Dehai News

(አል-ዐይን) የኤርትራን ሰራዊት ከኢትዮጵያ የማስወጣት ሂደት መጀመሩ ተገለፀ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Thursday, 03 June 2021

የኤርትራን ሰራዊት ከኢትዮጵያ የማስወጣት ሂደት መጀመሩ ተገለፀ

በጦርነቱ ምክንያት የተዘጉትን የሽሬ እና ሁመራ አውሮፕላን ጣቢያዎችን ለመክፈት ዝግጅት መጀመሩም ተጠቁሟል

አል-ዐይን 
2021/6/3 16:39 GMT

መንግስት በትግራይ ጉዳይ ሁሉን አቀፍ ውይይት ሊያደርግ መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ጉዳይ ያዘጋጀውን የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ይህ የምክክር መድረክ በትግራይ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ እና በተለያዩ ተቋማት እየተነሱ ባሉ ቅሬታዎች ላይ ግልጸኝነትን መፍጠር ዓላማው አድርጓል።

በዚህ መድረክ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የሰላም ሚኒስትር ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ፣ የኢንሳ ዳይሬክተር ፣ የአደጋ መካለከል እና ዝግጁነት ኮሚሽነር ፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እንዲሁም ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ጊዜ እንዳሉት ፣ መከላከያ ሰራዊት በክልሉ ሕግ በማስከበር ስራ ውጤታማ ስራ አከናውኗል።

ሰራዊቱ በተለያዩ አገራት ተሰማርቶ “ውጤታማ ስራ አስመዝግቧል” ያሉት ሚኒስትሩ በትግራይ ሰራዊቱ ፈጸማቸው ተብለው የሚነሱ “የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል።


የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው በትግራይ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለሰብዓዊ መብት እርዳታ የተጋለጡ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን በሶስት ዙር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው ለመመለስ ከትግራይ እና አማራ ክልል አስተዳደር ጋር ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።


ይህ በዚህ እንዳለም 46 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑ የጤና መሰረተ ልማቶች አገለግሎት በመስጠት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።

በክልሉ ለእርሻ ምቹ ከሆነው መሬት ውስጥ 70 በመቶ ወይም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመኸር እርሻ ዝግጁ በመደረግ ላይ ከመሆኑም በተጨማሪ ምርጥ ዘር እና ሌሎች ግብዓቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወድመው የነበሩ የጨርቃጨርቅእናሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ምርት መግባታቸውም የተገለጸ ሲሆን አገለግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማትም ቀስ በቀስ በመከፈት ላይ እንደሆኑ በምክክር መድረኩ ላይ ተገልጿል።

በክልሉ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳትፈዋል የተባሉ 60 ተጠርጣሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ደርጅት ጋር በመቀናጀት ተጨማሪ ምርመራ እነደሚያደርግም አክለዋል።

የአገር መከላከያ ሚኒስተሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በበኩላቸው የኤርትራን ሰራዊትን ከኢትዮጵያ የማስወጣት ሂደት መጀመሩን ገልጸዋል።

የሕወሓት ኃይል ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር መዋጋት በሚያስችለው ቁመና ላይ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ፣ ሕወሓት በኪስ ቀበሌዎች ላይ የደፈጣ ጥቃት ለማድረስ እየሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።


በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ድጋፍ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የረድዔት ተቋማት ሰራተኞች የሚጠቀሙባቸው የኮሙንኬሽን መሳሪያዎች ለወታደራዊ አገልግሎት ሊውሉ እንደማይችሉ የገለጹት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ናቸው።


ያልተፈቀዱ የኮሙንኬሽን መሳሪያዎችን ደብቀው ለማሳለፍ ሲሞክሩ የተያዙ የእርዳታ ድርጅቶች መኖራቸውን እና ኢትየጵያዊ ሰራተኞቻቸውንም ከስራ እያሰናበቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ በምንም መንገድ “አይፈቀድም” ሲሉም ዳይሬክተሩ አስጠንቅቀዋል።

የሰብዓዊ ድርጅቶች ድርጊት “ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሊሆኑ አይገባም” ይህ ሆኖ ከተገኘም “እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ዶክተር ሹመቴ አሳስበዋል።

 የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዶክተር አብርሀም በላይ በበኩላቸው በክልሉ ከተወሰኑ ኪስ አካባቢዎች ባለፈ “በአብዛኛው የክልሉ አከባቢዎች ድጋፎች እየተደረጉ ነው” ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት እና የክልሉ አስተዳደር በጦርነቱ የወደሙ የቴሌኮሙኒኬሽን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት እና ወደ ስራ በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ዶክተር አብርሀም ተናግረዋል።

“አሁን የምንፈልገው የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ ነው” ያሉት ዶክተር አብርሀም ተፈናቃይ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለስ ስለሚፈልጉ መሰረታዊ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን እንዲያገኙ ማድረግ አለብን ብለዋል።


የሁመራ እና ሽሬ አውሮፕላን ጣቢያዎችን አገለግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አብርሀም ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በምክክር ጉባኤው መዝጊያ ላይ መንግስት በትግራይ ጉዳይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።ተሳትፎ ደቂ ኣንስትዮ ኣብ ቃልሲ ኤርትራ| Eritrean Women participation in the armed struggle - ERi-TV

Dehai Events