World News

Satenaw.com: የኢትዮጲያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ከትላንቱ ታሪክ ጋር ስለመታረቅና በነገውን የሩቅ ጉዞ

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Thursday, 26 July 2018

ነዓምን ዘለቀ

በዚህ በዓል ላይ የተገኛችሁ ኤርትራዊያን ወንድምና እህቶቼ

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና የውይይት ተሳታፊዎች

የተከበራችሁ የክብረ በዓሉ አዘጋጆች

በቅድሚያ በዚህ መድረክ ላይ እንድገኝ ስለተጋበዝኩ ከልብ አመሰግናለሁ። በዚህ ዝግጅት ላይ አርበኞች ግንቦት 7ን ወክሎ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው እንግዳ የንቅናቄው የስራ አስፈጻሚ አባልና ዋና ጸሃፊ የሆነው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነበር። ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት ላይ ከኤርትራ መንግስት የተደረገለትን ድንገተኛ ጥሪ ተከትሎ ወደ ኤርትራ በመሄዱ በመካከላችን ሊገኝ አልቻለም።

የበዓሉ አዘጋጆች በዚህ የኤርትራዊያን የበዓል መድረክ ላይ እንድሳተፍ ሲጋብዙኝ ከኔ ይልቅ ስለፍትህ፣ ስለ ዲሞክራሲና ስለኢትዮጲያ አንድነት ሲል ከማናችንም በላይ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለውን አንዳርጋቸው ጽጌን መጋበዙ ትክክል ነው ብዬ ሃሳብ አቅርቤ ነበር። ሆኖም ያ ቀደል ሲል ባልኩት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቶ እነሆ እኔ በመካከላችሁ ተገኝቻለሁ። እዚህ ላይ አንድ ቁምነገር መጠቆም እፈልጋለሁ። ይህ ግብዣ በድንገት የቀረበልኝ በመሆኑ ያዘጋጀሁት ጽሁፍ ያለበቂ ጊዜ፣ ትኩረትና የሃሳብ ስምረት የተከናወነ መሆኑን አስቀድሜ ማሳወቅ እፈልጋለሁ።

በመጀመሪያ የኢትዮጲያን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድንና የኤርትራን መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በአርበኞች ግንቦት 7 ስም እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ። በሁለቱ አገሮችና ህዝቦች መካከል ለ20 አመታት ፈርሶ የነበረውን የሰላምና የወዳጅነት ድልድይ እጅግ ቆራጥና ድፍረት በተሞላበት ዕርምጃ በ20 ቀናት ውስጥ መልሰው መገንባት መቻላቸው በርግጥም የሚያስመሰግናቸው ነው። ነገሮች በሃይለኛ ፍጥነት እየተቀያየሩ ነው። በኢትዮጲያና በኤርትራ ህዝብ መካከል የታየውን የደስታ፣ የፍቅርና የፈንጠዚያ መንፈስ ማየቱ የሰው ልጅ መደበኛ አዕምሮ ሊገምተውና ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ሆኖ ነበር የታየው። ባለፉት 20 ቀናት ውስጥ የሆነውን ክስተት ባጭሩ ተአምር ነበር ብሎ ማለት ይቻላል። ያለፉት 20 አመታት ለሁለቱም አገሮች ህዝቦችና መንግስታት አስጨናቂና የክስረት ዘመን የሆኑትን ያክል አሁን የተፈጠረው አዲስ መግባባትና ወንድማዊ ፍቅር ደግሞ የነገውን አዲስ ተስፋና ብሩህ ዘመን አብሳሪ ነው ማለት ይቻላል፡

