World News

Goolgule.com: የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመሬት ነጠቃና ስደት (ክፍል ሁለት)

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Monday, 29 May 2017

የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመሬት ነጠቃና ስደት (ክፍል ሁለት)

 

የዛሬ 26 ዓመት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ብሎ የሰየመ የወንበዴዎችና የሽፍታዎች ስብስብ በምዕራባውያን አንጋሾቹ ታግዞ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቃላት እንደ እሣት እየተፉ ታሪክ ፈጽሞ ሊረሳው የማይችለውን ንግግር ያደረጉት ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ – ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!! ስለ ኤርትራ መገንጠል እና ስለ ህወሃት የአስፈጻሚነት ተግባር የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው ይህንን ነበር የተናገሩት

“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡

በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በአስተዳደሩ ተመስግኖ በክብር የተሸኘ ገዥ ስለመኖሩ የሚያወሳ ታሪከ-ድርሳን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስልም። ሁሉም አገዛዞች የተወገዱት በአመፅ አልያም በተፈጥሮ ሞት ነው። ልክ የዛሬ 26 ዓመት 1983 ዓ.ም. ወርሃ ግንቦት በምዕራቡ አለም ረዳትነት በጠመንጃ ወደ ሥልጣን የመጣው አፓርታይዳዊው የህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በቀደሙት ገዥዎች የብረት ጫማ ውስጥ ተከልሎ አፈናና ግድያውን “ግፋ በለው!” ማለቱን አላቆመም። በዚህ መንግሥታዊ ፍጅቱ ከትውልዱ ጋር ክፉኛ ተላትሟል። አሁን በተጨባጭ እየታየ ካለው ህዝባዊ ብሶት አኳያ የአገዛዙ ግብአተ መሬት ሩቅ አይመስልም።

በቀደመው ዕትማችን የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች በሚል ስለከሸፈው የፌዴራል ሥርዓት እና የትምህርት ፖሊሲው ክስረት ማስነበባችን ይታወሳል። እነሆ በክፍል ሁለት ዕትማችን የአፓርታይዳዊ አገዛዝ አራማጁ ህወሓት ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የዘራቸውን በርካታ መርዛማ ፍሬዎች መካከል ሁለቱን ብቻ ከማሳያዎች ጋር ማስነበባችን እንቀጥላለን።

መርዛማ ፍሬ 3. የመሬት ነጠቃ

የኢትዮጵያ የቀደሙ ነገሥታት መደባዊ ይዘት ባለው መልኩ ከሚነሳባቸው የህዝብ አስተዳደር በደል ውጪ የግዛት ማስፋፋት እና አንድነት ጥበቃ ረገድ እጅጉን አኩሪ ታሪክ አላቸው። ከመሬት ጋር የተያያዘው ግዛት የማስፋት ሁነት ጋር በተያያዘ እትዮጵያዊ ሁሉ ሞቱን ሲያስብ “የአገሬ አፈር ይብላኝ” በማለት ለመሬቱ ያለውን ፍቅር ይገልፃል። እትብቱንም ከመሬት ጋር በማስተሳሰር “እትብቴ የተቀበረበት” ሲል ፍቅሩን ይገልፃል። ይህ የተለየ ተዛምዶ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረ ቢሆነም ዛሬ ላይ  በተቃራኒው የእፍረት ምንጭ እየሆነ ነው። ህወሓት መሀሉን አገር ዳር እያደረገው ህዝቡ ችግር ላይ ወድቋል። በየቀየው የህዝቡን መሬት የሚቀራመቱ ባዕዳን በገዥው ኃይል አመቻማችነት ይጠራሉ። ገዥዎቻችንም በዘር ማንዝራቸዉ ሥም መሬትን ባሻቸው መጠን መቀራመታቸውንም ተያይዘውታል።

ስለመሬት ጉዳይ ስናነሳ ቀዳሚው ጥያቄያችን የየዋህ ዜጋ ጥያቄ መሆን አለበት፣ “እኔ አገሬ የምላት ኢትዮጵያ፣ ጎኔን የማሳርፍበት የቤት መስሪያ ቦታ በሊዝ ግዛ የምትለኝን ነው?!” “ያ – አድማስ ይታያችኋል? … እስከዚያ ድረስ የሰፈሩትን አባወራዎች አንሷቸውና መሬቱን አልሙበት” በሚል ለባዕዳን ቀያችን የሚሸጥ ሰው በላ አገዛዝ በምን አግባብ “መንግሥት” ብለን ልንጠራው እንችላለን? እዚህ ላይ በተለይ በውጪ የሚገኙ የሚዲያ ውጤቶች ይህንን አፋኝ ቡድን “የህወሓት መንግሥት” እያሉ ሲጠሩ ስንሰማ እርስበርሱ የሚጋጭ ነገር እየተናገሩ መሆናቸውን አለማስተዋላቸው ብዙዎች የታዘቡት ነው። “አገዛዝ” መባልም ሲበዛበት ነው።

