ራሳቸውን “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር” ብሎ በመሰየም የትግራይን ሕዝብ ሽፋን በማድረግ፤ “የምታገለው ለአንተ ነጻነት ነው” በማለት፤ መልሶ እታገልለታለሁ ያለውን ሕዝብ ያስጨፈጨፈው፣ ያስራበው፣ የግፈ ሰለባ ያስደረገው፣ … ራሱን ህወሓት እያለ የሚጠራው የወንበዴዎች ቡድን የኢትዮጵያን የሥልጣን መንበር ከተቆናጠጠ በኋላ የትግራይ ሰዎችን በሌላው ኢትዮጵያዊ ለማስጠላትና “ስም ለማሰጠት” እንዲሁም ለማጠልሸት ባለፉት 26ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል። እነዚህ በኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ አነጋገር “የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ …” የኢትዮጵያን ሃብት እየዘረፉ በትግራይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የትግራይ ተወላጆችን የተለያዩ ስልቶችን – ከግድያ እስከ ማስገደድ – እየተጠቀሙ የወንጀላቸው ተባባሪ እንዲሆኑ በማድረግ፤ ትግራዮችን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማስጠላት ጉዳዩን ከራሳቸው በማውረድ በሕዝብ መካከል የሚደረግ በማስመሰል እኩይ ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። ለሆዳቸው ያደሩን በፕ/ር መስፍን አነጋገር “አእምሯቸው የሻገተባቸው” ይህንን ማታለያና ማባበያ እየወሰዱ ከሌላው የኢትዮጵያ ወገናቸው ጋር ሆድና ጀርባ በመሆን “ነጻ አውጣኝ” ብለው በስምምነት ያልሰየሙት ቡድን ባዶ ተስፋ እየሰጠ የውንብድና ተግባር ሲፈጽምባቸው የተግባሩ ተባባሪዎች ሆነዋል።
ባለፉት 26ዓመታት ከግንቦት 20 “ካተረፍናቸው” “መርዛማ ፍሬዎች” አንዱ የዘውግ ወይም የጎጥ (የጎሣ) ፖለቲካ ነው። ከዚህ የከበረው ደግሞ ላለፉት 26ዓመታት አገር “በነጻ አውጪ” ስም በግፍ እየገዛ ያለው ህወሓት ብቻ ነው!
መርዛማ ፍሬ 9. የከረረ የዘውግ ፖለቲካ!
የኢትዮጵያን አገራዊ የማንነት እሴቶች ለአዲሱ የፖለቲካ ሥርዓት ማዋቀሪያነት መጠቀም ለኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይሎች የተሻለ መንገድ መሆኑን የሚወተውቱት የፍልስፍና ምሁሩ ፕ/ር መሳይ ከበደ ናቸው። ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚስተዋሉት ችግሮች ሁሉ ቀዳሚና እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ዘውጋዊ ፖለቲካ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ህወሓት/ኢህአዴግን ለመጣልና አዲስ ሥርዓት ለመመስረት ስለ ዘውግና ዘውጋዊ ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት (መያዝ) አስፈላጊ እንደሆነም ይመክራሉ። “ህወሓት/ኢህአዴግ ከተሸነፈ የዘውግ ፖለቲካ በራሱ ይጠፋል” ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት መሆኑን ያሰምሩበታል።
የፕሮፌሰር መሳይ ስጋት ተገቢ መሆኑን እናምናለን። ለዚህም በኢትዮጵያ የዘውግ ብሔረተኝነት ጅማሮ ከማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥልቅ ቅሬታ ጋር በተያያዘ የሚነሳ በመሆኑ ነው። የዘውግ ፖለቲካ ከ26 ዓመት ወዲህ የተጀመረ ሳይሆን ከዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ነገሥታት ጋር የነበረው ግንኙነትና የማዕከላዊ መንግስቱ አመሰራረት፣ አወቃቀር፣ አሰያየም፣ … ጉዞ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጭብጦችን መነሻ በማድረግ የታሪክ ጡዘት በመፍጠር በ“ጨቋኝ” Vs “ተጨቋኝ” ትርከት ዘውጋዊ ንቃት መፍጠር