Date: Wednesday, 11 October 2017
(ዘ-ሐበሻ) በአምቦ፣ ዶዶላ እና ሻሸመኔን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ዛሬ እንደ አዲስ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲደረግ ዋለ:: በሻሸመኔ መንገድ እስከመዘጋጋትና የሰው ሕይወት እስከመጥፋት ያደረሰ ተቃውሞ መደረጉም ከስፍራው የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል::
የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው እንደገለጹት በዛሬው ተቃውሞ በትንሹ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን እና ከሰላሳ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ነው::
በከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሻሸመኔው ተቃውሞ አምስት ሰዎች መገደላቸውን አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸው ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ ም ዕራብ ሃረርጌ ውስጥ በምትገኘው በቆቲ ከተማ ውስጥ ተገድለዋል ብለዋል::
በተያያዘ ዜና የጀርመን ድምጽ ራድዮ ከአዲስ አበባ በ126 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን ተችተዋል ሲል ዘገበ:: “የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ የመንግሥት ሠራተኞች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞው ትልቅ ነበር ሲሉ ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል። የዓይን እማኞች እንደሚሉት ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት አካባቢ የጀመረው ተቃውሞ እስከ ስድስት ሰዓት ዘልቋል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ኦሮሞ ሊዋሐድ ይገባል የሚሉ ጥሪዎች ተደምጠዋል የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ መንግሥት ይውረድ የሚል መፈክርም ተደምጧል ብለዋል።” ያለበትን ዘገባ እንደወረደ ያንብቡት::
“በቃ ሕብረተሰቡ በሙሉ ማለት እንችላለን ከተማው አልቀረም ጫፍ እስከ ጫፍ ብዙ ነበረ። ደስ የሚል ነበረ። በሰላም ነው የተጠናቀቀው። መፈክሮች ወያኔ ይጥፋ፤ ወያኔ ይብቃን ካሁን በኋላ ኢሕአዴግ አይግዛን ኦሮሞ ራሳችንን እናስተዳድራለን ነው።”
የተቃውሞ ሰልፉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በወጣቶች ብቻ ሳይሆን መላ የከተማዋን ነዋሪዎች አካቷል የሚሉት ሌላኛዉ የአምቦ ነዋሪ ለሁለት ሰዓት መካሔዱን ተናግረዋል። የተቃውሞ ሰልፈኞች የመብት ጥያቄዎችን ጠይቀዋል የሚሉት የዓይን እማኙ በአካባቢው የነበሩት አድማ በታኝ ፖሊሶች ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል። በአምቦው ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፈኞች ፋብሪካ መነቀል የለበትም፤ ዜጎች ከሶማሌ ክልል ሊፈናቀሉ አይገባም የሚሉ መፈክሮች ማሰማታቸውን የከተማዋ ነዋሪ ነኝ ያሉ ግለሰብ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ከአምቦ ባሻገር ሻሸመኔ እና ዶዶላን በመሳሰሉ አካባቢዎችም ተደርጓል። የዶዶላው ነዋሪ አቶ አህመድ መሐመድ እንደታዘቡት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ከወትሮው በተለየ አመራሮች እና የጸጥታ ኃይሎች ጭምር የተሳተፉበት ወጥነትም የነበረው ነው።
በዶዶላው ተቃውሞ በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ይፈቱ ከሚለው ጥያቄ ባሻገር የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቷል ሲሉ የዓይን እማኙ አክለዉ ነግረውናል።
በሻሸመኔ ከተማ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ አንድ የተመታ ሰው አለ የሚል መረጃ ቢኖርም ለማረጋገጥ ሳንችል ቀርተናል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችም በተደጋጋሚ ያደረግናቸዉን የስልክ ጥሪዎች አልመልሱም።