የትግራይ ሕዝብ “ነጻ አውጡኝ” ብሎ ሳይሰይማቸው፣ ሳይመርጣቸው፣ ሳይጠይቃቸው፣ ራሳቸውን “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር” ብለው የሰየሙ ወንበዴዎችና ሽፍቶች የምኒልክ ቤተመንግሥት ከገቡ 26 ዓመታት ተቆጥረዋል። በቂም፣ በበቀል፣ በክፋትና በኢሞራላዊ ተግባራት የተሞሉ፤ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ፈጽሞ የሚያጠራጥር፤ ማንነታቸው ይህ ነው ተብሎ የማይታወቅ፤ በሐሰት ስም ከበረሃ እስከ ቤተመንግሥትና ዓለምአቀፍ መድረክ ላይ የታዩ፤ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የትግራይን ሕዝብ ያስጨፈጨፉ (ሐውዜንን ይጠቅሷል)፤ ሲነሱ አንዳች ገንዘብ ያልነበራቸው መናጢዎች በበረሃ የድሃ ረሃብተኛ እህል ዘርፈው በመሸጥ፤ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ሐብት ሙልጭ አድርገው ዘርፈው ሲያበቁ “የራሳችን ንብረት ነው” በማለት ኤፈርት የሚባል የወንበዴዎች ሃብት ማከማቻ ቋት የፈጠሩ፤ ከበረሃ እስከ መንግሥታዊ ሥልጣን ድረስ ውሸት መለያቸው የሆነ፤ የሃይማኖት ተቋማትን ያረከሱ፤ ተዘርዝሮ የማያልቅ መርዛማነት በኢትዮጵያ የተከሉ … ህወሓት እና ህወሓታውን እነዚህ ናቸው። ዕፍረት ዓልባ ድንቁርናቸው በለገሳቸው አንደበትም እስካሁን “በነጻ አውጪ ስም” አገር ለምን እንደሚገዙ ሊያስረዱን ይሞክራሉ።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኮ/ሎ ጎሹ ከ26 ዓመት በፊት በትክክለኛ ሁኔታ ገልጸዋቸው ነበር፤ እንዲህ ሲሉ “… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል።
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች ክፍል ሦስት ይቀጥላል፤
መርዛማ ፍሬ 5. የ“መንግሥት” ውሸት!
በፖለቲካል ሳይንስ መዝገበ ቃላት “መንግስት” (state) የሚለው ቃል ከባህሪያት አቀራረብ አኳያ አከራካሪ እንደሆነ ይነገርለታል። “መንግስት” እንደ መንግስት ሊያሟላቸውና ሊኖሩት የሚገቡ ባህሪያት እስከሌሉት ድረስ “መንግስት” የሚለውን ቃል የሚመጥን አይሆንም። በትንሹም ቢሆን አንድ መንግስት የህዝብ ውክልና ያለው፣ በህዝብ የተመረጠ፣ ይፋዊ መዋቅሮችን በየዘርፉ ዘርግቶ ያለ አንዳች ልዩነት ለአገር ዕድገት የሚተጋ፣ ስለዜጎቹና ሉዓላዊነቱ ግድ የሚሰጠው፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች (ባለሥልጣናት) ያሉበት ስብስብ “መንግሥት” የሚለውን ቃል ከሚተረጉሙልን ጭብጦች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ህወሓት/ኢህአዴግ ከመነሻው ጀምሮ ከአቅሙ በላይ በፕሮፓጋንዳ የተወጠረ በሃሳዊነት የቆመ እውነት ጠል ድርጅት መሆኑን የመጣበት የታሪክ መንገድ የሚነግረን እውነት አለ። በተዛቡ የታሪክ ትርክቶች እና በክህደት የታጀበውን የድርጅቱን “ሚኒፌስቶ” እያሰመርንበት ከዚህ የጥላቻ መሳሪያው የሚጨለፉ ውሸቶች ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸው መሆናቸውን እናስታውሳለን። በበበረሃ የውንብድና