ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ሃብታቸውን አሳልፈው በመስጠት ከእስር ለመፈታት እየተደራደሩ መሆናቸውን አስታውቋል። ዜናውን ሌሎች የዜና አውታሮች ለማረጋገጥ አልቻልንም ማለታቸው ተሰምቷል።

በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር በድንገት በተጀመረ ጊዜ ከተያዙት በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ባለሃብቶችና ንጉሣዊ ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። እንደተባለው እስከ 70 በመቶ በሚሆነው ሃብታቸው ከእስር ለመፈታት የሚደራደሩ ከሆነ የሳዑዲ መንግሥት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር እያሽቆለቆለ ወደሄደው ካዝናው ማስገባት ይችላል ተብሏል። ድርድሩንም ወደዚህ አቅጣጫ እንዲሄድ ያደረገው ግለሰቦቹን ለመፍታት ከማሰብ ሳይሆን ሃብታቸውን ከመውረስ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ጉዳዩን የሚከታተሉ ያስረዳሉ።

አል አሙዲ ከኃይለማርያም ጋር በወልዲያ ስታዲየም (ፎቶ Addis Fortune)

በአድናቂዎቹና ከእጁ በበሉ “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” እየተባለ የሚሞካሸው አል-አሙዲ 70በመቶ ሃብቱን አስረክቦ ከወጣ “ድርጅቶቼ” በሚላቸው ኩባንዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጽዕኖ ካሁኑ አሳሳቢ ሆኗል። ለአልባሌ ጉዳዮች ከሚያባክነው ገንዘብ እና በሥሩ ከተሰገሰጉት ሞሳኞች ተርፎት በ30በመቶ ለመቀጠል የመቻሉና ኩባንያዎቹንም በዚህ የማስቀጠሉ ጉዳይ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ማስፈኑን ለጎልጉል አስተያየታቸውን ከአዲስ አበባ የላኩ ገልጸዋል። ከዚህ ሌላ ከሙስና ጋር በተያያዘ ታስሮ መፈታት በራሱ የሚፈጥረው ኃፍረትና ቅስም መሰበር ከሰውየው የጤና ችግሮች ጋር ተዳምረው ሁኔታዉን የከፋ ደረጃ እንዳያደርሱት ስጋት አለ።

የአል-አሙዲን “የጽድቅ ተግባራት” ዘርዝረው ለመናገር ቃላት የሚያጥራቸው ግለሰቡ የህወሓት አንጋሽና የዘረፋ ሃብት ተካፋይ ከመሆን አልፎ በጋምቤላ 424 ወገኖች በግፍ ከተጨፈጨፉ በኋላ መሬታቸው በሳንቲም ሲቸበቸብ መሬቱን ከተቀራመቱት ዋንኛ ድርጅቶች መካከል አብዛኛውን የወሰዱት የሕንዱ ካሩቱሪና የአል-አሙዲ ሳዑዲ ስታር መሆናቸውን መዘንጋታቸው ብቻ የአል-አሙዲ ደጋፊዎች ጭንቅላት “በስብ ለመደፈን” በአስረጅነት የሚቀርብ ነው በማለት ተቃዋሚዎቻቸው ይሞግታሉ። በአገር ውስጥ ያሉት የግለሰቡ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ በዳያስፖራም የህወሓት ቀንደኛ ነቃፊ የሆኑ “ከእጃቸው የበላን” የሚሉ ለአል-አሙዲ ጭፍን ድጋፍ የመስጠታቸውን ጉዳይ የህወሓትን አገዛዝ ጋር በተመለከተ የፖለቲካችንን ጭፍን ወገናዊነትን የሚያሳብቅ ነው ይላሉ።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚ/ር ሌ/ጄ ጋዲ ኢዘንኮት (ፎቶ IDF Spokesperson)

ከእስራኤል ጋር የቅርብ ግንኙነት እየመሠረተች ያለችው ሳዑዲ አረቢያ እየወሰደች ላለችው እርምጃ የእስራኤል ሙሉ ድጋፍ አላት የሚሉ መረጃዎች በብዛት ይሰማሉ። የእስራኤሉ ጠ/ሚ/ር ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከተናገሩት በተጨማሪ አልጋወራሹ ልዑል ሳልማን በቅርቡ በምስጢር የእስራኤል የመከላከያ ሚ/ር የሚገኝበትን የቴልአቪቭ ከተማ ጎብኝተዋል እስከሚለው ድረስ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ትኩረትን የሳበ ሆኗል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእስራኤሉ የመከላከያ ሚ/ር ሌ/ጄ ጋዲ ኢዘንኮት፤ ኤልፋ ከተባለ የሳዑዲ የድረገጽ ጋዜጣ ጋር “ታሪካዊ” የሚባል ቃለምልልስ ማድረጋቸው ሁኔታውን በታሳሪዎቹ ጉዳይ የእስራኤል እጅ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ጥያቄ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎታል። በተለይም ሁለቱ አገራት ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሳይኖራቸው አሁን እየተካሄደ ያለው “ትብብር” ከመከላከያ ሚ/ሩ ቃለምልልስ ጋር ተዳምሮ ነው ጉዳዩን “ታሪካዊ” ያስባለው።

የመከላከያ ሚኒስትሩ የኢራንን ጉዳይ አስመልክቶ ከሳዑዲና ከአሜሪካ ጋር ግምባር በመፍጠር አዲስ ዓለምአቀፋዊ የመተባበር ዕድል ተከፍቶልናል ያሉ ሲሆን “አስፈላጊ ከሆነ (ከሳዑዲ አረቢያ) ጋር የመረጃ (የስለላ) ልውውጥ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤ በሁለታችን መካከል በርካታ የጋራ ፍላጎቶች አሉ” ማለታቸው እነ አል-አሙዲ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የሞሳድ ዓይን የት ድረስ ይከተላቸው ይሆን የሚል ጥያቄ በአንዳንዶች ዘንድ አስነስቷል።

ማስታወሻ፤ አላሙዲንን “አንተ” ብለን መጥራታችን ለሚያሳስባችሁ ይህንን እንድታነቡ ይሁን


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events