Date: Thursday, 13 November 2025
ግልጽ ደብዳቤ
ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
የቀይ ባህር ሰው
ዋሽንግተን ዲ ሲ
ጥቅምት 15 2025
ጉዳዩ፡ በኤርትራ ሉዓላዊነት ፥ የግዛት አንድነት እና ህዝቧ ላይ ያነጣጠሩ መልእክቶችህ
በቅድሚይ ኤርትራዊ ባህላችን በሚጠይቀው ጨዋነት የአክብሮይ ሰላምታየን አስቀድማለሁ። ቀጥሎም በኤርትራ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ ያነጣጠሩ መልዕክቶችህ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካካል ጥላቻን የሚያራግቡና ለጦርነት የሚቀሰቅሱ ሃላፊነት የጎደላቸው ናቸው። የዚህ ግልጽ ደብዳቤ አላማ በቂ ማስረጃ በማቅረብ የሃሰት ትርቶችህን ማጋለጥና የኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ ግንዛቤ ላማስጨበጥ ይረዳል በሚል ተስፋ ነው።
1. "የአለም አቀፍ ህግ የኢትዮጵያን
የባህር በር ባለቤነት እውቅና ይሰጣል፡"የባህር ኃይል ያቋቋምነው የባህር በር ባለቤትነት ለመሆን ነው"
የአለም-አቀፍ ህግ ወደብ የሌላቸው አገሮች ወደብ ካላችው አገሮች ጋር በመስማማት በወደብ የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የባህር መውጫ ማግኘት መብት ሲባል ግን በሃይል የመያዝ ወይ በባለቤትነት መያዝ ሳይሆን በወደቦቹ መጠቀም (access to the sea) መብት ብቻ መሆኑን በማያሻማ ቃላት ተደንግጓል። የባህር በር ያላቸው አገራት የባህር በር የሌላቸውን ጎረቤት አግሮችን ማስተናገድና የልማት አጋር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እውቅና ይሰጣል። ይህ የሚፈጸመውም በአለም አቀፍ ህግ፡ ሉአላዊነትን የማክበር መርህ ላይ የተመስረት ሲሆን ብቻ መሆኑን አስምሮበታል።
በአለም ዙርያ 44 አገሮች (700 ሚልዮን የህዝብ ብዛት ያላችው) የባህር በር ባላቤቶች አይደሉም። ከነዚሁም 16ቱ አገሮች (36%) በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያን ሳይጨምር 15ቱ 365 ሚልዮን የህዝብ ብዛት ያላቸው ናቸው። እነዚህ አገሮች ያደረጉት የአለም አቀፍ ህግ በሚፈቅደው መሰረት፥ ከጎረቤት አገሮች ጋር ባደረጉት ስምምነት የባህር በር መውጫና መተላለፍያ መብታቸውን አስከብረው የህዝባቸውን ኑሮ ለማሽሽል በመረባረብ ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ ኢትዮጵያና ኤርትራ በአለም አቀፍ ህጎች መሰረት ሁለቱንም ተጥቃሚ የሚያደርግ የወደብ አጠቃቀም ስምምነት ማድረግ ይችላሉ።
2. "ከተቻለ በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ ግን በጦርነት ኢትዮጵያ የወደብ ባላቤትነትዋን ታረጋግጣለች"፡
"የህዳሴውን ግድብ ጨርሰናል፥ አሁን የቀረው የቀይ ባህር ጉዳይ ነው"