አገር ገንጣዩ የህወሓትም ሆነ በኢትዮጵያ “አንድነት እናምናለን” የሚሉ የዋለልኝ መኮንን “ደቀመዛሙርት”ና የእስካሁን አድናቂዎች የሆኑት የ“ያ-ትውልድ” ዘውጌ ብሄርተኞች ውርስ ምልከታ ነው። የዘውግ ብሄርተኝነት መከራከሪያውም በደልና ጭቆናው መደባዊ ይዘት ያለው አለመሆኑን በ“ማመን” የተነሳ ነው። በዚህ መሰል ትርክት በየራሳቸው የታሪክ ክህደት መስመር “አገራዊ አጀንዳ” ይዘናል ያሉትን ለጊዜው ተወት ተደርገው ህወሓት እና ኦነግ የመጨረሻ አቅማቸውን በመጠቀም በዘውጎች መካከል ደማቅ የልዩነት መስመር ለማስመር ሞክረዋል። የኢትዮጵያን ማህበረ-ባህል ኑባሬ በመፋቅ መደባዊ ጭቆናውን ወደ ዘውጋዊነት በመለጠጥ ፈጠርን የሚሉት ዘውጋዊ ንቃትም አገር አፍራሽ ሚና ከመጫወት የዘለለ አልሆነም።
የሩብ ክፍለ ዘመኑ መዋቅራዊ የዘውግ ፖለቲካ አካሄድ ፍፁም አገር አፍራሽ የሆነ የከረረ ስሜት ያለበት እንደሆነ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምስቅልቅል ገጽታ ህያው ምሳሌ ናት። አገሪቱ ውስጥ ብዙ ትንንሽ “አገሮች” እየተፈለፈሉ በመሆናቸው ዜግነትን የሚንተራሰው የጋራ ማንነት ተጨፍልቆ የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” ባዩ በዝቷል። “ከክልላችን ውጡ” የሚለው ኃይል አከል እርምጃም የዚህ የከረረ የዘውግ ፖለቲካ ወላጅ ነው። ለብዙ ዘመናት ያለ ድንበር ከለላ አብረው ሲኖሩ የነበሩ ጎሣዎችና ዘውጎች፣ የዘውግ ፖለቲካ በከረረ መንገድ መዋቅራዊ ይሁንታ ማግኘቱን ተከትሎ በተሰሩ ሰው ሰራሽ ወሰኖች የተነሳ የማንነት ጥያቄ ለልዩነት መስፋት ሰበብ ሆኗቸዋል። እነዚህ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ባልተካለለው ድንበርና ወሰን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ ከመጠቀም አልፈው ወደ ርስበርስ ግጭት መግባት የጀመሩት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ነው።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ እየታዩ ያሉ የድንበር ግጭቶች በአፍሪካ በመጀመሪያዎቹ የድህረ-ቅኝ ግዛት ዘመናት ሲስተዋሉ ቆይተዋል። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የፈጠሯቸው ሰው-ሰራሽ ድንበሮች ለአፍሪካዊያን የእርስ በእርስ ግጭት መነሻ ምክንያት እንደነበሩ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው። በአባቶቻችን ተጋድሎ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ቅኝ-ገዥ በመያዟ የድንበር ግጭቶችና ዘውግ ተኮር ትንቅንቶች መገለጫዋ ሆኗል።
ለአንድም ኅልዮታዊ ትንታኔ የማይመቸው የዘውግ ፖለቲካ በከረረ መልኩ እየተለጠጠ መሄዱ ኢትዮጵያ ይህን ክፉ ጊዜ እንዳትሻገር አንቆ ይዟታል። በአንድ ዘውግ (ለአብነት፡- ኦሮሞ) ስር ከአምስትና ስድስት በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በተቋቋሙባት ኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ የሊሂቃኑ አቋራጭ የሥልጣን መንገድ ሲሆን ይታያል። “መገንጠልን መደገፍ በራሱ የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን ያረግባል” የሚለው የቀደመ ምልከታ ዛሬ ላይ የበዛ ፍንገጣ የሚስተዋልበት የብተና ደወል ሆኗል። በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሂደት ውስጥ አካባቢያዊ ማንነት ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ዘውጋዊ መፈክሮችን ከማነብነብ ባለፈ አገሪቱ የመጣችበትን ረዥም የታሪክ ውጣ ውረድ፣ የነፃነትና የድል መንገድ እንዲሁም ማህበራዊ ስሪት በቅጡ ያላወቁ “ኢትዮጵያ” በሚለው ሥም ጥላቻ የተነደፉ ጨለምተኛ (NIHILIST) ትውልድ እዚህም እዚያም እየታየ ነው።