ትግል ወቅት “በድምፀ ወያኔ” ራዲዮ፣ በ“ወይን”፣ “ታጠቅ”፣ … በተሰኙ የህትመት ውጤቶቹ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው አካል የነበሩ ጉዳዮች ዛሬም ድረስ ይዘታቸውን እያሰፉ በ”መንግስታዊ” መዋቅሩ በስፋት ይንፀባረቃሉ። “ለሽምቅ ውጊያ ፕሮፓጋንዳ ትልቅ ኃይል ነው” የሚለው መከራከሪያ የግራ ኃይሎች ሃሳብ ነው። ፕሮፓጋንዳ ሲባልም አንድን ጉዳይ ለጥጦና አስፋፍቶ ማውራት በሚል አግባብ ሊተረጎም ይችላል።
የህወሓት/ኢህአዴግ የበረሃ ፕሮፓጋንዳ ከዚህም የወጣ ፍፁም ምናብ ወለድ ነበር። “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተሰኘው ተከታታይ የፈጠራ ቅፆች ለዚህ አብይ ማስረጃ ናቸው። የዚህ አይን ያፈጠጠ ውሸት ልማድ ዛሬ ላይ የምርጫ ኮሮጆን በመገልበጥ፣ የአደባባይ መንግስታዊ ፍጅትን በ“ህጋዊነት” ሽፋን ሥም በማፅደቅ፣ የአንድ ዘውግ የፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት የአገሪቱ “ዕድገት” ማሳያ አድርጎ በማቅረብ፣ ጎተራ ላይ የሌለ የገበሬ ምርት በቁጥር ፈጠራ (ድርደራ) ብቻ ያለ አስመስሎ በማቅረብ፣ የመንገድ፣ ድልድይ፣ ህንፃ እና ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማስፈፀሚያ ብር ዘርፎ የግንባታውን ሂደት በበሬ ወለደ የቁጥር (ፐርሰንት) ዘገባ አሰልቺ ዜና ደጋግሞ ከመስራት እስከ ተራራ መስረቅ ድረስ የደረሰ “መንግስታዊ” ውሸት መስማት ከተላመድን ሩብ ክፍለ ዘመን ተሻገርን።
አገዛዙ እንደአገር እያስፋፋው ያለው የውሸት ባህል በጊዜ ሂደት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል እየለመደው በመሄዱ ህዝቡ የውሸት ባህል ነፀብራቅ ውጤት እንዲሆን አድርጎታል። ተዘቅዝቆ የተተከለን ችግኝ በሪፖርት የሚያፀድቁት የአገዛዙ ካድሬዎች በ1፡5 የጥርነፋ አካሄድ ያልታቀደው ታቅዷል፣ ያልተሰራው ተሰርቷል፣ … በሚል የሚያስተላልፉት ሪፖርት በተጠና የፕሮፓጋንዳ ስልት የ“ዜና” ግብዓት ሲሆን እየታየ ነው።
“መንግስት” ነኝ ባዩ የሽፍቶች ስብስብ የአገዛዙን ዕድሜ ለማስቀጠል ይዋሻል፣ የመንግስት ሰራተኛው ስለሚሰራው ስራ ይዋሻል፣ ነጋዴው ግብር ለማስቀነስ ይዋሻል፣ ትልልቆቹ ሙያና ሙያተኞችም ከውሸት አዙሪቱ ሲወጡ አልታዩም። የኃይማኖት መሪዎች ሃሳዊነት ባለው መልኩ የ“መንግስት” ውሸት አባሪ ተባባሪ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ አሁን አሁን “ቁጥር” የተባለ ነገር በእጅጉ የረከሰባት አገር ሆናለች። የአገሪቱ የኢኮኖሚ “ዕድገት” ላለፉት አስር ዓመታት በሁለት አሃዝ ተመነደገ ሲሉ ሕዝቡ ግን ዕድገቱን ሌማቱ ላይ አጣው፤ የጤና ሽፋኑ “100%” ደረሰ የሚለው ፕሮፓጋንዳ በኮሌራና መሰል ውሃ ወለድ በሽታዎች አስደንጋጭ ዜና የጤና ሽፋኑን አይረቤነት እያየ ነው። የአገሪቱ የትምህርት ሽፋን “96% በላይ” ደረሰ የሚለው ዜና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የማያቋርጥ ፍልሰት፣ በከተሞች በየጎዳናው ከተበተኑ ታዳጊ ህፃናት የጎዳና ህይወት፣ ትምህርት በዞረበት ያልዞሩ ሴተኛ አዳሪዎች፣ … የትምህርት ሽፋኑ ደረሰ የተባለበት ቁጥር ላይ ለመድረሱ ብርቱ ጥርጣሬ ያድርብናል።