የኤርትራና የኢትዮጲያ ህዝቦች ሃሳባቸውንና ስሜታቸውን በግልጽ ተናግረዋል። ለዓመታት የተነፈጉትን የርስ በርስ ፍቅራቸውንና ናፍቆታቸውን በማደስ ለሰላምና ለወዳጅነት ያላቸውን ዝግጁነት አሳይተዋል። በኤርትራም ሆነ በኢትዮጲያ ውስጥ ለሁለቱም ርዕሰ ብሄሮች ህዝቡ ያሳየው የጋለ አቀባበልና ፍጹም ቤተሰባዊ ፍቅር በርግጥም የሁላችንንም ልብ ኮርኩሮታል።በተለያዩ መንገዶች የሁለቱም አገር ህዝቦች ያሳዩት የመነፋፈቅና የመከባበር መንፈስ ለ20 አመታት በላያቸው ላይ የተጋረደው የመለያየት ግድግዳ ሊያስቆመው እንዳልቻለ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው። ይህ ምስክርነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው አንድ ዕውነት ቢኖር የቱን ያክል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቢነዛም፣ የቱን ያክል የጥላቻ ስብከትና የተሳሳተ መረጃ ቢሰራጭም በኤርትራዊያንና በኢትዮጲያዊያን ልብና መንፈስ ውስጥ ያለው ቁርኝት ከብረት የጠነከረ ምንም ምድራዊ ሃይል ሊነቀንቀው የማይችል መሆኑን ነው። ስር የሰደዱና ዘርፈ ብዙ የሆኑት የታሪክ፣ የባህል፣ የማህበራዊ ህይወትና የስትራቴጂ ትስስራችን ሁሌም ቢሆን አሸናፊ ሆነው መውጣታቸው የማይቀር ሀቅ ነው። እርስ በርስ በተወራረስነው የደም፣ የጋብቻ፣ የባህል፣ የሰላም ጥማትና የተሻለ የወደፊት ህይወት ህልም ዕጣ ፈንታችን  ለዘላለሙ በጋራ የተገመደ ህዝቦች ነን።

የሁለቱ አገር ህዝቦች ከድህነት ብልጽግናን፣ ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን ይመኛሉ። ፍቅርና ሰላም ደግሞ በመጨረሻ ላይ አሸናፊ ሆነዋል። የሁለቱ አገር ህዝቦች ከጸብና ከፉክክር ይልቅ መተባበርንና አንድነትን እንደሚፈልጉ በአስመራና በአዲስ አበባ ከተማዎች ላይ ባሳዩት ተዓምራዊ የአቀባበልና የድጋፍ ሰልፎች በግልጽ አስመስክረዋል። አሁን በአዲስ ምዕራፍ የታሪክ ላይ እንገኛለን። ይህ ምዕራፍ ለኢትዮጲያ፣ ለኤርትራና አልፎም ለአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የብልጽግና ዘመን አብሳሪ የሆነ ልዩ ምዕራፍ ነው።

በዚህ አጋጣሚ የኤርትራ ህዝብና መንግስት ለኛ አርበኞች ግንቦት 7 ላደረጉልን ከፍተኛ ትብብር በንቅናቄአችንና በአባላቱ ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ። ኢትዮጲያና የኢትዮጲያ ህዝብ ፍጹም ጨለማ ውስጥ በነበረበት አስጨናቂ ወቅት ከጎኑ የቆመችለት ብቸኛ አለኝታ አገር ኤርትራ ስለነበረች ለዘለዓለሙ ባለውለታችን ናት። የኢትዮጲያ ህዝብ በጨቋኞች መዳፍ ውስጥ ወድቆ ለነጻነትና ለፍትህ ሲታገልና ሲሰቃይ አለም ሁሉ ጀርባውን በሰጠው ጊዜ አለንላችሁ ያለችን አንድ ብቸኛ አገርና ህዝብ ኤርትራ ነበረች። በኢትዮጲያ ውስጥ የነበረው አምባገነን ስርዓት እኛ ኢትዮጲያዊያን ለነጸነታችንና ለክብራችን የምናደርገውን ትግል ለማፈንና ለማኮላሸት የመከላከያ፣ የደህንነትና የገንዘብ አቅሙን በመጠቀም አለም አቀፉን ማህበረሰብ በማወናበድና አልፎም ዕጅ በመጠምዘዝ ረዥም ርቀት ተጉዟል። በዚህ ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ምድረ በዳ ላይ ሆነን ነበር ኤርትራ የተስፋ ደሴት ሆና ያስጠጋችን፣ ያስተናገደችን። ከሚደርስባቸው ጭቆናና በደል ሸሽተው ወደ ኤርትራ ምድር ለመጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ የኔና የናንተ ኢትዮጲያዊያን የነጻነት ተዋጊ ወንድሞችና እህቶች ጥላ ከለላ የሆነችን ኤርትራ ናት። ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለሰላም ባደረግነው መራራ የትግል አመታትም ኤርትራ ከሆናችን አልተለየችም ነበር። ጨካኙንና ዘረኛውን የአናሳ ቡድን ለመታገልና ለመጣል ባደረግነው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ አብራችሁን በጽናት በመቆማችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