በተካረረው የዘውግ ፖለቲካ መስመር መሃል፣ ህወሓት ዘውጎችን የጎንዮሽ እያፋጠጠና እያጋጨ ትግራይን እንደአገር መገንባቱን ቀጥሏል። የከፋ የርስ በርስ ጦርነት ጋባዡ ህወሓት ኢትዮጵያን ወደ ብተና እየገፋት ይገኛል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዘውጋዊ ፖለቲካን ማጥፋትም ሆነ የብቻ መሰረታዊ መንገድ ማድረግ የሚታሰብ አይደለም። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ እንደሚሉት ግን በመካከላዊ አሰራር የአገሪቱን አንድነትና ዘውጋዊ ፖለቲካ እንዲተባበሩ ማድረግ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ርዕይና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ቅዱስ ዴሞክራሲ ያስፈልጋል። በዘመነ-ህወሓት ይህን መተግበር ቀርቶ ማሰብ በራሱ በ“ሽብርተኝነት” እንደሚያስወነጅል የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ ህያው ምሳሌ ነች።
መርዛማ ፍሬ 10. ዘውጋዊ ኢኮኖሚክስ
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የገዥ ኃይል አስኳል ህወሓት መሆኑን ማወቅ እንደማይከብደው ሁሉ በአገሪቱ ውስጥ ቁጥራቸው የበዛ የኢኮኖሚ ሊሂቃኖችም ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የተገኙ መሆናቸውን ለመጠራጠር የማይቻል ያፈጠጠ እውነት ላይ እንገኛለን። “ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ ፖለቲካዊ የበላይነቱን ያረጋግጣል” በሚለው ድርጅታዊ “ፍልስፍና” የሚመራው ህወሓት የአገርና የህዝብ ኃብትን ለትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ማደሉን ከተያያዘው ሩብ ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል።
ዛሬ ላይ በአደባባይ አፍጥጦ የሚታየው የትግራይ ተወላጆች የኢኮኖሚ የበላይነት እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሦስት የሽግግር ጊዜ ማዕቀፎችን አልፏል። ሦስቱም የሽግግር ጊዜያቶች የራሳቸው የሆኑ ታሪካዊ አመጣጦች ቢኖሯቸውም የኢኮኖሚ የበላይነቱን በማፍጠኑ ረገድ ተያያዥነታቸውና ተደጋጋፊነታቸው ከፍ ያለ ነው።
ለትግራዮች የኢኮኖሚ የበላይነት መፈጠር በር ከፋች የሆነው የመጀመሪያው የሽግግር ጊዜ ድህረ-ደርግን ተከትሎ ከ1983 – 1991 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ህወሓት በአገሪቱ ላይ በዘረጋው ዘውጋዊ የፖለቲካ መዋቅር ላይ የበላይነቱን ለማስረገጥ በማዕከላዊ “መንግስቱ” እና በክልሎች በየዘርፉ በግልጽና በስውር ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሰጡ ትግሬዎችን መመደብ የጀመረበትና የኢትዮጵያን የፖለቲካል-ኢኮኖሚ መዋቅር በራሱ ፍላጎት መቅረጽ የቻለበት ጊዜ ነበር። በመከላከያና ደህንነት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ትግራይ ተወላጆ ቁልፍ ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ የተደረገበት፣ የቀበሌና የኪቢያድ ቤቶች እንዲሁም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ምሪት እነሱው በብዛት ያገኙበት፣ በተለየ መልኩ በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል የብቻ ኮንትሮባንድ ንግድ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገበት፣ በከተሞች የአነስተኛና መካከለኛ የንግድ እንቅስቃሴዎችን (ሸቀጣሸቀጥ፣ የልብስ ንግድ፣ ጋራዥ፣ የወርቅና ብር ቤቶች፣ …) ከኤርትራዊያን ጋር ጎን ለጎን መስራት የጀመሩበት፣ በየክፍል ሃገሩ የነበሩ የአገሪቱ ሃብቶች (እንደ ጎንደሩ ግዙፍ ጄኔሬተር፣ የጋምቤላ ጄኔረተር፣ የአዲስ አበባ ትልልቅ የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች፣ … ወዘተ) ወደ ትግራይ ክልል በመጓጓዝ፣ የክልሉ ህዝብ አዲስ የሥነ-ህዝብ አሰፋፈር እንዲከተል በማድረግ በተለይም በምዕራብ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ ሁመራ፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ በጥቅሉ ወልቃይትንና አካባቢውን በመጠቅለል ነባር ህዝቡን በመግፋትና በመዋጥ ለም መሬቱን የብቻ ተጠቃሚ ለመሆን የተሰራውን ግፍ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው። ከዚህም ባለፈ የጦርነት ፍፃሜ የብቻ ተቋዳሽ የሆነው ህወሓት ከመንግስታዊ መዋቅሩ በተጨማሪ የዘውግ ኢኮኖሚ ኢምፓየር መፍጠሪያ መሳሪያ የሆነውን ግዙፉን ኢፈርት የህዝብ ንብረቶችን በመጠቅለል እና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ ንግድና ልማት ባንክ ብድር በመውሰድ ራሱን በማግዘፍ ትግራይን እንደአገር ማደራጀት የጀመረበት የመጀመሪያው የጊዜ ማዕቀፍ ነው።
ለትግራዮች ዘውጋዊ የኢኮኖሚ የበላይነት ሁለተኛ የጊዜ ማዕቀፍ የሆነው ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ከተነሳ በኋላ ከ1991 – 1997 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው። በድህረ-ደርግ የመጀመሪያ ጊዜያት በከተማ አፍላ ፍቅር ውድቀው የነበሩት ሻቢያና ህወሓት በድንበር ግጭት የተነሳ ሁኔታዎች መስመር ሲስቱ የኤርትራ ተወላጆ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደረገ። በዚህም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ ከቀደመው የጊዜ ማዕቀፍ መጠነኛ ለውጥ የታየበት ሆነ።
ከኤርትራዊያን ስንብት በኋላ የትግሬዎች በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እጃቸው እየረዘመ መጣ። መዋቅራዊ ድጋፍ ባለው መልኩ ኮንትሮባንድ እና ግብር አልባ ንግድን በዋና ዋና ከተሞች በበላይነት መከወን ቀጠሉ። ከንግድ እንቅስቃሴው ባሻገር በፖለቲካ መዋቅሩ ከህወሓት ዳግማዊ “ህንፍሽፍሽ” በኋላ በመለስ ዜናዊ መሪነት በጥገኞች የኢህአዴግ አልባና አጋር ድርጅቶች ታዛዥነት የትግራዮች የኢኮኖሚ ሊሂቃን ግስጋሴን የሚያቆመው ጠፋ። ከትግራይ ክልል ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ይህን ሲመል በክልሉ ውስጥ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና ልዩ ፖሊሲዎች አፈፃፀም ከኤፈርት፣ ማረትና ትልማ ፕሮጀክቶች ጋር እየተመጋገበ ትግራይን ከድቀት ወደ ከፍታ አሻገራት።
በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባገኘው ጦርነት የደቀቀ ኢኮኖሚ ከመታቀፏ በተጨማሪ የጦርነቱ ማህበራዊ ቀውስ የከፋ ደረጀ የደረሰበት ጊዜ ነበር። ይህም ሆኖ ትግራዋያን ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ፣ ከአድዋ እስከ ቦረና፣ ከአክሱም እስከ ጅጅጋ፣ ከሽሬ እስከ ጎጃም፣ ከአዲግራት እስከ ጋምቤላ፣ … ድረስ የኢኮኖሚ የበላይነቱን ከማስቀጠል ወደኋላ አላሉም።