ከሁሉ በላይ አስፈሪው ነገር እውነት እየሰለለች ውሸት እየፋፋ መሄዱ እንደ አገር ያሉብንን ችግሮች አወሳስቧቸዋል። ከችግሮቻችን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛታቸው የእውነትን ቀጭን መስመር ይበልጥ ገዝግዞታል። እነርሱም ያለቅጥ ይዋሻሉ፤ የማይፈጽሙትን ተስፋ እንደ ጣቃ ጨርቅ በየቀኑ ይቀዳሉ፤ ነጻነት የናፈቀውን ሕዝብ ገንዘቡን፣ ጊዜውን አንዳንዴም ህይወቱ ይዘርፉታል፤ በመጨረሻ ከህወሓት ጋር አንሶላ ሲጋፈፉ ይገኛሉ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት እንደአገር የተጫነብን “መንግስታዊ” ውሸት ሁለንተናችን በክሎታል፤ አቆሽሾታል፤ አሳድፎታል። ከብክለቱ ለመፅዳት ማህበራዊ ወጌሻ ማግኘት ግድ ይለናል። ከዚያ በፊት ግን የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ይቀድማል። የአደበባይ “መንግሥታዊ” ውሸት ያነገሰብን አገዛዝ እስካልተነቀለ ድረስ ኢትዮጵያ ነፃ አትወጣም።
መርዛማ ፍሬ 6. የኃይማኖት ተቋማት ውድቀት!
በአስራ ሰባት ዓመቱ ወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ጊዜ የኃይማኖት ተቋማት እመቃ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነበር። ከ“ህግ” ሽፋን ጀርባ ከደርግ ግራ ዘመም እይታ የበዛ አክራሪ የሆነው ህወሓት “መንገዴ” ከሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መነፅር አኳያ የኃይማኖት ተቋማቱን እንደሚመለከት ይታወቃል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በባህሪው የየትኛውንም ተቋማት ነፃነት ከቶውንም ማየት የማይሻ፣ የተቋማቱ ነፃ ሆኖ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ረዣዥም እጆቹን ደጋግሞ እየጫነ ሲጨፈለቅና ሲያስጨፈልቅ እንደኖረ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። በዚህ ረገድ የኃይማኖት ተቋማቱን ነፃነት በመንፈግ ፈርጣማ የፖለቲካ ክንዱን አሳርፎባቸዋል። በዚህ የተነሳ የኃይማኖት ተቋማቱ ተቋማዊና ሞራላዊ ውድቀት ላይ ናቸው።
ህወሓት ወደ በረሃ ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ “ማህበራዊ ጠላት” አድርጎ የፈረጀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ነው። በበረሃ ቆይታውም ዋልድባን ጨምሮ ትልልቅ ገዳማትን በመሰለልና በማሰለል የቤተክርስቲያናቱን ምስጢራት ሲያራክስና ቅርሷን ሲያወድም፤ ለባዕዳን ሲቸበችብ ቆይቷል። ወደ አገዛዝ መንበሩ ሲመጣም በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁለቱን (ክርስትናን እና እስልምናን) ግዙፍ ኃይማኖታዊ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዕቅዱን ዳር ለማድረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በኩል በህይወት ያሉትን ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስን በማባረር ኃይማኖታዊ ቀኖናውን በፍፁም በሚጋፋ መልኩ የህወሓት ጉዳይ ፈፃሚ የነበሩትን የአድዋውን ተወላጅ፣ ከመለስ ጋር አብረው የተሸኙትን አቡነ ጳውሎስን በምትካቸው የተኩበት ሁኔታ፤ በድህረ ደርግ ጊዜያት ለህወሓቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአፈና መንገድ እና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖታዊ ተቋም ውድቀት ጅማሬ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ማህበራዊ ቦታ ተነፍጎ የቆየውን እስልምናን በ“ኃይማኖት ነፃነት” ሥም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲያውል የቆየው ህወሓት/ኢህአዴግ በጊዜ ሂደት ከኃይማኖቱ ሊሂቃን ጋር በቀጥታ ተላትሟል። የ“አወሊያ ንቅናቄ”ን መነሻው ያደረገው ትግል የአገዛዙ ራስ ምታት ሆኖ ከርሟል። ክፉ ጠባሳው ዛሬም ድረስ አልሻረም። በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፊት አውራሪነት “እስልምናን በቁጥጥር ስር የማዋል” እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተላበሰ እስልምና የመፍጠር ዓላማ” ያነገበው ዘመቻ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው በመሆኑ ለበርካታ ወጣቶች ህይወት ማለፍ፣የአካል መጉደልና የሙስሊሙ ወኪሎች “ኮሚቴዎች” በሃሳዊ ወንጀል በካንጋሮው ፍርድ ቤት በኩል ወደ እስር ሲወረወሩ አይተናል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በግልጽ የሚታዩትን የሁለቱን ኃይማኖት “ሲኖዶስ” እና “መጅሊስ” በማይታይ ስውር መዳፉ ጨብጦ እየጋለበ ኃይማኖታዊ ተቋማቱን የፖለቲካ ክንፍ እንዲሆኑ አርክሷቸዋል። በሁሉም ኃይማኖቶች በተቋም ደረጃ በተሰገሰጉ የአገዛዙ ቅጥረኛ የኃይማኖት “መሪዎች” አገርንና ትውልድን ከጥፋት ከመታደግ ይልቅ የአገዛዙን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስቀጠል የሚተጉ፣ የፈጣሪን ቃል ከመስበክ ይልቅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ “የልማት መሪ ሃሳብ” ማንነታቸውን የተቆጣጠራቸው፤ ህወሓት/ኢህአዴግን መቃወም ፖለቲካ፣ መደገፍ ግን ኢትዮጵያዊነት የሚመስላቸው፤ ከአባታዊ ተግባር በተቃራኒው ፖለቲካዊና “”ልማታዊ ሚና ያላቸው መሆኑ ለኃይማኖት ተቋማቱ ውድቀት በር ከፋች ሆኗል።
የኃይማኖት ተቋማቱ የአገዛዙን የፖለቲካ መስመር ጠብቀው እስከተጓዙ፣ የፖለቲካ ታዛዥነታቸውን በአሜን ባይነት ስሜት እስከተቀበሉ ድረስ በተቋማቱ ውስጥ ያሉትን ብልሹ አሰራሮችንም ሆነ አይን ያወጡ የዘረፋ ተግባራትን በተመለከተ ጠያቂ የለባቸውም። የቤተ-እምነቶች አፀደ በንግድ ተቋማት ተወርሮ፣ ሰማያዊ ተልዕኳቸው ቀርቶ ንግድ ተኮር የሆነ ተግባር ላይ ተዘፍቀዋል። የኃይማኖት “መሪዎች” አገዛዙ በምልዐት እያስቀጠለ ያለውን አገራዊ የዘረፋ ተግባር በየተቋማቶቸቸው አጠናክረው ቀጥለዋል። “ምላጭ ካበጠ በምን ይበጡ? ውሃ ካነቀ በምን ይውጡ?” እንዲሉ የኃይማኖት ተቋማቱ በዚህ መሰል የሞራል ልሽቀት እየተጓዙ ባሉበት ሁኔታ አገሪቱንና ትውልዱን የሚያስቡ የኃይማኖት “አባቶች” አደባባዩ ላይ ተመናምነዋል። በአገዛዙ የፖለቲካ አካሄድ እየደረሱ ያሉትን ማህበራዊ ቀውሶች ሊጠግንና ሊያሻሽል የሚችል ማህበራዊ ኃይል ከቶም በጠፋባት ኢትዮጵያ፣ የኃይማኖት ተቋማት እንደ ተቋም መውደቃቸው ሰብዓዊና መንፈሣዊ ንጥፈት የተበራከተበት ዘመን ላይ አድርሶናል።