እኛም የአርበኞች ግንቦት 7 አመራርና አባላት ኤርትራ ላይ የተጣለውን ኢፍትሃዊ ማዕቀብ ከመቃወም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቻልነው ሁሉ ለኤርትራ ህዝብና መንግስት ድጋፋችንን ስንገልጽና አጋርነታችንንም ስናሳይ ቆይተናል።

ላለፉት አስር አመታት በኤርትራ መሬት ላይ ሆነን የምናደርገውን የነጻነት ትግልና የኤርትራ መንግስት ለዚህ ትግል ያደረውን ኣዎንታዊ ድጋፍና አቋም አስመልክቶ በኢትዮጲያ ውስጥም ሆነ በውጭ አለም ለሚኖረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጥና የማንቃት ስራ ስንሰራ ቆይተናል። በተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎችና የብዙሃን መገናኛ መድረኮች ላይ የኤርትራ መንግስት እንደመንግስት ያገሩን ያጭርና የረዥም ጊዜ ዘላቂ የስትራቴጂ ጥቅሞቹን እሳቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ይንቀሳቀሳል እንጂ ኢትዮጲያ ላይ ያነጣጠረ ምንም አይነት አፍራሽ የጥላቻ መርህና አክሳሪ መንፈስን መሰረት ያደረገ ዕርምጃ የመውሰድ ቅንጣት ታክል ፍላጎት እንደሌለው ደጋግመን አስገንዝበናል።  የተለያዩ የውይይት መድረኮችንና ኢሳትን በመሳሰሉ የብዙሃን መገናኛዎች ላይ የሚደረጉ ቃለ መጠይቆችን( ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ኢሳት ካደረገውና ኤርትራን በበጎ መልኳ ለህዝብ ካቀረበው ፕሮግራም አንስቶ) በመጠቀም ብዙ በሀገር ውስጥ የሚኖሩም ይሆኑ በውጭ ያሉ ኢትዮጲያዊያን ኤርትራንና መንግስቷን አስመልክቶ የነበራቸውን መሰረተ ቢስና አሉታዊ አመለካከት ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን በሰፊው ሰርተናል። በኢትዮጲያና በኤርትራ ጉዳይ ላይ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ሆን ተብለው የሚናፈሱ ውዥንብሮችና ቅጥፈቶች ዕውነት አደባባይ እንዳትወጣ አፍነዉ ይዘዋት መቆየታቸው ዕሙን ነው። በሀሰት የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ውስጥ የመጀመሪያዋ ሰለባ ሁልጊዜም ዕውነት ናትና።

በሁለቱ አገሮች ውስጥ ያለውን እጅግ ውስብስብ የሆነ ጉዳይ በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ ማካተት አይቻልም።ኤርትራ የኢትዮጲያ አንድ አካል ናት ብለው ከልባቸው በማመን በጀግንነት የተዋደቁና የተሰው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጲያዊያን እንዳሉ ይታወቃል። በተመሳሳይ መልኩም የኤርትራን ነጻነት ለማወጅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ሕይወታቸውን መስዋዕት እንዳደረጉ እናውቃለን። ጉዳዩ ለኢትዮጲያዊያኑ የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝቦች አንድነት መረጋገጥ ሲሆን ለኤርትራውዊያን ደግሞ ነጻነታቸውን ዳግም ለመጎናጸፍ ያደረጉት አግባባት የነበረው ትግል ነበር። ይህን ተከትሎም በአፍሪካ ውስጥ የመጨረሻ ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት ተካሄደ። የኔ ትውልድ የወረሰውም የዚህን ታሪክ መጥፎ ቱሩፋት ነበር።