ዜግነት፣ የመሬት ባለቤትነት መገለጫ ነው። ዜግነት በዚህ መሬት ላይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የባለመብት ድርሻን ህጋዊ አድርጎ የሚደለድል የፍትህ ምርኩዝ ነው። በኢትዮጵያ መሬት ላይ መኖር፣ መክበርና መከበር፤ ለመሬቱ ከመሞት ጋር የተያያዘ መብትና ግዴታ ነው። መብቱ ከሌለ ግዴታው የለም፤ ግዴታ ከሌለ መብትም የለም።

ለህወሓት/ኢህአዴግ የመሬት ጉዳይ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ የደም ስሩ ነው። “መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በሚል “የገጠሩም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው” በሚል ያወዛግባል። “ህዝብ” ማነው? “ብሔሮች” እነማን ናቸው? “ብሔረሰቦች” የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? …  26ዓመታት አልፈዋል መልስ ግን የለም!!!

በ“ህዝብ፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች” ብያኔ ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወተው ህወሓት “መሬት አይሸጥም አይለወጥም” ባለበት አንደበቱ የ“ሊዝ ህግ” በማውጣት የመሬት ሽያጭ ንግዱን አጧጡፎታል። በከተሞችም ሆነ በገጠር የሚታየው የመሬት ነጠቃ የዜግነት መብትን የጨፈለቀ “በላኤሰባዊ” አካሄድ ነው። በከተሞች ያለው የመሬት ቅርምት ህወሓት ከሚከተለው “ዘውጋዊ ኢኮኖሚ” ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። በተለይም የሊዝ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምር መዋቅራዊ ድጋፍ ያላቸው የትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃን እና የገዥው ኃይል ተለጣፊ ባለሃብቶች በዋናነት አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ያሻቸውን ያህል የቦታ ስፋት ነባር ነዋሪውን በማፈናቀል ቅርምቱን አጠናክረው ቀጥለዋል፡ የሊዝ ክፍያው የሚፈፀመው በረዥም ጊዜ ሂደት መሆኑና ከባንክ ብድር መመቻቸቱ  ደግሞ ባለሃብቶቹ ሰብዓዊነት በጎደለው አልቦ ርህራሄ ያሻቸውን ድሆዎች አፈናቅለው የህንፃ ባለቤት ይሆናሉ። አልያም መሬቱን ያለከልካይ አጥረው ይይዛሉ። ድሆቹን ዘወር ብሎ የሚያያቸው አንድም አካል የለም። “የልማት ተነሽ” ከሚለው መጠሪያ ስማቸው በስተቀር የሚተርፋቸው አንድም ጥሪት  የለም። በዚህ መሰል የሚገፉ ዜጎች መውደቂያቸው እንደ “ቆሼ” ባሉ ቦታዎች ይሆናል።

ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያዊያንን የመሬት ባለቤትነት መብት በመካድ ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪነትንና ፖለቲካዊ ታማኝነትን መለኪያ ባደረገ መልኩ ለመሬት ቅርምቱ አገዛዙ ይሁንታ ሲሰጥ እየታየ ነው። በ“ልማት” ሥም ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ በገዛ መሬታቸው ላይ ጥበቃና የቤት ሰራተኛ ሆነው ሲቀጠሩ እየታየ ነው። እንዲህ ላለው በደል አዲስ አበባ ከበቂ በላይ ማሳያ ነች። በጆሞ፣ ሲ.ኤም.ሲ.፣ ገላን፣ የካ አባዶ፣ መሪ፣ ለገጣፎ፣ … ወዘተ ባሉ ኮንዶሚኒየምና ሪል ስቴት መንደሮች የጥበቃ፣ የልብስ አጣቢነት፣ የአትክልት ሰራተኝነት፣ … መሰል ስራዎችን ከሚሰሩት ሰራተኞች ውስጥ ከዓመታት በፊት የመሬቱ ባለቤት የነበሩትን ዜጎች ፈልጎ ማግኘት የሚከብድ  አይደለም። “መንግስተ ሰማያት የእግዚአብሔር፣ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የገብረ እግዚአብሄር ነው” የሚለውን የአዲስ አበቤዎች መራር ቀልድ በመስመር መሃል ማስታወሱ የመሬት ተቀራማቹን ማንነት ይበልጥ የሚያሳብቅ ይመስላል።