የአለም-አቀፍ ስርዓት የተመሰረተው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር መርህ (Principle of Respect for Sovereignty and Territorial Integrity) ላይ ነው። የአገር ሉዓላዊነት መሰረታዊ መርህ ወደብ ባለቤት አገሮች ብቸኛ እና ፍፁም የሆነ የባለቤትነት መብትን ይሰጣል። በተጨማሪ የተ/መ ቻርተር አንቀጽ 2 (4) በሌላ አገር ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ላይ ሃይል መጠቀም ወይ ማስፈራራት አይፈቅድም።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት እንደማትፈልግ ደጋግማ አስታውቃለች። " በህውሃት ሰራዊት በተወጠርክበት ወቅት - “የኤርትራ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ውላታ ለዘለአለም የማይረሳ ነው" አንዳላልክ፡ አለም አቀፍ ህግን በመጣስ አሰብን ለመያዝ መሞከር ( መያዝ ይችላል ወይ አይችልም የሚለውን ወደ ጎን ትተን) የኤርትራ ሰራዊት (“ይክአሎ” ብሎ የሚታወቀው የቀድሞ ታጋዮች) እና “ዋርሳይ” በሚል የሚጠራው የሳዋ ትውልድ) የአገሪቱን ሉአላዊነት ላለማስደፈር ዝግጁ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። የሰላሙን መንገድ ረግጠህ ጦርነት ከመረጥክ፡ ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ወደ አላስፈላጊና አውዳሚ ጦርነት ከማስገባትና ከፍተኛ የህይወት ዋጋ ከማስከፈል ሌላ ፋይዳ አይኖረውም። ይልቁንስ የአራት ኪሎ ስልጣንህ አደጋ ላይ ስለሚጥል “አሳ ጎጉጓሪ ዘንዶ አወጣ፡ የሰው ፈላጊ የራሱን አጣ" እንዲሉ የጦርነቱን ጎዳና ባትመርጥ ይሻላል።
3. "130 ሚልዮን ህዝብ ያላት ኤትዮጵያ አለ ባህር መኖር አትችልም"
የወደብ ባለቤትነትና አጠቃቀም የአለም አቀፍ ህግ በማያሻማ ቋንቋ የተቀመጠ ነው። የአለም አቀፍ ህግ አንድ አገር ከ100 ሚልዮን በላይ ህዝብ ካላት ወይም ከባህር ዳርቻ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሆነች የባህር በር ባለቤትነት መብት ይገባታል" ብሎ አይደነግግም። የኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር ለመወሰን የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን ጉዳዩን በ2021መመልከቱ ይታወቃል። ሁለቱም አገሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የውጭ አገር ባለሙያዎች ቀጥረው ከአንድ ዓመት በላይ መከራከራቸውን የኮሚሽኑ መዝገቦች ያረጋግጣሉ። የኮሚሽኑ ውሳኔ በ1908 አፄ ሚኒሊክና የጣልያን መንግስት ስምምነት፡ "ከባህር ዳር ወደ መሬት 60 ኪሎ ሚትር ረቀት በመሄድ አሰብ የኤርትራ መሆኑን" በድጋሚ አረጋግጧል።
“ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን የሚስያችላት የአለም አቀፍ ህግ አለ”፡ “ራስ አሉላ የኢትዮያ ታርካዊ ድንበር ቀይ ባህር ነው” ብለው ነበር፡ “ኢሃደግ አሰብ የራስ ገዝ ስለነበረ ተከራክሮ ለኢትዮጵይ ማስቀረት ይቻል ነበር” ከተባለ ኢትዮጵያ አለም ፍርድ ቤት ጉዳይን አቅረባ መከራከር ትችላለች። የማይቻለው በጉልበት መንጠቅ ሲሆን ነው !!