“ወርሰናል” ያልኩበት ዋናው ምክንያቴ እኔ በተወለድኩበት ሰዓት በሁለቱ ወገኖች መካከል ሊኖር የሚገባው የሰለጠነ ውይይት ቀርቶ ጦርነት የመጨረሻና ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበበት ወቅት ስለነበር ነው። ከልጅነቴ አንስቶ ተከታታይ ስርዓቶች በኢትዮጲያ ውስጥ ሲፈርሱ አይቻለሁ። የነኚህ ስርዓቶች መፍረስ ሂደት የጀመረው ግን እኔ ከመወለዴ ቀደም ብሎ ነበር ማለትም ይቻላል። ከ40 አመታት በላይ በጣሊያን አገዛዝ ስር የቆየችውንና ለ10 አመታት ደግሞ በእንግሊዝ ወታደራዊ ሞግዚትነት ስትተዳደር የነበረችውን ኤርትራን በልዩነቷ ዕውቅና ሰጥቶ የተመሰረተው የፌዴሬሽን ስርዓት መፍረስ የሂደቱ ቀዳሚ ክስተት ነበር። ይህ ኤርትራን ከሌሎቹ የኢትዮጲያ ክፍሎች ልዩ የሚያደርጋትን ታሪክ ዕውቅና ባለመስጠትና በግልጽ ውይይት ካለማስተናገድ የተነሳ በተከታታይ የመጡት ስርዓቶች ኤርትራንና ህዝቧን ለማስገንጠልና ለነጻነት ትግል የጋበዙ ነበሩ።

ይህን የታሪክ ዕውነት መቀበልና የኤርትራን ህዝብ የነጻነት ፍላጎት ማክበርና መቀበል ለአብዛኛው ኢትዮጲያዊ በቀላሉ የሚዋጥ ኪኒን አይደለም።እኔም ራሴ ብሆን ይህንን ዕውነት ለመቀበል ረዥም ጊዜ ወስዶብኛል። ይህ ለኔ በህይወቴ ካጋጠሙኝ ፈተናዎች ሁሉ ትልቁ ፈተና ነበር። ነገሩን ውስብስብ ያደረገብኝ ደግሞ ጉዳዩ ከቤተሰቤ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለሆነ ነበር። አባቴ ኮሞዶር ዘለቀ ቦጋለ የኢትዮጲያ ባህር ሃይል የመጀምሪያ ምሩቅና ከፍተኛ መኮንን የነበረ ሲሆን በኋላም የኢትዮጲያ የባህር ወደቦች ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ ያገለገለ ሰው ነበር። በጊዜው አባቴ አብዛኛውን ህይወቱን ያሳለፈው የባህር ሃይሉና የወደብ አስተዳደሩ ማዕከል በነበሩት አሰብና ምጽዋ ነበር።በነኚህ ረዥም የስራ ዘመናት ውስጥ አባቴ ወደቦቹን ከማስፋፋት በተጨማሪ ሁለት ከተሞችን  ትላልቅ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ቀን ከሌሊት ይሰራ የነበረበት ወቅት ነበር።  ከአሰብ በ30 ኪሎ ሜት ርቀት ላይ በምትገኘው የሃሌብ ከተማ ውስጥም አንድ የማሪቴም አካዳሚና ዘመናዊ  የመርከብ ማደሻና  ጀልባ ፋብሪካን ለመገንባት በተደረገው ጥረት ውስጥ ቀዳሚ ሚና ነበረው።አብዛኛዎቹ የአባቴ ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች በኢትዮጲያ ባህር ሃይል፣ ምድር ጦርና አየር ሀይል ውስጥ ተመድበው የሰሩና ኤርትራ ውስጥ የተሰው ናቸው። ( ከእነኚህም መካከል ከአባቴ ጋር የአንድ ኮርስ ምሩቅና ጓደኛ የነበሩት ኮሞዶር  በለገ በለጠና ኮሞዶር ጌታቸው በ1990 ምጽዋ ላይ በተካሄደው ታላቅ ጦርነት ላይ የተሰዉት)። በልጅነቴ ዘመን በሙሉ ይህ አባቴ የሚደክምላት፣ ዕንቅልፍ አጥቶ የሚሰራላት አገር አንድ ቀን ትገነጠላለች የሚል ሃሳብ በፍጹም በአዕምሮዬ መጥቶ አያውቅም።

