World News

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው የተገኙበት አካባቢ ምልከታ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Thursday, 26 July 2018

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው የተገኙበት አካባቢ ምልከታ

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው የተገኙበት አካባቢ ምልከታ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብዙዎቻችን እንደሰማነው ይህ አሳዛኝ ድርጊት ሆኖ የተገኘው እዚሁ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ጋር ነው ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ከ2003 አ.ም አንስቶ እስካሁን ድረስ ፕሮጀክቱን በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲመሩት የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መኪና ውስጥ ዛሬ ሞተው እዚሁ መስቀል አደባባይ ተገኝተዋል ።

መረጃው ከተሰማ በኋላም ኢንጂነር ስመኘው መኪና ውስጥ ሞተው የተገኙበት ቦታ ሪፖርተራችን ተገኝቶ ነበር።

ህይወታቸው አልፎ የተገኙበት መኪና መስቀል አደባባይ ቦታ ሆኖ መኪኖች የሚቆሙበት እንዲሁም ወጣቶች ኳስ የሚጫወቱበት አካባቢ ነው።

ሞተው የተገኙበት ወርቃማ ቀለም ያላት ላንድ ክሩዘር መኪና ናት።


ኢንጂነር ስመኘው በቀለ

ኢንጂነር ስመኘው እዚህ መኪና ውስጥ ጋቢና ውስጥ በሹፌር ቦታ ላይ ተቀምጠው ነው ህይወታቸው አልፎ የተገኙት።

ሪፖርተራችን እንደታዘበው አስከሬናቸው ከአንገታቸው ወደ ቀኝ አዘንብሎ የነበረ ሲሆን፥ ኮፍያና ቀይ ዳማ ጃኬትን አድርገዋል።

በዚህ ሁኔታ ነው በአሳዛኝ መልኩ ህይወታቸው አልፎ ስፍራው ላይ የተገኙት ።

ያሉበት መኪና ሪፖርተራችን ስፍራው ላይ ሲደርስ ሞተሩ አልጠፋም ነበር፤ በአስከሬናቸው በኩል ያለው የጋቢና መስኮትም አልተዘጋም ነበር ።

በርካታ የፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በቦታው ላይ ተገኝተው የአሻራን ጨምሮ በርካታ ምርመራን ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በስፍራው ላይ የሆነውን ድርጊት ተላላፈ ሰዎች ከሰሙ በሁዋላ ተላላፊ ሰዎች ተሰብስበው ሲመለከቱ ነበር ሲያለቅሱም ነበር ።

በርካታ የፖሊስ አባላት ቦታው የተለያዩ መሳርያዎችን ተጠቅመው ምርመራ ካደረጉ በሁዋላ በግምት ከቀኑ 5 ሰዓት ተኩል አካባቢ ለተጨማሪ ምርመራ አስክሬናቸው ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በቀጣይ የምርመራው ሂደት ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያውን በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን በተለያየ መንገድ በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። በርካቶች የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን በመጠቀም በህልፈታቸው የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ኢንጂነሩ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሌሎች የሀገሪቱ የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ያሳረፉትን አሻራ እያወሱ ነው።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለን በተለይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጀመር አንስቶ በስፋት በህዝቡ ዘንድ ይታወቃሉ ።

ግድቡንና ኢትዮጵያዊነትን አስተሳስረው የሚናገሯቸው ነገሮች እጅግ አነሳሽ እንደነበሩ እናስታውሳለን ።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን መምራት ከመጀመራቸው በፊት በግልገል ጊቤ የውሃ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በሀላፊነት መርተው ነበር ።

በካሳዬ ወልዴ


ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው የተገኙበት አካባቢ ምልከታ


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events