Dehai News

(ዶይቸ ቬለ) የስህተት ሰለባው ኤርትራዊ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Wednesday, 28 August 2019

ኢትዮጵያ ቀን 28.08.2019

የስህተት ሰለባው ኤርትራዊ

መድሃኔ ተስፋ ማርያም በርሄ በሱዳን ወታደሮች ታስሮ ከሱዳን ለጣልያን ተላልፎ ተሰጠ።በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን በማሻገር ተጠርጥሮ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው «መድሃኔ ይህደጎ መርዕድ» «ጀነራሉ» ተብሎ የሚጠራው ሰው ነው ተብሎ ነበር የተያዘው።መድሃኔ ይህደጎ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውር ሰፊ መረብ ያንቀሳቅሳል የሚል ውንጅላ ይቀርብበታል።


Medhanie Tesfamariam Berhe during his trial in Sicily: now held in a deportation centre. Photograph: Andreas Solaro/AFP
መድሃኔ ተስፋ ማርያም በርሄ 

ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ተጠርጥሮ ታስሮ ነበር። ከሱዳን ለጣልያን ተላልፎ ከተሰጠ ከሦስት ዓመት በኋላ በቅርቡ በነፃ ተለቆ በቅርቡ እዚያው ጣልያን ጥገኝነት አግኝቷል። በስም ስህተት ያላሰበው ችግር ውስጥ የወደቀው ኤርትራዊ ጉዳይ የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ለዝግጅቱ ኂሩት መለሰ።
አውሮፓውያን ሕገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለመከላከል ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይ በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ሕገ ወጥ በሚባሉ መንገዶች አውሮጳ ከገቡ በኋላ፣ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞች እንዳይመጡባቸው የጋራ የመከላከያ መንገዶችን ቀይሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር፣ የስደተኞች መነሻ እና መተላለፊያ ከሆኑ ሃገራት ጋር ስደተኞችን እንዲይዙላቸው ያደረጓቸው ልዩ ልዩ ስምምነቶች እንዲሁም ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን ከያሉበት አድኖ መያዝ ይገኙበታል። 
በአሁኑ ወቅት የህብረቱ ደቡባዊ ድንበር የሆኑት ጣልያን እና ማልታን የመሳሰሉ ሃገራት የባህር ድንበራቸውን ለስደተኞች ዘግተዋል ማለት ይቻላል። የስደተኞች መተላለፊያ የሆነችው ሊቢያም ከጣልያን እና ከአውሮጳ ህብረት በምታገኘው ድጋፍ የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን እየመለሰች ነው። ሌላዋ የስደተኞች መተላለፊያ ሱዳን የፀጥታ ኃይሎቿ በአውሮጳ ሃገራት እገዛ ስደተኞችን መቆጣጠር የሚያስችላቸው ሥልጠና  እየተሰጣቸው ነው። 
የኢትዮጵያዋ ጉረቤት ሱዳን በሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪነት የሚጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፋ ትሰጣለች። ከመካከላቸው አንዱ የዛሬ ሦስት ዓመት በዚሁ ወንጀል ተጠርጥሮ ለጣልያን ተላልፎ የተሰጠው መድሃኔ ተስፋ ማርያም በርሄ ነው። ኤርትራዊው መድሃኔ ለ3 ዓመታት ጣልያን ውስጥ ከታሰረ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ወር በነጻ ተለቋል። መድሃኔ እንዴት እና ለምን ተያዘ? እንዴትስ በነጻ ተለቀቀ? ከአሁን በኋላስ ምን ይጠብቀዋል?

Italien Medhanie Yehdego Mered (Reuters/Italian Police Department)