በክልል ከተሞች እና በገጠር አካባቢዎች የ“ኢንቨስትመንት” አማራጭ በሚል የዜጎች ከመሬት መፈናቀል፣ ከግጦሽ መሬት መባረርና በግዴታ የሚፈፀም የመንደር ምስረታ በተጨማሪም የደን መጨፍጨፍና የብርቅዬ የዱር እንሰሳት መሰደድ ከመሬት ቅርምቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተጨባጭ ጉዳቶች ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል እና አፋር ክልል ወደር የለሽ የመሬት ቅርምት ሰለባዎች ናቸው።

ርካሽ መሬት፣ በአነስተኛ ወጪ የሚገኝ የሰው ኃይል፣ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ታክስ ተኮር የሆነ መንግስታዊ ድጋፎችን የሚያገኙት፣ የቻይና፣ የህንድ፣ የሳውዲ አረቢያ፣ የቱርክ፣ … ባለሃብቶች መሬትን በተመለከተ ከህወሓት ጋር በአፍላ ፍቅር ወድቀዋል። የሰፋፊ መሬት ስጦታው በቅርምት የሚተረጎም ቢሆንም ህወሓትና ኩባንያዎቹ (የውጪ ባለሃብቶች የሚመሯቸው) በተድበሰበሰ እና እጅግ ምስጢራዊ በሆነ የንግድ ስምምነት መሬቱን እየተቀባበሉት ይገኛል። በተለይም በጋምቤላና በምስራቅ ኦሮሚያ በብሔራዊ ፓርክነት ተወስነው የተከለሉት ድንበሮች ሳይቀር ተጥሰው ለህንዱ ካሩቱሪ ሳዑዲ ስታር ባለሃብቶች መሬቱ ተቸብችቧል። የመሬት ቅርምቱ አስከፊነት ደግሞ እነዚህ ሰፋፊ መሬቶች ለኢንቨስተሮቹ ሲተላለፉ በስምምነቱ ቀዳሚ ተጠቂ የሚሆኑትን የአርብቶ አደሮችን እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ፍፁም የዘነጋ መሆኑ ነው።

ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር፣ ከግብርና ጋር በተያያዘ ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ሴክተሮች መሻገር እንዲሁም ያልታረሱ መሬቶችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚሉት አማራጮች የኢትዮጵያ ገበሬዎች የዕድገት አማራጮች ቢሆኑም መሬትን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚያየው ህወሓት በአማራጭ ኢንቪስትመንት ሥም ለውጭ ባለሃብቶች፣ ለትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃን እና ለተለጣፊ (ሎሌዎች) የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ለም መሬት ማደሉን ተያይዞታል። በዚህም ባሉበት ከመርገጥ ወርደው የበይ ተመልካችነት እና ምፅዋት ጠባቂነት ደረጃ ላይ የደረሱት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በአስር ሚሊዮን ይቆጠራሉ። 26ኛውየ“ግንቦት 20 በዓል” እየተከበረ ባለበት በዚህ ዓመት እንኳ አገዛዙ በይፋ ባመነው አህዛዊ  መረጃ መሰረት 7.8 ሚሊዮን ህዝብ (በአብዛኛው ገጠር)  የዕለት ምግብ ደራሽ ተረጂ ነው። ህወሓት ከቁጥር ጋር ያለበትን ችግር ስናስተውል የረሃብ አደጋ ያንዣበበባቸው የዕለት ምግብ ተረጅ ዜጎች ከተጠቀሰው ቁጥር በእጥፍ እንደሚልቅ መረዳት ይቻላል።

ህወሓት/ኢህአዴግ በኢንቨስትመንት ሥም ለመሬት ነጠቃው ይሁንታ ሲሰጥ፤ መሬቱን ነዋሪዎችን ከቀያቸው በማፈናቀል ከማቅረብ በተጨማሪ ከቀያቸዉ በመፈናቀላቸዉ የተቆጡ ዜጎች አንዳችም ጥቃት እንዳያደርሱ መከላከልና የአፈና እርምጃ ለመውሰድ ለባለሃብቶች የገባው ግዴታ አለ። በዚህ ረገድ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልል የታየው ተከታታይ አፈና እና ግድያ ህወሓት ለባለሃብቶቹ ለገባው ግዴታ መገለጫ ይሆናል።