አዲስ አበባ ላይ በልዩ ሁኔታ በቦሌ፣ ሃያት ሁለት፣ ሳሪስ፣ ተክለሀይማኖት፣ ቄራ፣ ሲ.ኤም. ሲ.፣ ፒያሳ ባሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የትግራዮች ድርሻ ከፍ ሊል ታይቷል። መርካቶ ላይም እንዲህ እንዳሁኑ ጉልህ ባይሆንም አንፃራዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩት። እስከዚህ ጊዜ ድረስ የትግራይ ተወላጆችን የኢኮኖሚ የበላይነት በተመለከተ በኢ-መደበኛ ወጎች ከማውራትና በነፃ-ኘሬስ ላይ ደፋር ፀሐፍት “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ (ሌላው አገር ይድማ)” በሚል ያሰሙ ከነበረው ነቀፌታዎች ባሻገር ጉዳዩን በፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ወደ አደባባይ የወጣ አንድም ኃይል አልነበረም። ግና፤ የዘውግ ኢኮኖሚክሱ እየባሰበት ተጠያቂነትና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የዜጎች ኢ-ፍታሃዊ የገቢ መጠን ቋንቋ ተናጋሪነትን መነሻው አድርጎ እየሰፋ በመሄዱ በቅድመ-ምርጫ 97 ወቅት ጉዳዩ የአደባባይ ሙግት ለመሆን በቃ። ዓይን አውጣነትን የተካኑበት የህወሓት ሰዎች “ትግራይ ዛሬም በጦርነት የደቀቀች ክልል ነች” በማለት ተከራከሩ። በወቅቱ የነበረው የአገር ሀብት ምዝበራ በይፋ ከካዝና ማራገፍ ወደ ምርጫ ኮሮጆ ግልበጣ አድጎ ህወሓት፣ የትግራይ ኢኮኖሚ ሊሂቃን እና ከዘውጉ ውጪ ያሉ ጥቂት ታማኝ ባለሃብቶች በንጹሃን ደም እየተረማመዱ የዘውግ ኢኮኖሚክሱን አድማስ አስፉት፤ የገቢ ኢ-እኩልነቱን ከቶም የማይደረስበት አደረጉት።
ድህረ-ምርጫ 97 ላይ ጀምሮ እስከአሁን የዘለቀው የትግራዮች የኢካኖሚ የበላይነት ጉዞ ሦስተኛው የጊዜ ማዕቀፍ ላይ የሚያርፍ ነው። ይህ ጊዜ ህወሓት በሙሉ ጉልበቱ ሆን ብሎ ትግራይንና ተወላጆቹን መጥቀም የጀመረበት ጊዜ ነው። አገሪቱ በተከታታይ አስር ትውልዶች ውስጥ ከፍላ የማትዘልቀው የብድር ዕዳ ውስጥ እየዘፈቀ በ“ልማታዊ መንግስት” ሥም የዘውግ ኢኮኖሚክሱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ቢሮክራሲው ላይ ያለው ዘረኛ ቁጥጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረና እየተጠናከረ መጥቷል። በተለይም ኢሚግሬሽን፣ ውጪ ጉዳይ፣ መከላከያና ደህንነት፣ የማዕከላዊና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ አየር መንገድ፣ ጉምሩክና የቀረጥ ጣቢያዎች፣ ባንኮች … ወዘተ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተወረሩ ናቸው። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ጋብቻ ትስስርና በኗሪነት ቆይታ በየክልሉ ክልላዊ “ዉክልና” የያዙ የፖለቲካ ታማኞች መፍጠር ችለዋል።
በቢልዬን ዶላሮች የሚቆጠር ካፒታል ባለቤት የሆነው ኢፈርት፣ ማረት፣ ትልማ ትግራይን እንደ አገር የመገንባቱን ዘመቻ ተያይዘውታል። ታክስ ተኮር ድጋፍ፣ የባንክ ብድር፣ የመሬት አቅርቦት፣ የተመቻቸላቸው የትግራይ ባለሃብቶች በአገሪቱ የሆቴል፣ የእርሻ፣ የኮንስትራክሽን፣ የባንክ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት፣ በመዝናኛ፣ ማዕድን ምርት፣ የውጭ ንግድና መሰል ግዙፍ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል።
አብሮነታቸውንን የሚያጠናክሩ ማህበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ የልዩነት ግንብ እየከለልን ከመሄዳችን ባሻገር ቋንቋ ተናጋሪነትን የተንተራሰው የገቢ ኢ-እኩልነት የኢትዮጵያን ነገ እጅግ አሰፈሪ አድርጎታል። ትግራዋያን ዛሬ ላይ ያለውን እጅግ የተዛባ የሃብት የክፍፍል ከመቃወም ይልቅ ሁነቱን እንደ “ትልቅ ማህበራዊ ዕድል” በመቁጠር የዘረፋው ተሳታፊ ሲሆኑ እየታየ ነው። የነገ የብቻ ዋይታቸውን በሚያብስ መልኩ የብቻ የኢኮኖሚ ጥቅመኘነት አካሄዱ የበዛ ዋጋ እንደሚያስከፍልና ይህም በህወሓት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሤራ መሆኑ የገባቸው አይመስልም። ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲቃቃሩ ብቸኛ መጠለያቸው ህወሓትን እንዲያደርጉ የታለመ መሆኑን “እንዲጠሉ” የተደረጉት ትግራዮችም ሆነ “እንዲጠሉ” የተደረገው ሌላው ሕዝብ ቆም ብሎ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ለአንድ ዘውግ የሚደረግ የኢኮኖሚ አድልዎ በሌላኛው ዘውግ የከረረ ስሜት ከመፍጠሩ ባሻገር የፖለቲካው ታማኝ የሆኑ አካላት እኔም “የድርሻዬን” ላገኝ እንጅ “ኢትዮጵያ” ምንተዳየ የሚል ከንቱ የጥቅመኝነት ፖለቲካ አሰላለፍ ፈጥሯል። ሞራል የሌለው ትውልድም በገፍ አምርቷል። ይህ የተደረገው ደግሞ ህዝቡን ወደ ጥቅል ድህነት በመክተት ነው። ዘውጋዊ አካሄድ ባለው መልኩ ህዝቡን ሆን ብሎ ደሃ በማድረግ በኑሮ ሃሳብ እንዲጨነቅ ካደረጉ በኃላ መላወሻ ሲያጣ ሆድ አደር ተገዥ ማድረግ የህወኃት የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነው። ገንዘብ አምላኪ ህዝብ በመፍጠር ሰዎች ወንድም እህታቸውን ለጥቂት ገንዘብ ሲሉ አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያደርግ ሰብአዊ ንጥፈት እና አልቦ-ሞራል የሆነ ትውልድ መፍጠር የህወሓት ግብ ነው።
በተለይ ይህ ሁኔታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የሚታይ ሆኗል። በየጊዜው ለመፍረሳቸው ዋነኛ ምክንያቶች ሞራል የሌላቸው ለጥቅም የተገዙ ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ “ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለው የቀደመ ቃለ-ግቡነት በርቀትም እንኳ የማያውቁ የክህደት ህመምተኞች በጥቅም መደለላቸው ነው። በዘውጎች መሀከል የተፈጠረው የገቢ ኢ-እኩልነት አገሪቱን ወደ ርስ በርስ ጦርነት እየገፋት ነው። የአገሪቱ የቀደሙ ማህበራዊ ዕሴቶች መውደም እና የወንጀል መበራከት ግጭት አባባሽ ሆነው ቀርበዋል። ይህም ወደ ትግራዋያን ያዘነበለው የዘውግ ኢኮኖሚክስ ውጤት ነው። ድርጊቱም የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ ነው። መርጠው አንዱን ዘውግ የበላይ ያደርጋሉ ከዚያ እንግሊዞች አፍሪካ ላይ በተለያዩ አገራት እንዳደረጉት አገሩን ለቀው ሲወጡ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ጥለው ይወጣሉ። የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው “ቅኝ-ገዥው” ኃይል የአገር ውስጥ መሆኑና የወጣበትን ዘውግ ለይቶ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ የበላይነት መምረጡ ነው። ትግራይ በየትኛውም መጠን እንደአገር ብትሰራ እንኳ ኢትዮጵያን ለብተና ዳርጎ “ታላቋን ትግራይ” መመስረት ሊሳካ የማይችል ከንቱ ቅዠት ነው። ቅድሚያ የኢትዮጵያን ህዝብ አንጡራ ሃብት መመለስ ለድርድር የማይቀርብ ተግባር ነው። ከዚህ ባለፈ ተይዞ ያለው የነጠቃና የተገንጣይነት መንገድ በ“ጠላት” የተከበበች ትግራይ፣ መፈናፈኛ ያጣች ኩርማን አገር ከመመስረት ያለፈ አይሆንም።
ይህ መንገድ ለትግራዋያን ብቻ ሳይሆን ለራሷ ለትግራይም የሚያዋጣ አይደለም። አገሪቱን በደም ካሳ (ጉማ) መያዥያነት ሰንጎ የያዘው ህወሓት እና የትግራይ ተወላጆች ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል። እየመጣ ያለው መዓት እንኳንስ ለትግራይ ለምስራቅ አፍሪካም ያሰጋል!!
ቀደም ብለው የታተሙት ኣርእስቶች:
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች! (ክፍል 1)
http://dehai.org/dehai/dehai-news/160333