ይህንን ሁሉ ካልኩ በኋላ ግን አሁን ለደረስንበት የሰላምና የወዳጅነት ደረጃ የራሳቸውን ሚና ተጫውተው ላለፉ ባለራዕይ  ግለሰቦች ዕውቅና መስጠት ይገባል ብዬ አምናለሁ። ምንም እንኳን ጥረታቸውና ህልማቸው በጊዜአቸው ዕውን ሆኖ ባያዩትም የነሱን ስም ማንሳትና ዕውቅና መስጠት ታሪካችንን ሙሉ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ። ከፍተኛ ዕልቂትና የጦርነት ወከባ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እነኚህ ግለሰቦች ወደ ትክክለኛውና ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ ወደሚችለው አቅጣጫ ለማመላከት ሞክረዋል። በርግጥም እኛ ዛሬ ለደረስንበትና ልናጣጥም ለተዘጋጀነው የዚህ ሰላምና ወዳጅነት ዕውን መሆን ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ ብዙ ኢትዮጲያዊያን እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል።

ዶክተር አቢይ አህመድ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የጋበዟቸው ዕለት የልጅነት ጓደኛዬ የሆነውንና ኤርትራ ውስጥ የቀድሞው ጦር የሁለተኛ አብዬታዊ ሰራዊት አዛዥ የነበሩት የሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶን ልጅ ደረጀ ደምሴን አነጋግሬው ነበር። “ይህ ያባቴ ራዕይ ነበር” ነው ያለኝ። ጄኔራል ደምሴ በጊዜው የነበረውን የአምባገነኑን የመንግስት ሃይለማሪያምን አገዛዝ ለመጣል ከኢፒ ኤል ኤፍ ጋር ያደረጉትን የሰላም ድርድርና የተኩስ አቁም ስምምነት ብዙዎች በበጎ አይን አላዩትም ነበር። እንደ ክህደትም ቆጥረውት ነበር። ደረጀ እንዳለኝ “ዕውነተኛ የጦርነት እሳት ውስጥ አልፈው አስከፊ ገጽታውን የተመለከቱ ግለሰቦች በወንድሞቻችን ላይ ያወጅነው ጦርነት ለችግሩ በፍጹም መፍትሄ እንደማይሆን ያመኑበት ጉዳይ ነበር ” ሲል ነበር ያወጋኝ። ታዲያም እንደዚህ አይነቶቹ ሰዎች ነበሩ ዛሬ የደረስንበትን ደረጃ አስቀድመው የተነበዩ አርቆ አስተዋዮች። ችግሩ ዘመን ተሻጋሪ ህልም ያለው አንድ ነቢይ በሺዎች የሚቆጠሩ ካፍንጫቸው በላይ ማሰብ በማይችሉ ጠባቦች የተከበበ መሆኑ ነው።

ይህ የደረጀ አባባል የደርግን ስርዓት በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ  የተያዙት የአየር ሀይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ በጊዜው እስር ቤት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አስታወሰኝ። “እንዴት ከሽፍቶች ጋር ትደራደራለህ” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ጄኔራሉ ሲመልሱ” ከነሱ ጋር ቁጭ ብለን በመወያየት ችግራችንን መፍታት አለብን” ነበር ያሉት። በተመሳሳይ መልኩ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመን የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት እንደ ጄኔራል ከበደ ገብሬ በኋላም የመከላከያ ሚኒስትር፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሃብተወልድን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የፌዴሬሽኑን መፍረስ በመቃወም ሃሳብና ስጋታቸውን ለንገሱ ነገስቱ ማካፈላቸው የታሪክ ሀቅ ነው። ጄኔራል አማን አንዶምም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ሃሳብ አቅርበው ነበር። ሆኖም ግን የነኚህ ሁሉ አርቆ አሳቢዎች ምክር ብዙም የጠለቀ ዕውቀት በሌላቸው የፖለቲካ መሪዎቻችን ተኮላሽቶ ቀረ። እነኚህ መልካም ጥረቶች ስርዓቶቹ ከሚያራምዱት ትርክት በተጻራሪው የቆሙ ነበሩ። ጦርነት የስልጣን ዕድሜን ማራዘሚያ አንዱና ዋነኛው መንገድ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ጠባብ የሆነ አመለካከት የመጀመሪያ ሰለባ የሆነው ደግሞ በኤርትራ ተራራዎችና ሸለቆዎች፣ በአስመራ መንገዶችና አደባባዮች፣  በከረን፣ በምጽዋና ሌሎች ትናንሽ ከተሞች ውስጥ የደማው፣ የቆሰለውና የሞተው ተራው የኢትዮጲያና የኤርትራ ህዝብ መሆኑ የሚያሳዝን መራራ ሀቅ ነው።  ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባና በአስመራ አደባባዮች ላይ ሲፈነዳ የያየነውም የነኚህን ህዝቦች የታመቀና የተዳፈነ የፍቅርና የናፍቆት ገሞራ ነበር።

