Date: Sunday, 13 August 2017
ገዥው የህወሓት ቡድን የኦሮሚያ እና አማራ ክልል አስተዳደሮችን ወቀሰ፡፡ በሁለቱ ክልሎች እየተካሔደ ያለውን ህዝባዊ አድማ እና ተቃውሞ በሚገባ አልተቆጣጠሩም ተብሎ በህወሓት ግሳጼ የደረሰባቸው የሁለቱ ክልል አመራሮች፣ ‹‹ተቃውሞዉን ለማዳፈን እንዝላልነት ታይቶባችኋል›› ተብለዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ህወሓት የሚያሽከረክራቸው የሁለቱ ክልል አመራሮች፣ አሁንም ድረስ በየክልሎቻቸው የቀጠለውን ተቃውሞ ማስቆም አለመቻላቸው በህወሓት ዘንድ ከፍተኛ ብስጭት ፈጥሯል፡፡
በአሮሚያ አምቦ፣ ወለጋ፣ ወሊሶ፣ ደምቢዶሎ እና መሰል አካባቢዎች እንዲሁም በአማራ ክልል ባህርዳር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልድያ እና በሌሎች አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞች እየተደረጉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከስራ ማቆም አድማ ጀምሮ ሌሎች የተቃውሞ ድምጾችን እያሰማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አሁንም ድረስ በተቃውሞው እንደገፋበት ይገኛል፡፡ የተቃውሞዉ እንቅስቃሴ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሔዱ ስጋት ላይ የጣለው የትግራይ ነጻ አውጭ ቡድን ህወሓት፣ የዛሬ ዓመት እንደነበረው ዓይነት ከፍተኛ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል የሚል ጭንቀት ውስጥ ወድቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር አጋዚ ወታደሮችን ጨምሮ ሌሎች የፖሊስ አባላትን ለግድያ የሚያሰማራው ህወሓት፣ አሁን ደግሞ ድንበር ጠባቂ ወታደሮችን ተቃውሞ ለመበተን መጠቀም ጀምሯል፡፡ ስራቸው ድንበር መጠበቅ የሆኑ እና ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሊኖራቸው የማይገባ የሰራዊቱ አባላት፣ የህወሓትን መንግስት በተቃወሙ ዜጎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁን ሰዓት በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘው የህወሓት ቡድን፣ የተንገዳገደውን በትረ ስልጣኑን መልሶ ለማቆም ጥረት እያደረገ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