መድሃኔ እንደማንኛውም ኤርትራዊ ወጣት ዘመዶቹ ወደሚገኙበት ወደ አሜሪካ ይሁን ወደ አውሮፓ ለመሰደድ አስቦ ወደ ሱዳን የሄደው ከ4 ዓመት ተኩል በፊት ነበር። ከትውልድ ሃገሩ ኤርትራ ተነስቶ በአዲስ አባባ አድርጎ ነበር ሱዳን የገባው። ኤርትራን ጥሎ የወጣውም በሳዋው ብሔራዊ ውትድርና ተማሮ መሆኑን ጠበቃ ሚኬኤል ካላንትሮፖ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል። ጠበቃው እንዳሉት ሱዳን በቆየበት ጊዜም ወደ ሌላ ሃገር ለመሻገር የሚያስፈልገውን ገንዘብ እየጠበቀ ነበር። እዚያ ስራ እንዳልነበረው እና የሚኖረውም አሜሪካ እና ኖርዌይ የሚገኙ እህቶቹ እና ወንድሞቹ በሚልኩለት ገንዘብ እንደነበር ገልጸዋል። መድሃኔ ያልታሰበው ዱብ እዳ የገጠመው ሱዳን ውስጥ አንድ ዓመት ካሳለፈ በኋላ ነበር። 
«ከኤርትራ የወጣው በጎርጎሮሳዊው 2014 መጨረሻ ላይ ነበር። ከዚያም ለጥቂት ወራት አዲስ አበባ ነበር። መጋቢት፣ ሚያዚያ ነበር ድንበር አቋርጦ ሱዳን የሄደው። ስለዚህ ሱዳን የቆየው እስከሚታሰር ድረስ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ነው። የታሰረውም ግንቦት 2016 ነው።» 
መድሃኔ ተስፋ ማርያም በርሄ በሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ታስሮ ከሱዳን ለጣልያን ተላልፎ ተሰጠ። በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን በማሻገር ተጠርጥሮ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው «መድሃኔ ይህደጎ መርዕድ» ወይም «ጀነራሉ» ተብሎ የሚጠራው ሰው ነው ተብሎ ነበር የተያዘው። መድሃኔ ይህደጎ ወይም ጀነራሉ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ፣ በሱዳን፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በአውሮፓም ጭምር ቅርንጫፎች ያሉት ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውር ሰፊ መረብ ያንቀሳቅሳል የሚል ውንጅላ ይቀርብበታል።
የመድሃኔ ይህደጎ ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የገባው በተለይም በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 2013 በጣልያን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የሰጠመችውን ጀልባ ጉዞ በማዘጋጀት ከተጠረጠረ በኋላ ነበር። በሜዴትራንያን ባህር ላይ ከደረሱ አደጋዎች፤ «አሰቃቂ» በተባለው በዚህ የጀልባ መስጠም አደጋ ቢያንስ የ360 ስደተኞች ህይወት አልፏል። የዛሬ ሶስት ዓመት ጣልያን፣ ሱዳን እና ብሪታንያ መድሃኔ ሱዳን ውስጥ መያዙን አድንቀው እርምጃውም ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ለማሻገሩ ንግድም «ከባድ ምት ነው» ብለው ነበር። ሆኖም «ተፈላጊ ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪ» የተባለው መድሃኔ ተስፋ ማርያም ሱዳን ውስጥ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ «እኔ የተባለው ሰው አይደለሁም» ቢልም ሰሚ አለማግኘቱም ጠበቃው ሚኬኤሌ ካላንትሮፖ

Europa Migraten Flüchtlinge Eritrea (picture-alliance/dpa/H. W. Bowman)