በአሁን ሰዓት ላይ የቆምንበትን መስቀለኛ መንገድ በመተው ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘን እየሄድን እንገኛለን። ሆኖም አንድ ማወቅ ያለብን ነገር “ይህ የያዝነው መንገድ ወዴት እንዲወስደን እንሻለን? የመጨረሻው መዳረሻችን የት ነው?” ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ ግንዛቤና መልስ ሊኖረን ይገባል። አርበኞች ግንቦት 7 ሁለቱ አገራትና ህዝቦች ስትራቴጂካዊ ትብብር በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይኖራቸው ዘንድ  አቋሙን ግልጽ አድርጎ አስቀምጧል። የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን ከማፋጠንና በአካባቢው የሚያንዣብበውን የደህንነት ስጋት ከመዋጋት አንስቶ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ የተመሰረተ አስተማማኝ ግንኙነት በሁለቱ  አገሮች መካከል መፍጠርን አስመልክቶ ንቅናቄአችን አርበኞች ግንቦት 7 ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አስቀምጧል። ኢትዮጲያና ኤርትራ ሁለት ሉዓላዊ አገሮች ናቸው።ይህ ዕውነት ኢትዮጲያዊያን ዕውቅና ሊሰጡትና ሊቀበሉት የሚገባ ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ ግን እነኚህ አገሮች ከሌላው አለም ሁሉ ለየት የሚያደርጓቸው የራሳቸው ባህሪያት አሏቸው።  አመጋገባችን፣ አለባበሳችን፣አነጋገራችን፣ የምንወደውና የምንጠላው ነገር፣ ሳቃችን፣ ደስታችን፣ ለቅሶአችን፣ ጸሎታችን፣ጭፈራችን፣ ሀዘናችን፣ በዓላት አከባበራችንና እርስ በርሳችን የምናሳየው መደጋገፍ ሁሉ ተመሳሳይ ነው። አንዳችንን ካንዳችን መለየት እንኳን አይቻልም። በመሆኑም አሁን መመለስ ያለብን ጥያቄ “ይህን ሁሉ አንድ የሚያደርገንን እሴትና ማንነት ጠብቀን አንዱ የሌላውን ነጻነትና ብሄራዊ ማንነት ሳይጋፋ እንዴት ወደፊት በጋራ እንራመድ?” የሚለው ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 በመላው አለም ያሉትን አባላቱን በአካባቢያቸው ካለ የኤርትራ ማህበረሰብና መሪዎች ጋር እንዲሁም ከኤርትራ ኤምባሲዎች ጋር በቅርበት እንዲሰሩና የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በኢትዮጲያዊያንና በኤርትራዊያን መካከል የተፈጠረውን ክፍተት እንዲሞሉ በማበረታታት ረገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በኤርትራ የነጻነት ቀን፣ በኤርትራዊያን ክብረ በዓል ላይና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች ላይ በመገኘት የጋራ ግንዛቤና መናበብ እንዲፈጠር የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

