World News

Ethsat.com: በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃላፊዎች በጦር መሳሪያ ንግድና በሌሎች የሙስና ወንጀሎች ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገለጸ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Friday, 03 February 2017

በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃላፊዎች በጦር መሳሪያ ንግድና በሌሎች የሙስና ወንጀሎች ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 25 ፥ 2009)

February 02, 2017

በሶማሊያ ተሰርቶ በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ አመራርነት የተቀመጡ ሃላፊዎች በጦር መሳሪያ ንግድና ሌሎች የሙስና ወንጀሎች ውስጥ ተሰማርተው መገኘታቸውን የሃገሪቱ መገኛኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።

ለበርካታ አመታት በሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰራዊት በሃላፊነት በማገልገል ላይ ያሉ ሃይሌ ገብሬ በዚህ ህገወጥ ድርጊት በመሰማራት ከፍተኛ ንብረት በማካበት ላይ መሆናቸውን ሱና ታይምስ የተሰኘ ጋዜጣ የአመራሩን ፎቶ በማስደገፍ ለንባብ አብቅቷል።

በቅፅል ስማቸው በሶማሊውያን ዘንድ ጀኔራል ገብሬ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት እኝሁ ወታደራዊ መኮንን ከሶማሊያ መንግስት ጋር በመመሳጠር የጸጥታ ድጋፍ የሚለግስን ገንዘብ እየመዘበሩ እንደሚገኝ ጋዜጣው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሃይሌ ገብሬ የቅርብ ባልደርቦች ዋቢ በማድረግ ለንባብ አብቅቷል።

በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማግኘትና በሶማሊያ መንግስት ውስጥ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ የሃገሪቱ ባለሃብቶች ለእኚሁ ወታደራዊ መኮንን የገንዘብ ጉርሻን እንደሚያቀርቡም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአመታት በፊት ወደ ሶማሊያ ከተሰማራ ጊዜ ጀምሮ በሃገሪቱ የሚገኙት ወታደራዊ አመራሩ በቤይና ባኮል ተብለው በሚጠሩ የደቡብ ሶማሊያ ግዛቶች የአነስተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውስጥ መሰማራታቸውምን ጋዜጣው ዘግቧል።

ለተለያዩ የሶማሊያ ታጣቂ አጀንዳዎች የጦር መሳሪያን ለሽያጭ በማቅረብ ይታወቃሉ የተባሉት ሃይሌ ገብሬ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 በሶማሊያ የሚገኙ ታጣቂዎች በኬንያ ድርድር በጀመሩ ጊዜ የኢትዮጵያ ተወካዮ ሆነው መቅረባቸውን ሱና ታይምስ አመልክቷል።

ከእኚሁ የመንግስት ተወካይ ዙሪያ በርካታ ወታደራዊ አመራሮች ይገኛሉ ሲሉ የዘገበው ጋዜጣው በቅፅል ስማቸው ጀኔራል ገብሬ የሚባሉት አመራር በቅርቡ በጅቡቲ ወደብ በኩል ከዱባይ የኮንስትራክሽን ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ማስገባታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

በጅቡቲ እና ዱባይ የሚገኙ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ዘገባን ያቀረበው ጋዜጣው ወታደራዊ መኮንኑ በዘመዳቸው በኩል የሚያስተዳደሩት የንግድ ተቋም በተባበሩት አረብ ኤሜሬት እንዳላቸውም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከ10 አመት በፊት ቁጥሩ ያልታወቀ ሰራዊትን በሶማሊያ በማሰማራት በወቅቱ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት በሚባለው ታጣቂ ሃይል ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷ ይታወሳል።

ይኸው ወታደራዊ ሃይል አሁንም ድረስ አልሸባብ ከተሰኘ ታጣቂ ሃይል ጋር ውጊያን እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከወራት በፊት ወደ አራት ከሚጠጉ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቃ መውጣቷን ሲዘግብ ቆይቷል።

ወደ አራት ሺ አካባቢ የሚጠጉ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት ስር ተሰማርቶ በሚገኘ የሰላም አስከባሪ ልዑክ ስር ቢታቀፉም ቁጥራቸው ያልታወቀ ወታደሮች አሁም ድረስ የተናጠል ውጊያን እያካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሰራዊቱ ዙሪያ ዘገባን ያቀረቡ ሱና ታይምስ ጋዜጣ ወታደራዊ ሃላፊው ሃይሌ ገብሬ ከምዕራባዊያን ሃገራት ለኢጋድ የሚቀርብ ድጋፍን ከሶማሊያ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ህገወጥ ሃብት ማካበታቸውም አክሎ ገልጿል። በጉዳዩ ዙሪያ በኢትዮጵያ በኩልም ሆነ በሶማሊያ መንግስት የተሰጠ ማስተባበያ የለም።

 

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events