4. “የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ረፈረንደም በታዛቢነት የተሳተፍው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት በጎ ፍቃድ ወይ ተባባሪነት ነው”
ይህ ፍጽም የሃሰት ትርክት ነው። ስለዚሁ ጉዳይ አስመልክቶ ፕረዚደንት ኢሰያስ ኣፍወርቂ በወቅቱ የተባብሩት መንግስታት (ተ/መ) ዋና ጸሃፊ ለነበሩት ለሚስተር ቡቶሮስ ጋሊ ከላከው ደብዳቤ በመቀንጨብ፥ " የኤርትራ ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ማረጋገጥ የህዝቡ ብቸኛ መብት እንጂ በኢትዮጵያ በተቁቋመው የሽግግር መንግስት በጎ ፍቃድ ወይም በማንኛውም የሌላ ወገን ፍቃድ ላይ የተመረኮሰ አይደለም"፥ አንዳንድ ወገኖች የተ/መ በረፈረንደሙ በታዛቢነት መሳተፉ በኢትዮጵያ ባለው የሽግግር መንግስት በጎ ፍቃድ ወይ ተባባሪነት ነው የሚሉ አሉ። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ታሪካዊ ስህተትም ይሆናል። ረጅም ጊዜ ለፈጀው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ከማስገኘት ይልቅ ለወደፊት ውጥረት አለመረጋጋት እና ጦርነት ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል"። ሲያጠቃልል " ሁኔታው በአግባቡ ካልተያዘ ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን። ሊከሰት ለሚችለው አላስፈላጊ ጦርነት ሃላፊነትን የሚወስደው አና ታሪካዊ ተጠያቂነቱን የምንሸከመው እኛ ሳንሆን ድርጅቱ መሆኑን በትህትና ማስታወቅ እወዳላሁ" የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ምልእክቱን ማስተላለፉ በግልጽ ተዘግቧል።(የተጠቀሰው ዳብዳቤ በተ/መ አርካይብ ይገኛል)።
ዋና ጽሃፊው በላከው የጽሁፍ መልስ ፡ " የተ/መ ጠቅላላ ጉባኤ በአንቀጽ 47/114 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፡ የኤርትራ ህዝበ-ውሳኔን ለማራጋገጥ በሚካሄደው ሪፈረንደም የታዛቢ ቡድን እንደሚላክ በይፋ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡ ሪፈረንደሙ ሰላማዊ ነፃ እና ፍትሃዊ እንደሚሆን ያለኝን ምኞትና ከፍተኛ ተስፋ እገልጻለሁ" የሚል ነበር። ይህን ተከትሎ የተ/መ ታዛቢዎች በተገኙበት ህዝበ-ውሳኔው (referendum) ሚያዝይ 1993 ተካሂዶ፡ ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ እንደነበረ፡ ውጤቱም 99.8% በሆነ ከፍተኛ ድምጽ ነጻነት መሆኑን ማረጋገጡን የዋና ፀሃፊ ልዩ መልዕክተኛ በይፋ አስተወቀ። ይህን ተከትሎ ኤርትራ ሚያዝያ 27 ቀን 1993 ነጻነቷን በይፋ አስታውቀች፡፡ የተ/መ ጠቅላላ ጉባኤ ኤርትራ ሉዓላዊ 182ኛ አባል ሀገር መሆኗን በይፋ አረጋገጠ። የኤርትራ ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት መቋጫ የተደርገበት፡ ማንም ይሁን ፍፁም ሊቀለብሰው የማይቻል መሆኑን መቀበል ግድ ይላል።
5. "ኤርትራ ወደቦቿን ኢትዮጵያ እንዳትጠቀምባቸው ከልክላለች"
ነጻነቷን ከተጎናጸፈችበት 1991 ማግስት ጀምሮ እስከ አሁን ኤርትራ ወደቦቿን ኢትዮጵያ እንዳትጠቀምባቸው ማንም ጊዜ ከልክላ አታውቅም፡፡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የ1991 የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤ አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ ባደረገው ንግግር "የሁለቱን አገሮች የጋራ ጥቅም ለመጠበቅ እንዲረዳ በማሰብ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ ነጻ ሆኖ እንዲያገለግል የኤርትራ የሽግገር መንግስት ወስኗል”ብሎ ማስታወቁ ይታወቃል። (ንግግሩ በቪድዮ ስለተቀረጸ መመልከት ይቻላል)። የወደብ ስምምነቱ ሁለቱንም አግሮች ከ1991-1998 ተጠቃሚ አድርጓል። ኢትዮጵያ ነጻ የወደብ ተጠቃሚ ያስደረገ፡ ለወደብ አገልግሎት የምትከፍለውም በዶላር ሳይሆን በብር እንዲሆን ያስቻለ እና ከውጭ አገሮች ልምታገኘው ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ ከክፍያ ንፃ የወደብ አግልግሎት ያስጠ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ክፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቷል።ለኤርትራም በተመሳሳይ ከወድብ ክፍያ ከፍተኛ ገቢ አስገኝሏታል።