የኃይማኖት ተቋማትን ከሰማያዊ ተልዕኮ ወደ ዓለማዊ (ፖለቲካዊ) ግብ ያወረደው አገዛዝ ራዕይ አልባ የሚባክን ትውልድ፣ የታቦታት ነጋዴ ካህን፣ ንግድና ኡላማነት የተምታታበት ሼኽ፣ ባለትዳር አማጋጭ ፓስተር፣ ፈሪሃ-ፈጣሪ የሌለባቸው ስግብግብ ነጋዴዎች (ጀሶን ከጤፍ ጋር ቀላቅለው እንጀራ ብለው የሚሸጡ አውሬዎችን)፣ … በማፍራት ረገድ ተሳክቶለታል። የዚህ ሁሉ ማህበራዊ ቁልቁለት ሥረ-ምክንያት የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ የወለደው የኃይማኖታዊ ተቋማት ውድቀት መሆኑ ችግሮቻችንን ከፖለቲካው በላይ አወሳስቦታል።
መርዛማ ፍሬ 7፡ የኢትዮጵያዊነት ፈተና!
ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ከአካባቢያዊ ማንነትና ከጎሣ በተሻገረ ለኢትዮጵያዊነት መታመን ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ ዋጋ የሚያስከፍል አደጋ ሆኗል። እስር፣ እንግልት፣ ስቅየት፣ ስደት፣ እልፍ ሲል ደግሞ ሞት በኢትዮጵያዊነት የመታመን አደጋዎች ናቸው። በዜግነት ማዕቀፍ የሚተረጎም የጋራ ማንነት በቀጨጨባት ኢትዮጵያ ዘውጋዊ ማንነት የፖለቲካ ሜዳው መገለጫ ሆኗል። ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ አገር እውን ከሆነች ወዲህ ኢትዮጵያዊ መሆን (ዜጋ) እና ኢትዮጵያዊነት እንዲህ እንደ ህወሓት የአገዛዝ ዘመን የፖለቲካ ልዩነት ምንጭ እና አከራካሪ የሆነበት ዘመን አልነበረም ማለት ይቻላል። ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ የዘውግ ፖለቲካ የሁሉም ነገር መስፈርት በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ፈተና ላይ ወድቋል። በዚህም የአንድነት ሳይሆን የመለያየትና የቅራኔ ምንጭ መሆን በህዝቡ ዘንድ ስጋትና ውጥረት ሲፈጥር ይታያል። ዘውጋዊ ግጭቶችም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ስፖርት ሜዳዎች ድረስ እየታዩ ነው።
በአካባቢያዊ ማንነት የታጠረ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኙ ህወሓት የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመቅበር ረዥም ርቀት ተጉዟል። በአደባባይ “የጋራ ማንነት የለንም” የሚለውን የታሪክ ኑፋቄ ከማስማት እስከ ታሪክ ክለሳ ድረስ፣ የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማንሳት ትውልድ ከፋፋይ ሃውልቶችን ከማቆም እስከ የወል የማህበራዊ እሴቶችን የማጥፋት እኩይ ድርጊት፣… የደረሱ አውዳሚ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።