የሁለቱን አገሮች ህዝቦች የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ ላለፉት አስር አመታት በአደባባይ በድፍረት ስንናገር የነበረው ህልማችን ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ዕውን ለመሆን የበቃበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ ውጤት ደግሞ በእጅጉ እንኮራለን። የምንኮራው ግን “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” ከሚል ስሌት በተነሳ ኤርትራ በትግላችን ዘመን የደገፈችን ብቸኛዋ አገር ስለሆነች አይደለም። ይልቁንም በሚከተሉት ሁለት ኣበይት ምክንያቶች ነው። አንደኛ፣ ከቅርብ አመታት በፊት በተቀሰቀሰውና ከሁለቱም ወገኖች ለመቶ ሺዎች ህይወት መጥፋት ሰበብ የሆነና የሚሊዮኖችን ኑሮ ያመሳቀለ ጦርነት ቢደረግም፣ አሁንም በሁለቱ አገሮች ህዝቦች መካከል ለረዥም ዘመን ስር የሰደደና በቀላሉ ሊበጠስ የማይችል ጥብቅ ማህበራዊ ግንኑነት በመኖሩ እንጂ። የኤርትራና የኢትዮጲያ ዕጣ ፈንታ እስከወዲያኛው የተቀላለፈ ነው።ዋናው ነጥብ እነኚህን የሁለት አገር ህዝቦች ያስተሳሰረ የረዥም ዘመን ግንኙነትና ወዳጅነት እንዴት በአዲስ መልክ አጠናክሮ፣ ጥልቅ ግንዛቤ፣ መተማመንና የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ስሌት ውስጥ ባስገባ መልኩ ወደፊት እንራመድ የሚለው ነው። ይህ ስታራቴጂካዊ ትብብር ለሁለቱ አገሮች የወደፊቱ ትውልድ መልካም ቱሩፋትን ታሳቢ ያደረገ፣ የረዥን ጊዜ ትልምን የሰነቀና የጋራ ብልጽግናን ከግንዛቤ ያካተተ መሆን ይኖርበታል።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የዓለም አቀፉ ወቅታዊ ሁኔታ ስለሚያስገድደን ነው። አሁን ያለንበት አለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተወሳሰበና ጊዜ እየጠበቁ የሚፈነዱ ግጭቶች በቀጠናውም ሆነ ከቀጠናው ባሻገር የሚፈጠሩበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። እነኚህን ከፊት ለፊታችን የተደቀኑብንን ግልጽና ስውር ችግሮች ለመመከትና ብሎም ለማሸነፍ የሁለቱን አገሮች የሰውና የተፈጥሮ ሃይል ባንድ ላይ መጠቀም አማራጭ ሳይሆን የጋራ ህልውናችን ጉዳይ በመሆኑም ጭምር ነው። ድህነት፣ የኢኮኖሚ ቆሞ ቀርነት፣ የከባቢ አየር ለውጥና አካባቢያዊ ብክለት የጋራ ችግሮቻችን ናቸው። እነኚህን ለመቋቋም ደግሞ የጋራ ጥቅሞቻችንን ሊያስጠብቁና በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ የሰላምና የደህንነት ዋስትና ለመፍጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ የደህንነት፣ የመከላከያና የኢኮኖሚ ትብብሮችና ተቋማት መፍጠሩ ግድ ይላል። ይህን ማድረግ ከቻልን በአካባቢው ላይ የሰላም ጠንቅ የሆኑ አክራሪ ሃይሎችን፣ የሽብር ቡድኖችንና ከፍተኛ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚከናወንባቸው የቀይ ባህርና የህንድ ውስቅያኖስ ላይ የሚፈጸሙ የባህር ላይ ውንብድናዎችን ( ፓይረሲ) መቆጣጠር ይቻላል።ኢትዮጲያና ኤርትራ በቀንዱ ዙሪያ በጋራ የሚጋሯቸው የጂኦ-ስትራቴጂክና የጂኦ-ፖለቲካል ጥቅሞች አሏቸው። ይህ በመሆኑም ነው ባጭርና በረዥም ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉን መንግስታዊና ኢ-መንግታዊ ሃይሎች የሚመሩትን የውጭ አደጋ ለመከላከል የግድ የጋራ ስትራቴጂካዊ ትብብር ማድረግ ያለባቸው። እነኚህንና የመሳሰሉትን የጋራ ጉዳዮች ነበር አርበኞች ግንቦት 7 ላለፉት አስር አመታት ሳይታክት ሲያሳስብና ግንዛቤ ሲያስጨብጥ የቆየው።