ከ1998-2000 በነበረው የሁለቱ አገሮች ጦርነት ምክንያት በወደቡ መጠቀም አልተቻለም። ሆኖም በአልጀርስ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ መቋጭ ካገኘ በኋላ ወደቦች ለኢትዮጵያ የሚረባ ጠቀሜታ እንደሌላቸው ለማጥላላት አቶ መለስ ዜናዊ "ግመሎቻችውን ያጠጡበት" ያለው የቅርብ ትዝታ ነው። ዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ስብሰባ ስለወደብ ለቀረበለት የስጠው መልስ፡ "አርግጥ ነው ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች በመጠቀም ብዙ ጥቅም ተገኛለች፡ በተመሳሳይ ኤርትራም ብዙ ትጠቀማለች። በጂቡቲ ወደብ መጠቀማችን ከፍ ያለ ወጪ እንደሚያስከፍለንና እንደሚጎዳን እናውቃለን። በአሰብ መጠቀም እኛን (ምናልባትም የኤርትራን ያህል) የሚጠቅመን ቢሆንም አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በአሰብ ወደብ መጠቀም ከኛ ይበልጥ የኤርትራን መንግስት ይጠቅማል የሚል ድምዳሜ ላይ ነው የደረስነው። ከፍተኛ የፖሊቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ተጽእኖ በስራዓቱ ላይ ባደረሰበት ሁኔታ ለመተንፈስ የሚረዳው ብር በአሰብ በኩል መላክ አይጠቅምንም የሚል አቋም ነው የያዝነው። እኛ ብራችንን ተጠቅመን በጅቡቲ ወደብ በመጠቀም የምንፈልገውን አገልግሎት ማግኘት እንችላለን" በማለት ሃቁን አስተውቋል።
በ2018 በአስመራ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተከትሎ ስለወደብ አጠቃቀም በተደረሰው መግባባት ፥ ኤርትራ ወደቦቿን ለኢትዮጵያ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነበረች። ሆኖም ከ2018-20 በህውሃት የድንበር መዝጋት እንቢተኝነት፡ ከ2020-2022 ከህውሃት ጋር በነበረው ጦርነት፡ቀጥሎም ከ2022-25 ኤርትራን በጠላትነት በመፈረጅህ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦቹን መጠቀም አልቻለችም። በ2018 በአስመራ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተከትሎ ስለወደብ አጠቃቀም በተደረሰው መግባባ: ኤርትራ ወደቦቿን ለኢትዮጵያ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነበረች። ሆኖም ከ2018-20 በህውሃት የድንበር መዝጋት እንቢተኝነት፡ ከ2020-2022 ከህውሃት ጋር በነበረው ጦርነት፡ቀጥሎም ከ2022-25 ኤርትራን በጠላትነት በመፈረጅህ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች መጠቀም አልቻለችም።
6. "ችግሩ ኤርትራውያን ድህነታቸውን enjoy ያደርጋሉ ፡ ድህነት መሆኑ አይገባቸውም፡ ከፍተኛና በሚያሳዘን ጉስቁልና ውስጥ ያሉ ህዝብ ናቸው"
ከጥቂት ወራት በፊት ስለ ኤርትራ ህዝብ የተናገረክውን ንግግር ያዳመጡ ኤርትራውያን በፍጹም ማመን አስቸግሯቸዋል። የኤርትራ ህዝብ ላይ ያነጣጠር የዘላፋ ናዳ በሚድያ በማስተላለግ በሁሉት ህዝቦች መካካል ጥላቻን ለመፍጠር ለምን ፈለግክ ? እንደ አንድ አገር መሪ ያውም “የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ” የጎረቤት አገር የሆነውን የኤርትራ ወንድም ህዝብ እንደዚህ ባለ አስፀያፍና አስነዋሪ ቃላቶች መግለጽህ አላፊነት የጎደለው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። ለነገሩ ጊዜና ቦታ ሳትለይ የኢትዮጵያን ህዝብ በጅምላ መዝለፍ የተለመደ ድርጊትህ መሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ነው።
ስለኤርትራውያን ድህነት በተመለከተ፡ በኤርትራ ምድር ርሃብ የለም። ማንም ኤርትራዊ ዜጋ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም የዕርዳታ ስንዴ አይጠበቅም። በአንጻሩ በከፍተኛ የተፈጥሮ ፀጋ የታደለችው ኢትዮጵያ (የ2024 UNDP report እንደሚያመለክተው) እድሜ ላነተ ብቃት-የለሽ አመራር፡ 80 ሚልዮን ህዝብ በድህነት ይጠቃል፡ 40 ሚልዮን በጉስቁልና ይሰቃያል፡ 20 ሚልዮን ከአለም ምግብ ፕርግርም በሚሰጠው ስንዴ ይኖራል። በቅድምያ የኢትዮጵያን ህዝብ ከከፋ ድህነት ለማላቀቅ መፋለም ሲገባህ ክቡርነትህ የመረጥከው በቢልዮን ዶላሮች ወጪ ፋይዳ የሌላቸው በጣም ትልቅ ቤተ መንግስት፡ ብልጭልጭ የኮሪደር ልማት (ከዱባይ የተኮረጀ) እና መናፈሻ ፓርኮች መገንባት ላይ ነው።
6. የኖቤል የሰላም ሽልማት ላንተ መሰጠቱ ተገቢ አይመስልኝም !