         በውጪ ካምፓኒዎች ስር ያለ የመሬት መጠን (በጋምቤላ ብቻ)

ተ.ቁ የድርጅቱ ስም አገር የተረከበው የመሬት መጠን ምርመራ
1 ካራቱሪ ህንድ 100,000 ሊዝ
2 ቢ ኤች ኦ ህንድ 27,000
3 ቨርደንታ ሀርቨት ህንድ 3,012
4 ሀናን አግሪ ካልቸር ህንድ 25,000
5 ካበር ፋርምስ ህንድ 25,000
6 ግሪን ቫሊ ህንድ 5,000
7 ቶሪን አግሮ ህንድ 6,000
8 ሳኡዲ ስታር ሳኡዲ አረቢያ 10,000
9 ሳናቲ አግሮ ህንድ 10,000
10 ሩቼ አግሪ ህንድ 25000
11 ላኪ ኤክስፖርት ህንድ 5000

የመረጃ ምንጭ “Land to investors”

ከዚህ በላይ የተመለከተው ሰንጠረዥ በኢንቨስትመንት ሥም በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለውን የመሬት ቅርምት ይበልጥ የሚያሳይ  መረጃ ነው። እነዚህ የውጭ ድርጅቶች ታክስ ነክ መንግስታዊ ድጋፍና የባንክ ብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸው በርካሽ የሰው ኃይል እና በተስማሚ አየር ንብረት በመታገዝ፤ በለም መሬታችን ላይ እንዳሻቸው ሲያዙ የነበሩ/የሚያዙ መሆናቸውን እያስመርንበት ከዚህ ከልካይ አልባ ፍቃድ ጀርባ የህወሓት ባለሥልጣናት የያዙትን ዘረፋ መረዳት አይከብድም። የጋምቤላ መሬት ቅርምት ጉዳይ በዚህ የሚያልቅ ሳይሆን ከውጪ ባለሃብቶች በላይ የትግራይ ተወላጆችን ገደብ የለሽ የንዋይ ፍቅርን በሚያንፀባርቅ መልኩ መሬቱን ወርረው የያዙበትን ሁኔታ አያይዘን ማስታወስ እንወዳለን። የጋምቤላ አርብቶ አደሮችንና አርሶ አደሮችን ዜግነታዊ መብት በሚጨፈልቅ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ነጠቃ የአፓርታይዱን አገዛዝ የሚያስታውስ ነው።

ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ለጅቡቲ መንግስት 3 ሺህ ሄክታር ለጥራጥሬ ምርት፣ የህንድ ኩባንያዎች ለሆኑት ለኢማሚ ባዮቴክ 100 ሺህ ሄክታር ለጃትሮፋና ለምግብ ዘይት ዘር፣ ለአልሚደሃ ኩባንያ 28 ሺህ ሄክታር ለሸንኮራ አገዳ፣ ለሮምቶን አግሪ ኩባንያ 10 ሺህ ሄክታር ለቲማቲም ምርት በሚል መሬቱ በሊዝ ተቸብችቧል። በደቡብ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምር 200ሺህ ሄክታር የሚያካልል 16 የኢንቨስትመንት ስምምነት ተደርጓል። እያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ ሲሆን ሁሉም የተሰጠው ለውጭ ባለሃብቶች ነው። በአፋር ክልል 409,678 ሄክታር መሬት በማዕከላዊ መንግስቱ መሬት ባንክ አማካኝነት ለባለሃብቶች ተመድቧል። በአማራ ክልል በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደተዘገበው ከ175 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለውጪ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ተመድቧል (በአጠቃላይ የመረጃ ምንጭ፡ the Oakland Institute’’)

ከዚህ በላይ የተመለከቱ መረጃዎች በኢትዮጵያ ያለውን የመሬት ነጠቃ ከብዙ እጅግ በጥቂቱ አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ። የመሬት ቅርምቱ በለስ የቀናቸው የውጪ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንታቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማስረፃቸው ቀርቶ በጉልበትና በአነስተኛ የሙያ ተግባራት ለሚቀጥሯቸው ኢትዮጵያዊያን ክብር ሲሰጡ አይታይም። ዝቅተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ከመክፈል ጀምሮ የጤና ኢንሹራንስ በመንፈግ፣ በቂ የመኖሪያ አካባቢ እና ደህንነት መጠበቂያ መንገዶችን ባለመፍጠር፣ የሰራተኞችን የጡረታ ሽፋን አለመክፈል፣… የመሳሰሉ ችግሮች ኩባንያዎቹ ዘወትር የሚወቅሱባቸው በጎ ያልሆኑ ተግባሮቻቸው ናቸው።