በመጨረሻም ፍትህ፣ ነጻነትና አርነት የሚባሉት እሴቶች በሁለቱም አገር ህዝቦች ህይወት ላይ የመተግበራቸው ጉዳይ መሰረታዊ ነው ብለን እናምናለን።የዜጎች ነጻነትና ፍትህ ባልተከበረበት ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ማለት ዘበት ነው። ስለሆነም በሁለቱም አገሮችና አልፎም በአካባቢው ፍትህንና አርነትን የማስፈን ስራ መስራት ይጠበቅብናል።

በዶክተር አቢይ አህመድና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተጀመረው የሰላምና ዘርፈ ብዙ የትብብር ስምምነት የሁለቱን አገሮችና ህዝቦች ህይወት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና ለዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ህብረትና ወዳጅነት መሰረት የጣለ ሆኗል።ይህ ለውጥ በሁለቱ አገራት መካከል “ሰላምም ጦርነትም የሌለበት”በሚል የቆየውንና ይህንን “ደም አልባ ጦርነት” ለማካሄድ ይወጣ የነበረውን የሰው፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ሃይል የተራውን ህዝብ ህይወት ሊለውጡ ወደሚችሉ ሰላማዊ ፕሮጄክቶችና መርሃግብሮች ማሸጋገር የሚቻልበትን መንገድ አመቻችቷል። በርካታ ተግዳሮቶች ከፊታችን እንዳሉ ይታወቃል። ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣበት የሚችልና ጥበብ የተሞላባቸው መልስ የሚሹ ከባድ ፈተናዎች ይገጥሙናል። እያንዳንዷ ዕርምጃችን አንዱ የሌላውን ጥቅም ባልተጋፋ መልኩ በጋራ የሚጠቀምበትን ግልጽና ዝርዝር ስራዎችን መስራትና ይህንንም ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርብናል።ይህ የተጀመረ የሰላምና የትብብር ጉዞ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል።

በሌላ አነጋገር ይህን የሰላምና የትብብር ስምምነት በዘላቂና አስተማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም የበሰለ የፖለቲካ ዕውቀት፣ ካለፉት መሪዎች ስህተት መማርንና ትልቁን መዳረሻ ብለን የያዝነውን ግብ ላፍታም ቢሆን አለመዘንጋት ያስፈልጋል።ትልቁን ስዕል አለመርሳት። ትዕግስት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ የፖለቲካ ጥበብ፣ መተማመንን ማጠናከርና የሁለቱን አገር ዜጎች መደገፍና ማበረታታት ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። ያለፉት ሀምሳ የጥፋት አመታት ካደረሱብን ጉዳቶች ሁሉ በርስ በርስ መተማመን ላይ ያደረሱት ጉዳት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል።

ወደፊት ሊሚፈጠሩ ችግሮችንና አለመግባባቶችን ስርዓትና ግልጽነት ባለው መንገድ የሚያስታርቁና የሚዳኙ ከሁለቱም አገሮች የተውጣጡ የጋራ ተቋማት ከወዲሁ መመስረት አለባቸው። የንግድ፣ የባህል ልውውጥ፣የኮሚኒኬሽንና ነጻ የህዝብ መዘዋወሮችን አስመልክቶ ህዝቡ ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል።ለህዝብ የሚሳነው ምንም ነገር የለምና። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሁለቱን አገራት ጥልቅና ጠንካራ ግንኙነት አስመልክቶ በአንድ ወቅት  እንዳሉት ” ፍቅር ካለ በሰማይ መንገድ አለ” ነውና።

አመሰግናለሁ

ሰላም፣ ፍቅርና ዘላቂ ወዳጅነት ለኢትዮጲያና ለኤርትራ ህዝቦች!

 

(ማስታወሻ፦ይህን በእንግሊዘኛ የቀረበ ጽሁፍ ወደ ጊዜውን ወስዶና በአጭር ጊዜ ውስጥ አማርኛ በመተርጎም ለአንባቢያን እንዲቀርብ ለላከልኝ ለአርበኛ ታጋይ እዝራ የአርበኞች ግንቦት 7 የሬድዮ ዝግጅት ሃላፊ የላቀ  ምስጋና አቀርባለሁ።)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events