ቂምን ለትውልድ በማውረስ ኢትዮጵያዊነትን እያከሰመ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ለመሹለኪያ ይሆነዉ ዘንድ ትግራይን እንደ አገር የመገንባት ሂደቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። የቅኝ ገዥ ባህሪ የሚንፀባረቅበት ይሄው ድርጅት ኢትዮጵያን እንደ አገር ያቆሟትን አገራዊ አዕማዶች በማፍረስ ተጠምዷል። በርግጥ በዚህ እኩይ ተግባር የተጠመደው ህወኃት ብቻ ሳይሆን በተቃውሞ ጎራው ያሉት የዲያስፖራ አክራሪ ዘውጌ ብሄርተኞችም የድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው። የሳይበር ልፈፋው መዋቅራዊ ድጋፋ ካለው የህወሓት አፍራሽ ድርጊት ጋር የሚነፃፀር እንዳልሆነ ግን እንረዳለን። የግራ ቀኙ አዉዳሚ ተግባር አገሪቱን ወደብተና እየገፋት ይገኛል።
የትላንቷ ኢትዮጵያ ፍጹም ልክ ነበረች ማለት ተገቢ ባይሆንም የጊዜውን አስገዳጅነት የተከለች ነፃ አገር ኢትዮጵያ መመስረቷ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይመስለንም። በዚህ አግባብ ኢትዮጵያዊነት በጭፍን የሚቀበሉት ውርስ ቀኖና አይደለም። ይልቁንም እንደዘመኑ ማህበረ-ፖለቲካ የለውጥ ሂደት እየተገለጸ የሚሄድና የሚሻሻል አካታች አገራዊ ምልከታ ውጤት ነው።
የትላንት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዛሬው የኢትዮጵያዊነት እርሾው የሚዘነጋ አይደለም።ይህም ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ባለበት መርገጥ ግድ የሚለው አጀንዳ ሳይሆን ተራማጅነቱን የማያቋርጥ የጋራ ቤት ምስረታ (አገረ-መንግስት) ሂደት ባካተተ መልኩ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚመጥን የኢትዮጰያዊነት ስሜት ለመፍጠር የተሻለ መንገድ እንደሆነ ይስማናል። ኢትዮጵያዊነት ከአካባቢያዊ ማንነት በተሻገረ ዜግነትን የተንተራሰ የአገራዊ ምልከታ ውጤት ነው። በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቅርሶች መገለጫቸውና ሃብትነታቸው አገር አቀፍ እንዲሆን የሚያስችል መዳረሻውን (ግቡን) የጋራ ማንነት በማጠናከር ላይ የሚያተኩር አገራዊ ስሜት ነው።
እውነታው ከዚህ በተቃራኒው እየሆነ መሆኑ ግን ኢትዮጵያዊነትን ፈተና ላይ ጥሎታል። የኢትዮጵያዊነት ፈተና በማወሳሰቡ ረገድ ደግሞ ህወሓት መዋቅራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ሌት ተቀን ተግቶ እየሰራበት ይገኛል። በርግጥ ኢትዮጵያዊነት ከተጋረጠበት ፈተናም ሆነ ከቀደመ ውርስ ቀኖናዊ ባህሪው ተሻግሮ አካቶነት ያለው የጋራ ማንነት ማሳደግ የሚችል የአገራዊ ስሜት መገለጫ እንዲሆን ከተፈለገ የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ ባለቤት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ መቅበር ግድ ይላል።
መርዛማ ፍሬ 8. የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ!