ገጠር ከተማ ድረስ ባደረሰው የመሬት ነጠቃ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በዋናነት ትግሬዎች መሆናቸውን ስናስብ ከመጋረጃው ጀርባ በአገር ላይ ተይዞ ያለውን ህወሓታዊ ቁማር አብዝተን እንድንኮንነው እንገደዳለን። “ግንቦት 20” ካበቀለብን መርዛማ ፍሬዎች አንዱ የመሬት ነጠቃ ነው። አገዛዙ መሬትን በተመለከተ በያዘው ቀኖናዊ ምልከታው ላይ የሽፍታ ባህሪው ታክሎበት የዘረፋ ምንጩ አድርጎታል።  ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ የህዝብ ብሶት ጫፍ እየረገጠ በመምጣቱ ህወሓት/ኢህአዴግ ከፈኑን በሚሰፋ፣ መቀበሪያውን እየቆፈረ ባለ ቅርብ ወራጅ (ሟች) ይመስላል።

መርዛማ ፍሬ 4፡ ስደት

የኢትዮጵያዊያን የስደት ታሪክ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረ፣ እንደየጊዜ ማዕቀፉ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነሻ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም ካለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ ያለው የስደት ታሪካችን በአመዛኙ ከፖለቲካ ነፃነት እጦቱ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለው የስደት ጭብጥ መነሻው ዘረኝነት ባጠላበት አፓርታይዳዊ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የተፈጠሩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለስደቱ አባባሽ ምክንያት ሁነዋል።

ምሁር ጠል በሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ሸፍጥ የተነሳ አገር ጥለው በተሰደዱ ምሁራን ቁጥር ኢትዮጵያን ከዓለም አገራት ቀዳሚ ተጠቂ ከሆኑት ውስጥ የሚያሰልፋት የOnlineuniversities.com ዘገባ፤ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያብራራል። እንደ ሪፖርቱ መደምደሚያ ባለፉት አስር አመታት ብቻ ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆኑትን የላቁ ምሁራን በስደት ምክንያት አጥታለች። የህክምና ባለሙያዎች የሚበዙበት ይኽው ስደት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝቡ ጤና መጓደል ላይ ጭምር ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።

በቦሌ በኩል ያለው አስፈሪ የስደት መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ በሞት ሸለቆ ውስጥ የመጓዝ ያህል በሚከብደው የሰሃራ በረሃ የስደት ጉዞ ውስጥ በአሸዋው ተውጠው ፣ በቀይ ባህር ሰጥመው ፣ በአክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ታፍነውና ታርደው፣ … የቀሩት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከግምት በላይ ነው። ብዙ ህልም ይዘው ቢወጡም ገንዘባቸው ባክኖ ህልማቸው ከመብነኑ ባሻገር ህይወታቸውን ያጡት፣ የመንፈስ ስብራት የደረሰባቸው ዜጎች የ“ግንቦት ሃያ” መርዛማ ፍሬ ሰለባ ናቸው።

በህገ-ወጥ መንገድ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 60% የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ UNHCR (2013፣ 2014፣ 2015፣ 2016) ሪፖርት የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ሄዷል። ስደተኞቹ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የዘለቀ የትምህርት ደረጃ ያላቸው፣ አነስኛ የሙያ ክሂል ባለቤት የሆኑ፣ የሚሰደዱበትን አገር መዳረሻ በቅጡ ያልለዩ፣ ከውጪ አገር ዜጎች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር ያለባቸው መሆኑ የስደተኞቹን መከራ አብዝቶታል።

በሲጋራ ፍም ሰውነታቸው የተለበለበ፣ አሲድ ሰውነታቸው ላይ የተደፋባቸው ፣ ለወራት ተገደው የሚደፈሩ፣ የሰውነት አካላቸውን (ኩላሊት) የተቀሙ (Organ Traffic) ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ታሪክ መስማት የተለመደ ሆኗል። እንደ የመንና ሊቢያ ባሉ መንግስት አልባ አገራት በኩል የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን በሽብርተኛ ቡድኖች በመታገት አስከፊ እንግልት፣ ስቅየትና ግድያ ይደርስባቸዋል። በእገታ የሚያዙ ስደተኞች በአሸባሪ ቡድኖች አስገዳጅነት አገር ቤት ያሉ የቤተሰብ አባላት ገንዘብ እንዲልኩ እንደሚገደዱም በየጊዜው የምንሰማው የመከራ ዜና ነው።