ተናግረዋል።
«ደንበኛዬ ሱዳን ውስጥ በሃገሩ ፖሊስ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በስህተት መያዙን ይናገር ነበር። በሱዳን ጦር መኮንኖች ምርመራ ሲካሄድበት ስሙ መድሃኔ ተስፋ ማርያም በርሄ እንጂ እነርሱ የሚፈልጉት መድሃኔ ይህደጎ መርዕድ አለመሆኑን ነግሯቸዋል። በፍርዱ ሂደት ፍጻሜ ላይ እንደሰማነው አሳልፎ የሰጠው ሱዳናዊ መኮንን ስማቸው የተለያየ ሆኖ ሳለ ለምን ለጣልያን ባለሥልጣናት እንደሰጠው ሲጠየቅ ሁለቱም መድሃኔ የሚል ተመሳሳይ ስም ስላላቸው ነበር ብሏል። እናም ደንበኛዬ የታሰረው በዚህ ምክንያት ነው። በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን በማሻገር ከሚጠረጠር ሰው ጋር ተመሳሳይ ስም ስላለው ብቻ ነው። ሌላ ምክንያት የለውም።»
ጠበቃ ካላንትሮፖ እንደሚሉት ሌላም የተፈጠረ ስህተት አለ።
«ደንበኛዬ ለህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ሲደውል ስልኩ ተጠልፎ ነበር እና በንግግራቸው መሃል መድሃኔ የሚለውን ስም የብሪታንያ ባለሥልጣናት ስለሰሙ እርሱም በዚህ ወንጀል ተሳታፊ ነው ብለው መጠርጠራቸውም ሌላው ስህተት ነው።»
ምንም እንኳን መድሃኔ ተስፋ ማርያም እና መድሃኔ ይህደጎ በገጽታቸውም ሳይቀር ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፣ የመድሃኔ የDNA ማስረጃም ቢቀርብም፣ ከሳሽ የጣልያን አቃቤያነ ሕግ  መድሃኔ ተስፋ ማርያም የ14 ዓመት እሥራት እንዲፈረድበት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ነበር። ይሁን እና 21 ወራት ከወሰደ የፍርድ ሂደት በኋላ ጉዳዩን ሲያይ የቆየው የፓሌርሞ ፍርድ ቤት «ፖሊስ ይዞ ለፍርድ ያቀረበው የተሳሳተ ሰው ነው» ሲል ብይን አሳልፏል። በስህተት መያዙ የተረጋገጠውን መድሃኔ ተስፋ ማርያምን  በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 4፣2019 በነጻ አሰናብቶታል። ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ «እኔ የሚፈለገው ወንጀለኛ አይደለሁም» ሲል እየተከራከረ ብይኑ ለምን ሦስት ዓመት ሊወስድ እንደቻለ የተጠየቁት የመድሃኔ ጠበቃ ሚኬሌ ካራንትሮፖ ሂደቱ ሊራዘም የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን ተናግረዋል።

Europa Symbolbild Grenzschutzmission Sophia rettet weniger Menschen (picture-alliance/dpa/G. Lami)

«የክሱ ሂደት የተወሳሰበ ነው። ብዙ ጊዜ ወስዷል። DNAን የመሳሰሉ ማስረጃዎች ያስፈልጉ ነበር። የደንበኛዬ እናት DNA መመርመር ነበረበት። ምስክሮችም ስለጉዳዩ ቃላቸውን ለመስጠት ፓሌርሞ ድረስ መምጣት ነበረባቸው። በእነዚህ ምክንያቶች ነው እስከ ጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 4 ድረስ ብይን ሳይሰጥ የቆየው።» 
የፓሌርሞ ፍርድ ቤት መድሃኔን በነጻ ከማሰናበቱ በፊት ካርቱም በነበረበት ጊዜ «የአጎት፣ አክስቱን ልጆች በህገ ወጥ መንገድ አውሮጳ እንዲሻገሩ አድርጓል» በሚል ክስ የ5 ዓመት እሥራት እንደሚጠብቀው አስታውቆ ነበር። ሆኖም ለሦስት ዓመታት በመታሰሩ ፍርዱ እንደተነሳለት በወቅቱ ገልጿል። ታዲያ በስም ስህተት ለሦስት ዓመት ለእስር የተዳረገው መድሃኔ፣  «ካሳ ሊሰጠው አይገባም ወይ?» ተብለው የተጠየቁት ጠበቃው፤
«የለም የለም ምክንያቱም ደንበኛዬ በሌላ ክስ ጥፋተኛ ስለተባለ ካሳ አያገኝም»
 ሲሉ ነበር የመለሱት። በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በነጻ የተለቀቀው መድሃኔ በነሐሴ መጀመሪያ ላይ ጣልያን ተገን ሰጥታዋለች። ጠበቃው እንደተናገሩት የ32 ዓመቱ መድሃኔ «ወደ ሃገሩ ቢመለስ ለተለያዩ ችግሮች ሊዳረግ ይችላል» በሚል ነው የጣልያን መንግሥት የተቀበለው። ላጤው መድሃኔ በአሁኑ ጊዜም ነጻነቱን እያጣጣመ መሆኑንም ጠበቃው ተናግረዋል። አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፉን፣ በተፈጠረው ስህተትም ብዙ መሰቃየቱን ገልጸዋል። መድሃኔን በቀጥታ ለማነጋገር ሞክረን ነበር ሆኖም ልናገኘው አልቻልንም። ጠበቃው እንደነገሩን ዋነኛው ተፈላጊ መድሃኔ ይህደጎ መርዕድ ግን እስካሁን አልተያዘም።

ኂሩት መለሰ

ተስፋለም ወልደየስ




EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events