በ1987 ዓ.ም በብዙ ንትርኮች ግን ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ ርዕዮት ዓለም የተቀነበበው “ሕገ-መንግስት” ሲፀድቅ፤ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ለቀጠሉ የህዝባዊ ተቃውሞ ጥያቄዎች መስረታዊ መነሻ የሆኑ ጭብጦችን ቢያካትትም የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲመጣ ሊጠቀም ይችላል የሚያስብሉ አንቀፆችን አካትቶ ነበር። ለዚህ መሰሉ ተስፈኝነት አስተዋፆኦ ያደረጉት ደግሞ፣ በሰነዱ ላይ የተካተቱት በነፃ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ እንዲሁም በምርጫ ፖለቲካ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ የሚያስችሉ አንቀፆች መኖራቸው ነበር።
ይሁንና ከነእንከኑ “ሕገ-መንግስቱ” ከፀደቀ ማግስት ጀምሮ በተደረጉት ተከታታይ ፌዴራላዊና የአካባቢ “ምርጫዎች” የመድብለ ፖርቲ ሥርዓት ህልው የሚሆንበትን ዕድል በመጥበብ ጀምሮ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ ተዘርግቷል። በአገሪቱ የፖለቲካ ተቋማት መቃብር ላይ የቆመው አገዛዝ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት”ን ወደ “ህወሓት/ኢህአዴግ ምክር ቤት” ቀይሮታል። የፖለቲካ ምህዳሩን በመዘጋጋት የተጠመደው አገዛዝ መንግስታዊና ህዝባዊ ሃብትን በመጠቀም እስከ እያንዳንዱ ቤተሰብ በወረደ የ1፡5 ጥርነፋ አወቃቀር ጠቅላይ አምባ ገነንነቱን አደንድኖታል። አገዛዙ የተቃወሞ ፖለቲካ አመራሮችን በማስር፤ በማሳደድ እና በማዳከም የብቻ የረዥም ጊዜ ገዠነቱን ለማፅናት ብዙ ርቀት ሄዷል። ይህም የአፈና መንገድ፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን ከጅምሩ ከመቀልበሱ ባሻገር በ“ሕገ-መንግስቱ” የተቀመጠውን የመድብለ-ፓርቲ ፖለቲካን የመመስረት ህዝባዊ ዕድልን አጨልሞታል።
በውጤቱም አገሪቱን ወደብተና የሚገፉ ህዝባዊ አመፆች እዚህም እዚያም ገንፍለው ወጥተዋል። ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የኃይል አማራጭን የሙጥን ያለው አገዛዝ መንግስታዊ ፍጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። አገዛዙ የመጣበትን መንገድ ምርጫቸው ያደረጉ የነፃነት ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት አገሪቱን “መንግስት” አልባ አስመስሏታል። በጎንደርና ባህርዳር አካባቢ በየጊዜው እየፈነዱ ያሉ ቦምቦች የጋዛ ሰርጥን ውጥረት የሚያስታዉስ ሆኗል። የፖለቲካ ነፃነት እጦት እና የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ ወደ ህዝባዊ አመጽ እና የህብዑ ጥቃት እንደሚገፋ የህወሓቷ ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ምሳሌ ነች።
ህወሓት/ኢህአዴግ “እታመንለታለሁ” የሚለውን “ሕገ መንግስት” በመጨፍለቅ የሚስተካከለው የፖለቲካ ኃይል የለም። “ሕገ-መንግስት” መኖሩ ትዝ የሚለውም ሆነ የሚያስታውሰው በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችንና የፓርቲ-ፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦችን ከነፓርቲያቸው ለመምታት “ህገ – መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ …” የሚል ሃሳዊ የውንጀላ “ክስ” ለመመስረት ሲፈልግ ብቻ ለመሆኑ በተደጋጋሚ የታየ እውነታ ነው።
የኢትዮጵያን ማህበራዊ ስሪት በቅጡ መረዳት ባልቻሉት የትግራይ ሽፍቶች የሚመራው ህወሓት በበረሃ በኩል በምዕራባውን አንጋሾቹ ተረድቶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የሰላማዊ ትግል ጀምበር ለአፍታ ፈንጥቃ ተመልሳ በማዘቅዘቋ ብረት ማንሳት ብቸኛ የነፃነት መንገድ ሆኖ ቀርቧል። አሁን ባለው ዘውጋዊ መካረር ኢትዮጵያን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበች አገር አድርጓታል። የችግሩ መውጫ ጫፍ ከነፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንም ቢሆን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሙሉ ኃይልን ማሳረፍ ያልተፈተሸው የትግል መንገድ ነው በማለት በርካታዎች ይከራከራሉ። ነውጥ አልባ ትግልን በፍጹም ልባቸው የሚደግፉና የሚያምኑበት ደግሞ በትክክለኛው አልተሞከረም እንጂ ነውጥ አልባው መንገድ ለኢትዮጵያ ችግር ፍቱን ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵ የተካሄደውን ትግል ሰላማዊ የፓርቲ ምርጫ ትግል እንጂ እውነተኛ ነውጥ አልባ ትግል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
የግንቦት ሃያን መርዛማ ፍሬዎች በተከታታይ ዕትም መዳሰሳችን ይቀጥላል።