በደቡብ አፍሪካ፣ በሊባኖስ፣ በኩዌት፣ በቤሩት፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ … ወዘተ በመሳሰሉ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በግፍ ተገድለው በአደባባይ መጣላቸውን፣ በመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን፣ ከፎቅ ላይ ራሳቸውን በመፈጥፈጥ ህይወትቸውን ማጥፋታቸውን … መሰል አሰቃቂ የዜና ዘገባዎች እንደ ሜትሮሎጂ ዘገባ በየዕለቱ መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። የዜጎቹ የመከራ ዜና ግድ የማይሰጠው ህወሓት/ኢህአዴግ በብዙ ጭንቀትና መከራ ስደተኞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብ መደጎሚያ ወደ አገር ውስጥ መላካቸው የምንዛሬ እጥረቱን የሚሸፍንለት በመሆኑ ህገ ወጥ ስደቱንም ቢሆን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል። የአገዛዙ ጭንቀት የምንዛሬ እጥረት እንጅ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች  የመከራ ህይወት ግድ አይሰጠውም።

ምዕራባዊያኑም ቢሆን ለራሷ ዜጎች መሆን አቅቷት በወደቀ አገዛዝ ስር የምትከላወስ አገር መሆኗን እያወቁ “ኢትዮጵያ የስደተኞች ቤት” ሲሉ ከደቡብ ሱዳን የምንሻል መሆናችንን በምፀት ይነግሩናል። ራሱን ከሱማሌያ እና ከኤርትራ ፈራሽ “መንግሥታት” ጋር የሚያወዳድረው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ዜጎች አሰቃቂ የስደት ገመና ደብቆ ስለጎረቤቶቹ ያወራል።

የኢትዮጵያን ድንበሮች ተሻግሮ የሚደረግ ስደት እጅግ የከፋ አደጋ ያለው ተግባር መሆኑ እየታወቀ ኢትዮጵያዊያኑ ወጣቶች ወደ ኋላ አላሉም። በየጊዜው ከሚመጡ መረጃዎች አኳያ የስደቱ ቀዳሚ ተሳታፊ ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ (አዲስ አበባን በውስጠ ታዋቂነት ይዘን) ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ያህል የበረታ በደል እንደሚፈጽም አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው። ከዚህ እውነታ አኳያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ስደትን ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ በመነሳት በፍቃዳቸው የሚያደርጉት አለመሆኑን መረዳት እንችላለን። ይልቁንስ ከፖለቲካ መዋቅሩ ዘረኛ አካሄድ የተነሳ የኢኮኖሚ የኃይል ምንጮች (የገቢ ሁኔታ) ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመንፀባረቁ ውጤት ነው። በጥቅሉ ስደት ከ”ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ ነው ስንል የኢኮኖሚ ውድቀቱ ከፈጠረው ጥልቅ ድህነት ባሻገር በፖለቲካ ጉዳይ በገፍ የተሰደዱ/ የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር የበዛ በመሆኑ ጭምር ነው።

“ጠላት” ካላበዛ ህልውናውን የሚያስረግጥ የማይመስለው ህወሓት/ኢህአዴግ በግፍ ጭቆና አስመርሮ ከአገር የሚያስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን የአገዛዙ ራስ ምታት ሲሆኑ እየታየ ነው። የዲያስፖራው ፖለቲካዊ መከፋፈልና የውስጥ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአገዛዙን ውድቀት በማፋጠኑ ረገድ ዲያስፖራው ደጋፊ ኃይል ነው። ላወቀበትም የመርዛማ ፍሬው ማርከሻ (ማምከኛ) ከምንጩ ዳር ይገኛል።

ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት በግፍ ሲገዙ የቆዩት የህወሓት/ኢህአዴግ ፖሊሲዎች ያፈሩት እነዚህን መርዛማ ፍሬዎች ብቻ አይደሉም። የእነዚህ ፖሊሲዎች ባለቤቶች ግን ማን እንደሆኑ ከላይ በመግቢያው ላይ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ በሚገባ ተናግረውታል። እንዲህ ነበር ያሉት፤

“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …”።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events