የኖርወይ የኖቤል ኮሚቲ “የሰላም ሽልማት” የሚሰጠው ለሰላም ክፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ነው። ዋናው መስፈርቱም ሰብአዊ መብቶችን፡ ዴሞክራሲና በአገሮች መካከል ግጭቶችን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የሚሰጥ እውቅና ነው።
ሆኖም ሽልማቱን የሰጡት ግለሰብ የድርጅቱ መርሆችን በከፍተኛ መልኩ የሚጻረር- በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የንጹሃን ዜጎች ህይወት ያፈሰስ ግለ ሰብ መሆኑን ሲይውቁ ከፍተኛ ፀፀት እንደሚሰማቸው አያጠራጥርም። የኖቤል ህጎች ሽልማቱ አንዴ ከተሰጠ በኋላ ለመሻር የሚያስችል ደንቦች ስለሌለው ነው እንጂ፡ የተሰጠህን ሽልማት በአስቸኳይ እንድትመልስ ማድረግ እንደሚመርጡ ምንም አያጠያይቅም።
7. ለኢትዮጵያና ኤርትራ የሚበጀው ጦርነት ሳይሆን ለዘላቂ ሰላምና ለጋራ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት መተባበር ብቻ ነው።
በሕዳሴ ግድብ አጠቃቀም ዙርያ ከግብፅ ጋር ያለው ፍጥጫ፡ በሱዳን ሶማሊያና ኤርትራ (ጎረቤት አገሮች)የምታራምደው የጦርኝነት ፖሊሲ የዩናይት አረብ ኤሚሬትስ የቀይ ባህር ቀጠና የውክልና ጦርነት
(proxy-war) አራማጅ በመሆን በቀጥናው ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሯል። ጦርነት ብትጭር አለም አቀፍ ህግን የሚጥስ፡ የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልና በቀይ ባህር ቀጠና ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር ስለሆነ፡ ኢትዮጵያ (1) በአለም ህብረተ ሰብ መወገዝ፡ (2) የኤኮኖሚ እገዳ (economic sanction) እና (3) ዲፕሎማሲያዊ መገለል (diplomatic isolation) ያስክትልባታል። ከሶማሊላንድ ጋር ባደረግክው አለም አቀፍ ህግ የጣሰ ሰምምነት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሽንፈት ተሸክመህ፥ ከሶማሊያ ሉዓልዊ መንግስት ጋር ህጋዊ የሆነ ስምምነት ለመፈረም መገደድህን ማስታወስ ጠቃሚ ነው።
በአገር ውስጥ የገጠመህን የፀጥታና የኤኮኖሚ ውጥረት መቋቋም አቅቶህ፡ የህዝቡን ስሜት ለማነሳሳት የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ማንሳት ህዝብ በሚገባ ተገንዝቦታል። የፋኖና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መቋቋም ባልቻለክበት፡ የኤርትራን ሰራዊት አሸንፈህ፡ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ማድረግ በፍፁም እንደማትችል ጠንቅቀህ ታውቃልህ። የባህር በር ጉዳይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል የግጭት ምክንያት ሊሆን አይገባም። የሚሻለው መንገድ የጦርነት ከበሮ መደለቁን አቁመህ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ለዘላቂ ሰላምና ለጋራ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ነው።
ለኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላምና ብልጽግና እመኛለሁ!!